1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ «ሲፌፓ»

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 24 2014

በሲዳማ ክልል የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓ የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተመሠረተ፡፡ ፓርቲው ሊመሠረት የቻለው የሲዳማ ህዝብ ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ጠንካራ የፓለቲካ ፓርቲ በማስፈለጉ መሆኑን የፓርቲው ተመራጭ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4GE9E
Äthiopien | SFP Parteikongress
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

ፓርቲው የተመሰረተዉ የሲዳማ ህዝብ ለወቅቱ የፖለቲካ ትግል ጠንካራ የፓለቲካ ፓርቲ በማስፈለጉ ነዉ

በሲዳማ ክልል የሲዳማ ፌዴራሊስት ፓርቲ ሲፌፓ የተባለ አዲስ የፖለቲካ ድርጅት ዛሬ በሀዋሳ ከተማ በይፋ ተመሠረተ፡፡ ፓርቲው ሊመሠረት የቻለው የሲዳማ ህዝብ ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ጠንካራ የፓለቲካ ፓርቲ በማስፈለጉ መሆኑን  የፓርቲው ተመራጭ አመራሮች ገልጸዋል፡፡

Äthiopien | SFP Parteikongress
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው መሥራች ጉባኤ የተመሠረተው የፖለቲካ ድርጅት የሲዳማ ፌዴራሊስት ፖርቲ ወይም ሲፌፖ የሚል መጠሪያ ያለው ነው፡፡ በጉባኤው ላይ እንደተገለፀው ፖርቲው ምስረታውን ያካሄደው ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ባገኘው ጊዜያዊ የእውቅና ፈቃድ መሠረት ነው ፡፡ ፓርቲው ባለፉት ሦስት  ወራት ለምስረታ የሚያስፈልገውን የድጋፍ ፊርማ ሲያሰባስብና የአባላት ምልመላ ሲያካሄድ መቆየቱን የፖርቲው መሥራቾች ተናግረዋል፡፡ ከፖርቲው መሥራቾች አንዱ አቶ ጴጥሮስ ደቢሶ ፓርቲው ሊመሠረት የቻለው የሲዳማ ህዝብ ወቅቱ የሚፈልገውን የፖለቲካ ትግል ለማካሄድ ጠንካራ የፓለቲካ ፓርቲ በማስፈለጉ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

አዲሱን የሲዳማ ፌዴራሊስት ፖርቲ በሊቀመንበርነት እንዲመሩ የተመረጡት ረዳት ኘሮፌሰር ተሰማ ኤሊያስ በበኩላቸው ፖርቲው በቀጣይ ሊሠራ አቅዶል ያሏቸውን ሥራዎች ለዶቼ ቨለ «DW» ተናግረዋል፡፡ ረዳት ኘሮፌሰር ተሰማ በማያያዝም  ‹‹ ሴፌፖ በቅድሚያ ትኩረት አድርጎ ለመስራት ያቀደው የሲዳማ ህዝብን አንድነት የማስጠበቅ ስራ ነው፡፡ ምክንያቱም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህዝቡ መካከል የጎሰኝነት ስሜት እያቆጠቆጠ ያለበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ይህ ደግሞ የክልሉን ህዝብ የዲሞክራሲያና የልማት ተጠቃሚ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል፡፡ በመሆኑም ፖርቲያችን ቅድሚያ እንደህዝብ አንድነቱን ለማስጠበቅ ይሰራል ፤ በመቀጠል የስራ አጥነትን ለመቀነስ ልማትና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ይታገላል ›› ብለዋል ፡፡

Äthiopien | SFP Parteikongress
ምስል Shewangzaw Wegayehu/DW

በሲዳማ ክልል በአሁኑ ወቅት 12 የፖለቲካ ፖርቲዎች ተመዝግበው በሥራ ላይ እንደሚገኙ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ፓርቲዎች አብዛኞቹ በምርጫ ወቅት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባለፈ የጎላ ፖለቲካዊ ተጽዕኖ እንደሌላቸው ይናገራል፡፡ በሲፌፖ የምስረታ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን በመወከል የተገኙት አቶ ፍሬው በቀለ ፖርቲዎች ለዲሞክራሲ ባህል መጎልበት አሁን ያላቸው ሚና ከፍ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ ለዶቼ ቬለ «DW» ገልፀዋል፡፡

በሲዳማ ፌዴራሊስት ፖርቲ የምሥረታ ጉባኤ ላይ ከ300 በላይ ጉባኤተኞች የተገኙ ሲሆን የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ምርጫም ተከናውኗል ፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ