አዲሱ የሊቢያ ምክር ቤት ሥልጣን መረከቡ
ሐሙስ፣ ነሐሴ 3 2004የሊቢያ የሽግግር ምክር ቤት ለአዲሱ አጠቃላይ ብሄራዊ ምክር ቤት ስልጣኑን ትናንት ማምሻዉን በይፋ አሸጋገረ። ባለፈዉ በተካሄደዉ ብሄራዊ ምርጫ ለተመረጠዉ አጠቃላይ ብሄራዊ ምክር ቤት ስልጣኑን ያስረከቡት የሽግግር ምክር ቤቱ የበላይ ሙስጠፋ አብደል ጃሊል፤ ዕለቱን ታሪካዊ ብለዉታል። የምክር ቤቱ 200 አባላት የስልጣን ሽግግሩ ከመደረጉ ሰዓታት አስቀድሞ ቃለመሀላ ፈፅመዋል። በሙስሊሞች የሮመዳን ፆም ምክንያት ማምሻዉን የተከናወነዉ የስልጣን ሽግግር ሂደትም ከ40ዓመቱ የኮሎኔል ሞሐመድ ኤል ጋዳፊ ከስልጣን መባረር በኋላ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተምሳሌት ተብሏል።
ምክር ቤቱ መንግስት የሚመሠርት አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰይማል። ሊቢያ ሙሉ ምክር ቤታዊ ምርጫ እንድታካሂድ የሚያስችል ህግና መመሪያም ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የምክር ቤቱ አባላት ከግል እጩዎችና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተዉጣጡ መሆናቸዉ ተዘግቧል።
በመዲናይቱ ትሪፖሊ የተከናወነው የርክክብ ሥነ ሥርዓት በሀገሪቱ ታሪክ ውስጥ ሥልጣን በሰላማዊ መንገድ የተላለፈበት የመጀመሪያው ነው። ስለሰላማዊው የሥልጣን ርክክብ ቀደም ሲል ስቱድዮ ከመግባቴ በፊት የጄዳውን ወኪላችን ነቢዩ ሲራክን አነጋግሬ ነበር። በመጀመሪያ የጠየቅሁት የአዲሱ የሊቢያ ምክር ቤት የወደፊት ተግባር ምን ሊሆን እንደሚችልና የሊቢያስ ሕዝብ ከአዲሱ ምክር ቤት ምን እንደሚጠብቅ ነበር።
ሸዋዬ ለገሠ/ ነቢዩ ሲራክ
አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ