1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢዉ የሰዎች እገታ በኢትዮጵያ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ነሐሴ 12 2015

በቡድን የተደራጁ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በጠራራ ፀሐይ ሳይቀር በርካታ ዘረፋዎች እየፈፀሙ እንደሆነ ዶይቸ ቬለ በተደጋጋሚ ጥቆማዎች እየደረሱት ይገኛል። አብዛኛው ጊዜም በድርጊቱ ተሳትፈው የሚገኙት ወጣቶች እንደሆኑ ይታመናል።

https://p.dw.com/p/4VJNH
የኢትዮጵያ ብር
የኢትዮጵያ ብርምስል Eshete Bekele/DW

አሳሳቢዉ የሰዎች እገታ በኢትዮጵያ

አንድ ስማቸውን እንድንገልፅ ያልፈለጉ እና በአሁኑ ሰዓት ጓደኛቸው ሱሉልታ አካባቢ ታግቶ እንደሚገኝ የነገሩን  የአዲስ አበባ ነዋሪ አጋቾቹ በሚሊዮኞች የሚቆጠር ገንዘብ ጠይቀዋል፣ ቤተሰብ እስከ ዛሬ አርብ ድረስም ገንዘቡን ካልከፈለ ጓደኛቸውን እንደሚገድሏቸው አጋቾቹ አስፈራርተዋቸዋል። « ጓደኛዬን ከመውሰዳቸው በፊትም በተደጋጋሚ ወደ ከተማ ይገባሉ ይወጣሉ። በዛ ያለ ሰው ለመውሰድ ሲፈልጉ በአይሱዙ ነው የሚመጡት» አጋጆቹ ለመክፈያ የሚያስቀምጡት ቀነ ገደብ አጭር በመሆኑ ገንዘቡ ለሌለው ሰው ብቻ ሳይሆን ላለውም ሰው ለመክፈል ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እኝሁ ሰው ያብራራሉ።  « ከ 50 ሺ ብር በላይ በቀን ከባንክ ማውጣት አይቻልም እና ብር ያለው ሰው ሁሉ እንዴት ብሎ ነው እስከ ሚሊዮን ብር ከባንክ የሚያወጣው። ስለዚህ አራጣ ተበድሮ ወይም በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማግኘት ይሞክራል።» በማለት ስጋታቸውን ይናገራሉ። 

ሌላው ስሙን እንዳንገልፅ የጠየቀን ወጣትም ቤተሰቡን ስለገጠመው አሳዛኝ እገታ ገልፆልናል። ታጋች ሱሉልታ ይኖር የነበረ የአጎቱ ልጅ ሲሆን አጋቾቹ እንደውም መጀመሪያ ላይ ቤተሰቡ  አራት ሚሊዮን ብር እንዲከፍል ጠይቀዋል። ኃላም በድርድር በሁለት ሚሊዮን ብር ተስማምተዋል። የሆነውን እንዲህ ሲል ገልፆልናል። « የእህቴን ሰርግ ሊታደም ወደ ደራ ሄዶ ከወር በኋላ ሲመለስ አለም ከተማ አካባቢ ያዙት። ሁለት ሚሊዮኑን ብር ከማህበረሰቡ አሰባስበን ልንልክ ስንል በአማራ ክልል በነበረው ችግር መንገድ ተዘጋጋ። ብሩን በሰው ጉልበት ነበር አምጡ የተባልነው።»

ኋላም መንገድ መዘጋቱን የተረዱት አጋቾች ገንዘቡን በአራት የተለያዩ አካውንቶች ገቢ እንዲሆንላቸው ይጠይቃሉ። ቤተሰብ ገንዘቡን ገቢ ማድረጉን የገለፀልን ወጣት አጋቾቹ የአጎቱን ልጅ እንደሚለቁት ቢናገሩም የአጎቱ ልጅ ግን ሳይመለስ ቀርቋል። ከሁለት ሳምንታት በኋላ እርማችሁን አውጡ የሚል መርዶ ይደርሳቸዋል ፣ ግንቦት ወር ላይም አስክሬኑ መገኘቱ ተነገረን ብሎናል። «  እናት አራት ልጆችን ይዛ ለማሳደግ በጣም ይከብዳታል»

«ልጄን በገንዘብ ገዛሁት» የቀድሞ ታጋች አባት

አብዛኛውን ጊዜ የታጋች ቤተሰቦች እንደዚህ አይነት እገታ ወዲያውኑ ለፖሊስ የማያመለክቱት ከአጋቾች ማስፈራሪያ ስለሚደርሳቸው ነው። ይህም ቤተሰብ በዚህ ምክንያት ወደ ህግ የሄደው ዘግይቶ መሆኑን ነው የሟች ቤተሰብ የነገረን። « በአካውንቱ ገንዘቡ ከገባ እና ልጁን ካስቀሩት በኋላ ነው ወደ ህግ የሄድነው። በርግጥም በአካውንቱ የገባላቸው ሁለት ወይም ሶስት ሰዎች ተይዘው ነበር።» በመጨረሻ ግን እንደተለቀቁ ሰማን ይላል።
በኦሮሚያ ክልል ሞጆ ከተማ ነዋሪ የሆነ  እና እንዲሁ ለደህንነቱ ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው ወጣት እንደገለጸልን መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ከሁለት ወራት በፊት አባቱን አግተው ነበር።
« በመኖሪያ ቤት ማታ ቲቪ እያየን በር አንኳኩ እና ክፈቱ አሉ። መሳሪያ ደቅነው ነበር። ከዛ አባቴን ወሰዱት። ከሶስት ቀን በኋላ ገንዘብ አምጡ አሉን። » ይላል። አባቱን ለማስለቀቅ 200 ሺ ብር ተጠይቀዋል።  የሞጆ ከተማውን ወጣት ቤተሰብ የገጠመው እገታ በዚህ አላበቃም። ከአንድ ወር በፊትም አማቼን አግተውት ነበር ይላል። « እሱ ደግሞ የጭነት መኪና ነበረው። መኪናውም እሱም ተያዙ። በመጨረሻ ብር ከፍሎ በተመሳሳይ መንገድ ተለቀቀ።» እሱም 150 ሺህ ብር ከፍሏል። ይሁንና አሁንም ገንዘብ አምጣ እያሉ እያስፈራሩት ነው ይላል።የሞጆው ነዋሪ ለፖሊስ ማመልከትን እንደ አማራጭ አያየውም።« ሁሉም አንዳይነት ናቸው። ምንም ማድረግ አንችልም። እዛ ስትሄጂ ይስቁብሻል። » አብዛኛውን ጊዜ በቡድን ተደራጅተው የሚዘርፉ ሰዎች እንደ ባንክ እና ፖሊስ ጣቢያ የመሳሰሉ መስሪያ ቤቶች የሚሰሩ ተባባሪዎች እንዳሏቸው ተጎጂዎች ይጠረጥራሉ። አንደኛው የሌላኛውን ብሔር ወይም ታጣቂ ቡድንም የሚወነጅሉ አሉ። ጓደኛቸው ታግተው የሚገኙት የአዲስ አበባ ነዋሪ ግን አጋቾቹ ወይም ተባባሪዎቻቸው ብሔረሰብ አይመርጡም ባይ ናቸው።

ሱሉልታ
ሱሉልታምስል Seyoum Getu/DW


በተደራጀ ሁኔታ የሚፈፀሙ ወንጀሎች  በአንዳንድ የአፍሪቃ ሀገራትም ትልቅ ፈተና እየሆኑ መጥተዋል

ካሜሮን ለምሳሌ እነዚህን ዘራፊዎች የበለጠ ወታደሮችን በማሰማራት ለማስቆም እየሰራች ትገኛለች። ከዚህ ቀደም  ናይሮቢ ኬንያ ውስጥ የሌብነት ወንጀል ትፈፅም የነበረችው አይሻ ኢብራሂም  ለ ዶይቸ ቬለ 77ከመቶው ዝግጅት እንደገለፀችው  « ገና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳለች ጀምሮ ትሰርቅ ነበር» 
«አስታውሳለሁ፣ ከልጅነቴ እድሜዬ አንስቶ በችግር እና ረሃብ የተነሳ ብዙ ሱቆችን እንዘርፍ ነበር።  ይህ ወደ ልማድ ተቆይሮ  የሰዎችን ሞባይል ከኪስ መስረቅ ጀመርን። ስልኮች ሸጠን ጥሩ ገንዘብ ማግኘት ጀመርን።  አንዲት ሴት ጥሩ ልብስ ለብሳ ሳይ እኔም እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ… ስለዚህ ከስርቆት የማገኘው ገቢ ተመሳሳይ ልብሶችን እንድገዛ ይረዳኛል። ገባህ እኔ ከደሀ ቤተሰብ የተገኘሁ ነኝ።.»
አይሻ ከዚህ የወንጀል ስራ እንዴት ልትወጣ እንደቻለችም ለዶይቸ ቬለ አስረድታለች።« ወንጀል ከመፈጸም የተቆጠብኩት የደቦ ፍርድ ከደረሰብኝ በኋላ ነው። አንድ ጊዜ ከተባባሪዎቼ ጋር በማናውቀው ስፍራ ለመዝረፍ ሄደን ተያዝን እና በጣም ከባድ የሆነ ድብደባ ገጠመን፤  ሊገድሉን ነበር። የተረፍነው ይህን ባዩ ሁለት ሴቶች ምክንያት ነው። ከዚያም የአካባቢያችን ሰዎች መጥተው ህዝቡ እንዲምረን ረዱን።» 
አይሻ ዛሬ ሌብነቷን ብቻ ሳይሆን ያቆመችው ሌሎች ወጣቶች ወደ ሌብነት እና ዘረፋ እንዳይገቡ አንድ ተቋም አቋቁማ ትመክራለች።  ኬንያዊው የወንጀል ጉዳይ ባለሙያ ብይሮን አዴሮ ሰዎች አፍሪቃ ውስጥ ወደ ወንጀል እንዲገቡ የሚገፋፋቸው የመልካም አስተዳደር እጦት ነው ይላሉ።« ጉዳይ ለማስፈፀም ወደ ቀበሌህ ወይም ወረዳህ ሄደህ ጉዳይህን የሚፈፅመው ባለስልጣን ጉቦ የሚቀበል ከሆነ ያ ጉቦ ተቀባዩ ግለሰብ የተሰጠው ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ ዋጋ አጥቷል ማለት ነው።  ስለዚህ በርካታ ሰዎች ወደ ወንጀል ሲገቡ ይታያል። ምክንያቱም ቀላሉ መንገድ ስለሆነ።  ቀላል መንገድ የሆነው ደግሞ በእኛው በመንግሥታችን መዋቅር አማካኝነት ነው። ዜጎች ሁሉም ነገር ተፈፅሞ ከሚያልፍበት ከእንዲህ አይነቱ የበሰበሰ ስርዓት የሚማሩት ወንጀልን ነው። እነዚህ በሙስና የተዘፈቁ ሰዎች ወይም ባለስልጣናት ለአጭር ጊዜም ቢሆን ፍርድ ቤት ከቀረቡ የህግ ስርዓቱም የራሱን ኃላፊነት የማይወጣ ከሆነ አጠቃላይ ህዝቡ ሊገነዘብ የሚችለው ለማግኘት የሚጓጓውን ጥቅም ለማግኘት ወንጀል መፈፀም ቀላሉ መንገድ ነው የሚል አስተሳሰብ ያሰርፃል። ይህም የሚሆነው ፍላጎትን ለማሳካት ፍትሀዊው መንገድ ዝግ ስለሆነ ነው።» ይላሉ። ኬንያዊው የወንጀል ጉዳይ ባለሙያ። 

ልደት አበበ

አዜብ ታደሰ