አራት የአፍጋኒስታን እስረኞች ከጓንታናሞ ነፃ ተለቀቁ
እሑድ፣ ታኅሣሥ 12 2007ማስታወቂያ
እስረኞቹ በጎርጎረሳዊዉ 2002 እና በ 2003 ዓ,ም በሀገራቸዉ ዉስጥ በአሸባሪነት ተጠርጥረዉ ነዉ ለጓንታናሞ እስር ቤት የበቁት። ቀደም ሲል ስድስት የጓንታናሞ እስረኞች ተለቀዉ ለኡራጓይ መሰጠታቸዉ ይታወቃል። ዛሬ መለቀቃቸዉ ከተሰማዉ አራት የጓንታናሞ እስረኞች ሌላ በጓንታናሞ 132 እስረኞች እንደሚገኙ የአሜሪካዉ የመከላከያ ሚኒስቴር ፔንታገን አስታዉቋል።
በጎርጎረሳዊዉ መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ, ም ዩኤስ አሜሪካ ዉስጥ ከባድ የአሸባሪዎች ጥቃት ከደረሰ በኋላ ከተለያዩ የዓለም አገራት በአሸባሪነት የተጠረጠሩ 779 ሰዎች ጓንታናሞ በሚኘዉ የአሜሪካ የባህር ኃይል ጦር ሰፈር ለእስር በቅተዋል። ከነዚህ እስረኞች መካከል አብዛኞቹ እስካሁን ክስም ሆነ ብይን አልተላለፈባቸዉም። ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ 2009 ዓ,ም የፕሬዚዳንትነትን ስልጣን እንደያዙ ኪዩባ ጓንታናሞ የሚገኘዉን እስር ቤት እዘጋለሁ ሲሉ ቃል ገብተዉ ነበር። ነገር ግን ኦባማ ይህን ቃላቸዉን እስካሁን ባለመጠበቃቸዉ ከአሜሪካዉ ምክር ቤት፤ ከፍትህ ጉዳይ ቢሮና ከብዙኃን መገናኛ ትልቅ ነቀፊታ ደርሶባቸዋል።
አዜብ ታደሰ
ልደት አበበ