1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንድነት እና የአጋርነትን ማሳያ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2011

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በጋራ የኢድ ሶላት የሚሰገድበት የአዲስ አበባ ስታዲየምን በትናንትናው ዕለት አጽድተዋል። ለዚሁ በዓል ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ተማሪዎችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ወጣቶች ተሳትፈውበታል።

https://p.dw.com/p/3Jpv3
Äthiopien Eid al-Fitr Afräumen nach Gebeten
ምስል Yehunegn Mohammed

በብሄርም በሀይማኖትም መቻቻል እንዳለ የሚያስመሰክር

የታላቁ ወር ረመዳን ጾም ተገባዷል። መላው ሙስሊሙ ማህበረሰብ 1440ኛውን የኢድ አልፈጥር በዓል ለማክበር በአዲስ አበባ እና አከባቢ ያሉ በአዲስ አበባ ስታዲየም የኢድ ሰላት ለመስገድ እንደወትሮው ሁሉ ይታደማል። ትናንት ማለዳውን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በጋራ ከአዲስ አበባ ወጣቶች ጋር በዓሉ የሚከናወንበትን የአዲስ አበባ ስታዲዮምና አካባቢውን አጽድተዋል። አቶ ካሳሁን ጥላሁን መከባበርና መቻቻል እንዳለ የሚያሳይ ነው ሲሉ ይገልጻሉ። «ሀይማኖት ብሄር ሳይበግረው ሁሉም ሰው 12 ሰዓት ተገኝቶ ስታዲየምንና ከስታዲየም ውጭ ከሜክሲኮ፣ ፒያሳ አካባቢ እስከ ቸርቸር ጎዳና ድረስ እንዲጸዳ ተደርጓል። ህብረተሰቡ ይሄን መልዕክት ሲነገረው መጥረጊያና አካፋ ይዞ በመውጣት ነው ጥሪውን የተቀበለው። በዋናነት አንድ እንደሆንን በብሄርም በሀይማኖትም መቻቻል እንዳለ የሚያስመሰክር መሆኑን ተገንዝቤአለሁ።» ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በጋራ በመሆን የአምልኮ እና የኢድ ሶላት መስገጃ ስፍራዎችን ሲያፀዱ እንደቆዩ ወጣት ሱራፌል እሸቱ ይናገራል። «በየመስጊዱ ከአንድ ሳምንት በፊት ነው የማጽዳት ስራ የጀመርነው። በአካባቢያችን የሚገኙ መስጊዶች ነበሩ ስናጸዳ የነበረው። ዛሬ ለየት የሚያደርገው አጠቃላይ እንደአዲስ አበባ ሁሉም አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች በቦታው ላይ ተገኝተዋል። ደስ የሚል መንፈስ ነበረው።» ከዚህ ቀደምም የበዓላት ወቅትን አስታከው ሃይማኖታዊ ክንዋኔ የሚደረጉባቸውን እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ሲያከናውኑ እንደነበር አቶ ቢሆነኝ መሀመድ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ጽ/ቤት ሃላፊ ይገልጻሉ። የክርስትና እምነት ተከታዮች የኢድ በዓል የሚከበርበትን አካባቢን በማጽዳት አጋርነታቸውንና አንድነታቸውንም አሳይተዋል። «ይሄን የጽዳት ስራ ለዚህ ለኢድ በዓል ብቻ የጀመርነው አይደለም። ከዚህ ቀደምም በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረውን የከተራ በዓልን ምክንያት በማድረግ ጃልሜዳን የማጽዳት ስራ ተከናውኗል። አንድነትን አብሮነትን፤ እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የሚገለጽበት ነው።» ያለፉት ዓመታት ለሙስሊሙ ማህበረሰብ የሰቀቀን ኢድ ሆኖ እንደሚታወስ ኡስታዝ አህመዲን ጀበል ይገልጻሉ። እምነቱ የሚፈቅዳቸውን አጋርነት ማሳየት አስፈላጊም እንደሆነም ያምናሉ። «ምናልባት ላለፉት ዓመታት ኢድ ለሙስሊሙ ማህበረሰብ በተለየ መልኩ ድምጹን ለማሰማት ተቃውሞ የመግለጫ፤ የነበረውን አፋኝ ስርዓት በቀጥታ ጥያቄን እንዲመልስ፤ እኔን ጨምሮ ታስረን የነበርነው በርካቶችን እንዲፈታ ጫና ማድረጊያ እና ድምጽን የማሰሚያ መድረክ ሆኖ ነበር። ሰዎች እምነታችንን ልዩነት ሊያራርቁን የበለጠ ክፍፍል ሊፈጥሩ የሚፈልጉ አካላት ጥሩ ምላሽ እና ሊያሰፉ የሚፈልጉትን ቀዳዳ የሚዘጋ መልካም ጅምር ነው እላለሁ።» የሃይማኖቶች የአብሮ የመኖር ባህልን ለማጠናከር እንደሚያግዝ፤ አንድነትና ትስስሩን የበለጠ እንደሚያስተሳስረው የብዙዎች እምነት ነው።

Äthiopien Eid al-Fitr Afräumen nach Gebeten
ምስል Yehunegn Mohammed

ነጃት ኢብራሂም 
አዜብ ታደሰ