ኔታንያሁ በአዲስ አበባ
ሐሙስ፣ ሰኔ 30 2008
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስት ቤንያሚን ኔታንያሁ 70 የሚሆኑ የንግድ ማኅበረሰብ አባላትን በመምራት ወደ ኢትዮጵያ የሄዱ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዉያን በእስራኤል፤ እስራኤላዉያንም በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ እንዲያፈሱ ጥሪ አቅርበዋል። እስራኤል ከበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ጋር እጅግ በጠነከረ መልኩ እየሠራች እንደምትገኝ ያመላከቱት የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አጋር የሆነችዉ እስራኤልን እንዲህ አይነቱን ቦታ ለመከልከል ምንም ምክንያት እንደማይኖር መናገራቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዘግቦአል። በአፍሪቃ ኅብረት ዉስጥ አባል ያልሆኑ ሃገራት ተመሳሳይ ቦታ እንደሚሰጣቸዉ ዘገባዉ አክሎ አመልክቶአል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ናይሮቢን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እዝያ በነበሩበት ወቅት የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸዉ እንደነበር ለማጣራት ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸዉ ጥያቄ የሚያዉቁት ነገር እንደሌለ መናገራቸዉንም አሶሽየትድ ፕሬስ ከአዲስ አበባ ዘግቦአል። ሚኒስትሩ በሃገር ዉስጥም ሆነ ከሃገር ዉጭ በፀጥታ ሃይላት ከፍተኛ ጥበቃ ሥር እንደሚንቀሳቀሱ ዘገባዉ አመልክቷል። ሚኒስትሩ በሃገር ዉስጥም ሆነ ከሃገር ዉጭ በፀጥታ ሃይላት ከፍተኛ ጥበቃ ስር እንደሚንቀሳቀሱ ይታወቃል። የአዲስ አበባዉ ዘጋቢያችን ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል።
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ