አሜሪካ የአርባ ምንጭ ሰው አልባ አውሮፕላን ተልዕኮን ዘጋች
እሑድ፣ ታኅሣሥ 24 2008ማስታወቂያ
ኢትዮጵያ የሚገኘው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ቃል-አቀባይ ዴቪድ ኬኔዲ የአርባ ምንጩ ሰው አልባ አውሮፕላን ማዕከል ከአሁን በኋላ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ በኢሜል መልእክት መግለፃቸቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። «የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ ሠራተኞች ከእንግዲህ በአርባ ምንጭ የሉም» ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የሶማሊያው ጽንፈኛ ታጣቂ ቡድን አልሸባብ ላይ ቅኝት እና ጥቃት ለመሰንዘር ትጠቀምበታለች የተባለው የአርባ ምንጭ ማዕከል ስለመኖሩ በይፋ አረጋግጣ አታውቅም። ኢትዮጵያ የአልሸባብ ታጣቂ ቡድንን ለመዋጋት ወታደሮቿን ወደ ሶማሊያ ማዝመቷ አይዘነጋም። ምንም እንኳን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ኢትዮጵያን በሰብአዊ መብቶች ጥሰት በተደጋጋሚ ሲወቅሱ ቢሰማም፤ ኢትዮጵያ ዩናይትድ ስቴትስ በምሥራቅ አፍሪቃ በምታካሂደው ፀረ-ሽብር ዘመቻ ዋነኛ ተባባሪ ናት።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ