1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አንጎላ:- የባይደን የመጨረሻ የአፍሪቃ ጉብኝት

ቅዳሜ፣ ኅዳር 21 2017

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ስልጣናቸዉን ከመልቀቃቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ አፍሪቃን ለመጎብኘት የገቡትን ቃል እየፈፀሙ ነው። ጆ ባይደን ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ የሚጎበኝዋት አፍሪቃዊትዋ አገር አንጎላ እንዲጎበኙዋት በአጋጣሚ አልተመረጠችም።

https://p.dw.com/p/4nbMF
USA Angola l Joe Biden mit Präsident Joao Manuel Goncalves Lourenco in  Washington
ምስል Yuri Gripas/ABACAPRESS/picture alliance

አንጎላ:- የባይደን የመጨረሻ የአፍሪቃ ጉብኝት

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ስልጣናቸዉን ከመልቀቃቸዉ ጥቂት ቀደም ብሎ አፍሪቃን ለመጎብኘት የገቡትን ቃል እየፈፀሙ ነው። ጆ ባይደን ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ የሚጎበኝዋት አፍሪቃዊትዋ አገር አንጎላ እንዲጎበኙዋት በአጋጣሚ አልተመረጠችም።  

ተሰናባቹ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆባይደን የተሳፈሩበት የሃገሪቱ አየር ኃይል አዉሮፕላን የፊታችን ሰኞ መዲና ሉዋንዳ ካረፈ በኋላ ባይደን በአንጎላ ላይ ብዙ መረሃግብሮችን እንዳላቸዉ ታዉቋል። ባይደን ወታደራዊ፣ ፖለቲካዊ እና በተለይም የኢኮኖሚ ስምምነቶች ይፈርማሉ ተብሎ  ይጠበቃል።  ይህም በዩናይትድ ስቴትስ እና በአንጎላ መካከል ያለው ትብብር ያጠናክራል ተብሎም ታምኖበታል።

አንጎላዊዉ የፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ክላዉዲዮ ሲልቪዮ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት የአንጎላ ጉብኝት  የመጣዉ፤ የአንጎላዉ ፕሬዚደንት ዦው ሉሬንሶ ለዓመታት የሰሩት የዲፕሎማሲ ጥረቶች ዉጤት ነዉ።

«የአሜሪካዉ ፕሬዚዳንት ወደ አንጎላ የመጓዝ እቅድየተሰማዉ ፤ የአንጎላ ፕሬዝዳንት ለዓመታት ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ካደረጉ በኋላ ነዉ። የአንጎላዉ ፕሬዝደንት ዦው ሉሬንሶ ሐገሪቱ በዓለም አቀፉ መድረክ የበለጠ ዕውቅና እንድታገኝ  ለዓመታት ያደረጉት ዲፕሎማሲ ጥረት ድል መሆኑ አያጠራጥርም። አሁን የዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን ፍሬ በመሰብሰብ ላይ ትገኛለች።»

የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግን እና የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዦዋዉ ሉሬንሶ በቤጂንግ
የቻይና ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግን እና የአንጎላ ፕሬዚዳንት ዦዋዉ ሉሬንሶ በቤጂንግምስል Li Xueren/Xinhua/Imago

ከአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ከአንጎላ ጋር ውሎችን ለመፈረም ጊዜው ተቃርቧል ሲሉ ዦው ሉሬንሶ መናገራቸዉን የፖለቲካ ተንታኙ ክላውዲዮ ሲልቫ አክለዉ ተናግረዋል። በሁለቱም ሃገራት መካከል ለረጅም ጊዜ የታቀዱ ኢኮኖምያዊ ፕሮጀክቶች በሁለቱም ወገኖች በኩል ቅድሚያ እንደተሰጠዉ መሰጠቱም ተመልክቷል።

ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕቅዶች

ዩናይትድ ስቴትስ አንጎላ ዉስጥ ከምትሳተፍባቸዉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል በሰሜን አንጎላ የሚገኘው የሶዮ ዘይት ማጣሪያ ግንባታ ስራ እንዲሁም በጀርመን የብድር ዋስትናዎችም የሚደገዉ እና ከሰሃራ በታች የሚገኘዉ የአፍሪቃ ትልቁ  "የገጠር ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት" ይገኙበታል።

ይሁን እና ትልቁ ግንባት "ሎቢቶ ኮሪዶር” እየተባለ የሚጠራው ነው። ይህ ግንባታ በአንጎላ አዋሳን የአትላንቲክ የባህር ዳርቻ ላይ በሚገን በሎቢቶ የባህር ወደብ እና የዛምቢያን ኮፐርቤልት እንዲሁም የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የኮባልት ማዕድን ሀብት ማመንጫን የሚያገናኝ የባቡር መስመር ዝርጋታን የሚያካትት ነዉ። ይህ የባቡር መስመር በጥሪ ሀብት የበለፀጉትን የመካከለኛው አፍሪቃን ክልሎች በአትላንቲክ የባህር ወደቦች ለማገናኘት ያለመም ነው።

ታዛራ - ከታንዛኒያ ወደ ዛምቢያ በባቡር
ታዛራ - ከታንዛኒያ ወደ ዛምቢያ በባቡርምስል Autentic

"ሎቢቶ ኮሪዶር” አሜሪካ ለዓለምአቀፍ መሠረተ ልማት እና ኢንቨስትመንት የምታደርገዉ አጋርነት (PGI) አንዱ አካል ነው፣ ብዙዎች ይህን የአሜሪካን መሰረተ ልማት ለታዋቂው የቻይና "የቀበቶ የመንገድ መሠረተ ልማት መርሃ ግብር” ምላሽ አድርገው ይመለከቱታል። በዚህም አለ በዝያ መሰረተ ልማቱ ከሀብት እና ከንግድ ጋር ግንኙነቶችን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

1,344 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለዉ የ "ሎቢቶ ኮሪዶር”  አንጎላን ከምዕራብ ወደ ምስራቅ የሚያቋርጥ እና ከኮንጎ የባቡር መስመር ጋር የሚያገናኝ ነዉ። በአንጎላ ለሦስት አስርት ዓመታት በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት፣ 34 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመኪና መንገድ አገልግሎት ብቻ ነዉ የተረፈዉ። ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ ህብረት እና ከአፍሪቃ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ በዛምቢያ 550 ኪሎ ሜትር የባቡር መስመር እና 260 ኪሎ ሜትር የመንገድ ዝርጋታን ለመገንባት እቅድም ተይዟል። ይህ የ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ከአሜሪካ፣ ከአውሮጳ ህብረት እና ከአፍሪቃ ልማት ባንክ ድጋፍ የሚገኝ ነዉ። የፖለቲካ ተንታኙ ክላውዲዮ ሲልቫ እንደሚሉት ቻይና አካባቢዉ ላይ ለረጅም ዓመታት ፍላጎትዋን አሳይታለች። 

ኮንጎ - የመዳብ እና የኮባልት ማዕድን ማዉጫ
ኮንጎ - የመዳብ እና የኮባልት ማዕድን ማዉጫምስል EMMET LIVINGSTONE/AFP/Getty Images

"ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው ያሉትን በርካታ ጠቃሚ ጥሬ እቃዎች ለቻይናውያን አሳልፋ መስጠት አትፈልግም። ጥያቄዉ ነገር ግን አሜሪካኖች በአካባቢው ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሲሳተፉ ከቆዩት ከቻይናውያን ጋር መወዳደር ይችላሉ ወይ የሚለዉ ነዉ። ቻይና በ 1970 ዎቹ ጀምሮ አካባቢዉ ላይ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ አፍስሳለች። ቻይናውያን በአካባቢው ያለውን የጥሬ ዕቃ ማለትም - የአንጎላ ዘይት፣ የዛምቢያ መዳብ እና የኮንጐን ኮባልት ይፈልጋሉ።"

የአሜሪካ-ቻይና ዉዝግብ አፍሪካን ያካልላል

"ሎቢቶ ኮሪዶር” መካከለኛው አፍሪቃን ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ለማገናኘት ያለመ መስመርም ነዉ። ቻይና በበኩልዋ ህንድ ውቅያኖስን የሚያገናኝ አዲስ መስመር እየዘረጋች ነው። እ.ኤ.አ. መጋቢት 2024 የቤጂንጉ መንግሥት የታንዛኒያ ዛምቢያ የባቡር መስመርን (TAZARA) በአንድ ቢሊዮን ዶላር ወጪ መስፋፋቱን አስታውቋል።

የቻይና፣ የሩሲያ እና የአሜሪካ፡ የቀጭን ገመድ ላይ ጉዞ

የፖለቲካ ተንታኝ ሲልቫ "የአንጎላ ፕሬዝዳንት ከሁለቱም የኢኮኖሚ ኃያላን ሀገራት ጋር መስራት እንደሚፈልጉ ይገልፃሉ።

«የአንጎላ ፕሬዝዳንት ዦዋው ሉሬንሶ ከሁለቱም ትላልቅ ኃያላን ጋር ለመስራት እና በተቻለ መጠን ከዉድድሩ ተጠቃሚ ለመሆን ይፈልጋሉ። ሩሲያም ብትሆን በዚህ ፉክክር ሩጫ ላይ ናት። አንጎላ የጂኦ-ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታውን ጠንቅቃ ስለምታዉቅ  በተጫዋቾች መካከል ባለው ውድድር ለመጠቀም እየሞከረች ነው ።»

የጦር ሰፈር እቅድ ?

የፖለቲካ ተንታኙ እንደተናገሩት ፕሬዚደንት ዦዋው ሉሬንሶ በመስከረም ወር የተካሄደውን የቻይና-አፍሪቃ ትብብር ጉባዔ ዘለዉ  በምትኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውን ቤጂንግ ከላኩ በኋላ፤ ብዙም ሳይቆይ መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረገዉ የአፍሪቃ ኮርፖሬት ካውንስል የ 2025 የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባዔን ሉዋንዳ ላይ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

"ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአሜሪካ እና በአንጎላ መካከል ያለው ወታደራዊ ትብብርም ጨምሯል" የሚሉት የአንጎላ የፖለቲካ ጉዳይ ምሁር ፓውሎ ኢንግልስ በጀርመን ሙኒክ ወታደራዊ ዩኒቨርሲቲ እና በባይሮይት ዩኒቨርሲቲ ምርምር እያደረጉ ነው። ፓውሎ ኢንግልስ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት አሜሪካ በሰሜን አንጎላ የጦር ሰፈር ለመመስረት ሃሳብ አላት።

አንጎላ፤ የሶዮ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ
አንጎላ፤ የሶዮ የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካምስል Borralho Ndomba/DW

የቢደን ጉብኝት ለአንጎላውያን ምን ማለት ነው?

"የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የአንጎላ ጉብኝት ታሪካዊ ክስተት መሆኑ አያጠያይቅም፣ ግን ጉብኝቱ የአንጎላን አሁናዊ ሁኔታ ወዲያውኑ ወደ መልካም አይለውጥም" ሲሉ የአንጎላ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ኪንኪናሞ ቱአሳምባ ለDW ተናግረዋል። እንደ ምሁሩ አስተያየት ዋናዎቹ የቻይና ፕሮጀክቶች ከአሜሪካ ኢንቨስትመንቶች ተጠቃሚ የሚሆኑ ጥቂት የአንጎላ ልሂቃን አባላት ብቻ ናቸው።

እንደ ኪንኪናሞ ቱአሳምባ  "በአብዛኛው የህዝብ ቁጥር ወጣቶች በሆኑባት የአንጎላ ከባድ የስራ አጥነት ይታያል። በዩናይትድ ስቴትስ ቃል የተገባላቸው ትላልቅ ኢንቨስትመንቶች ሁኔታዉን በቶሎ አይለውጡም"።

አዜብ ታደሰ / አንቶንዮ ካስያስ

ፀሐይ ጫኔ