አሜሪካ ኤምባሲዋን በኢየሩሳሌም ከፈተች
ሰኞ፣ ግንቦት 6 2010አሜሪካ አዲሱን ኤምባሲዋን ዛሬ በኢየሩሳሌም በተካሄደ ይፋዊ ስነ ስርዓት ከፍታለች፡፡ በስነ ስርዓቱ ላይ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያምን ኔታንያሁን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናት እና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።
ከወራት በፊት ኢየሩሳሌም የእስራኤል ዋና ከተማ መሆኗን ያጸደቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሀገራቸው ኤምባሲ ከነበረበት ቴልአቪቭ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲዛወር ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ የቀድሞ የአሜሪካ መሪዎች በፍልስጤም እና እስራኤል መካከል የሰላም ስምምነት እስኪደረግ በሚል የኤምባሲ ማዛወሩን ሲያዘገዩት ቆይተዋል፡፡ የሰላም ስምምነቱ ምዕራብ ኢየሩሳሌምን ለእስራኤል፣ ምስራቅ እየሩሳሌምን ደግሞ ወደፊት ለሚመሰረተው የፍልስጤም አገር ዋና ከተማነት በማከፋፈል ረዥም ዓመታት የዘለቀውን ደም አፋሳሽ ግጭት ለማስቆም ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡
አሜሪካ ለግጭት መንስኤ ሆኖ የቆየው አወዛጋቢው የኢየሩሳሌም ጉዳይ በስምምነት እንዲፈታ የአደራዳሪነት ሚና ይዛ የቆየች ቢሆንም የፕሬዝዳንት ትራምፕ አቋም እና እርምጃ ገለልተኝነቷን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ የአሜሪካንን እርምጃ ተከትሎ ዛሬም ጭምር በተካሄደ ተቃውሞ በርካታ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል፤ ጉዳትም ደርሶባቸዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ለተቃውሞ በወጡ ፍልስጤማውያን ላይ እስራኤል በወሰደችው የኃይል እርምጃ በትንሹ 52 ሰዎች ሲገደሉ ከ2000 በላይ ቆስለዋል፡፡ የእስራኤል የኃይል እርምጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ከበርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እና ሀገራት ውግዘት ደርሶበታል፡፡
አሜሪካ ኤምባሲዋን በኢየሩሳሌሙ ስለመክፈቷ በስፍራው ከሚገኘው ወኪላችን ዜናነህ መኮንንን ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ።
ዜናነህ መኮንን
ተስፋለም ወልደየስ
ነጋሽ መሐመድ