1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የኢትዮጵያ ኤርትራ ግንኙነት

ዓርብ፣ ሰኔ 22 2010

ኢትዮጵያ ከጥቂት ሳምንታት  በፊት ለኤርትራ የሰላም እና የእርቅ ጥሪ ካቀረበች በኋላ አንድ ከፍተኛ የኤርትራ የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ ገባ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ እና ከፍተኛ ባለስልጣናት የልዑካኑን ቡድን በቦሌ አየር ማረፊያ ተቀብለዋል።

https://p.dw.com/p/30Kh3
Karte Äthiopien Eritrea Grenze Englisch

«ፍጥጫ/ግጭት የሚያበቃ ማንኛውም ርምጃ በጣም ተቀባይነት አለው።»

ይህ የዛሬው ግንኙነት በድንበር ውዝግብ ሰበብ ለሁለት አሰርተ ዓመት ግንኙነታቸው ተቋርጦ ለቆዩት ሁለት ሀገራት ከፍተኛ ትርጓሜ እንደያዘ  የኢትዮ ኤርትራን ጉዳይ በቅርብ የሚከታተሉ አንድ ጋዜጠኛ እና አንዲት ጀርመናዊት ፖለቲከኛ ገልጸዋል።

የኤርትራ የልዑካን ቡድን ዛሬ አዲስ አበባ የገባው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል እንደአዉሮጳ አቆጣጠር ከ1998 እስከ 2000 ዓም የተካሄደውን የድንበር ጦርነት ያበቃውን የአልጀርስ ስምምነት ኢትዮጵያ ካላንዳች ቅድመ ግዴታ እንደምትቀበል እና የድንበር አካላይ ኮሚሽኑን ውሳኔም ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደምታደርግ ያስታወቁበት ውሳኔአቸው ከኤርትራ በኩል ባለፈው ሳምንት ያገኘውን አዎንታዊ ምላሽ ተከትሎ ነው። የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂ አማካሪ እና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ ፣ የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳሌህ እና በአፍሪቃ ህብረት የኤርትራ አምባሳደር አቶ አርአያ ደስታ የሚገኙበት የልዑካን ቡድን ከሃያ ዓመት የግንኙነት መቋረጥ በኋላ አሁን ለመጀመሪያ ውይይት አዲስ አበባ መግባቱን ጀርመናዊቷ የጀርመን አፍሪቃ ተቋም ፕሬዚደንት ኡሺ አይድ የሚሞገስ ብለውታል።
« ይህን የዛሬውን ግንኙነት ታሪካዊ እለዋለሁ። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ላለፉት ሃያ ዓመታት አንዳችም ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ስላልነበረ አሁን ይህ የመጀመሪያ ርምጃ በመወሰዱ ደስ ብሎኛል። ምክንያቱም፣ በሁለቱ ሃገራት መካከል ለብዙ ዓመታት የዘለቀው ውዝግብ ሲታሰብ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የወሰዱት ውሳኔ በጣም ከፍተኛ ቆራጥነት የታየበት እና የኤርትራ ፕሬዚደንት ኢሳይያስ አፈወርቂም ለኢትዮጵያ ግብዣ አዎንታዊ መልስ የሰጡበት ነው። »
የዛሬው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ከፍተኛ ባለስልጣናት በአዲስ አበባ መገናኘት ባለፉት ሁለት አሰርተ ዓመት አንዳችም ግንኙነት ያልነበራቸውን የሁለቱን ሃገራት የድንበር ውዝግብ በማብቃቱ ረገድ የሚረዳ አዎንታዊ ርምጃ መሆኑን ብሪታንያዊው ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውትም ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል።
« ይህ የመጀመሪያ ግንኙነት ከሃያ ዓመት አንዳችም እንቅስቃሴ ያልታየበት የድንበር ውዝግብ በኋላ እንደ በጎ የሚታይ ሂደት ነው። በዚሁ ጦርነትም ሰላምም የሌለበት በተባለው ውዝግብ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ጦር ኃይላት ፊት ለፊት የተፋጠጡበት እና አልፎ አልፎም ከድንበር ባሻገር የሚታኮሱበት ሁኔታ ነው የታየው። እና ይህን ፍጥጫ/ግጭት የሚያበቃ ማንኛውም ርምጃ በጣም ተቀባይነት አለው።»
የሁለቱ ሃገራት ችግሮች በአንድ ግንኙነት ብቻ የሚወገዱ እንዳልሆኑ ኡሺ አይድ በመግለጽ ከሁለቱ ወገኖች ሌሎች ተጨባጭ ርምጃዎች እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
« በፖለቲካው ዘርፍ ይህ የመጀመሪያ ርምጃ  በሁለቱ አገሮች መካከል ያሉትን ችግሮች ሁሉ ሊያወገዱ የሚያስችሉ ሌሎች ውይይቶችም እንደሚከተሉ የሚጠቁም መሆን አለበት።  የዛሬው ግንኙነት ለሁለቱ ሃገራት የመጀመሪያ የመቀራረብ ርምጃ በር ከፋች ብቻ ነው። ስለዚህ ሌሎች ተጨማሪ ርምጃዎች ያስፈልጋሉ። »
ይሁንና፣ ይህ በአንድ ውይይት እውን እንደማይሆን ባስታወቁት ኡሺ አይድ አስተያየት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሌሎች፣ ለምሳሌ፣ እርሳቸው እንደሚሉት፣  ድንበር ማካለልን፣ ዲፕሎማቲክ ግንኑነታቸውን መልሰው ማደስን እና መሰል ርምጃዎች ከመውሰዳቸው በፊት በመካከላቸው ጠፍቷል የሚሉትን መተማመን እንደገና ለመመለስ የሚያስችል የመጀመሪያ መቀራረብ አድርገው ተመልክተውታል። ልክ እንደ አይድ ጋዜጠኛው ማርቲን ፕላውትም መተማመኑ መልሶ ሊፈጠር ይገባል ይላል።
« እርግጥ ነው መወገድ ያለባቸው ግዙፍ እንቅፋቶች አሉ። ዋነኛው በሁለቱ መካከል ያለው አለመተማመን ነው። ምክንያቱም እርስ በርስ በጥርጣሬ ሳትተያይ ለዚህ ያህል ረጅም ጊዜ ፍጥጫ ላይ ልትቆይ አትችልም። እና የመጀመሪያው ተግባር መሆን ያለበት እምነት መፍጠር ነው። »
ሁለቱን በጥርጣሬ የሚተያዩትን ሃገራት በማቀራረቡ ረገድ የአልጀርስ ስምምነት ሲፈረም በታዛቢነት የተገኙት እና ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን አለመሆኑን የሚጠባበቁ ሃገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሚና ሊኖራቸው እንደሚገባ እና በተለይ አወዛጋቢውን ድንበር በማካለሉ ረገድ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ ማርቲን ፕላውት አስገንዝበዋል። 

Äthiopien Addis Abeba Abiy Ahmed begrüßt Delegation aus Eritrea
ምስል Prime Minister Office/Fitsum Arega

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ