1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሞዴል ናርዶስ አበበ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 26 2015

ከቤት በማይወጣበት በኮቪድ ወቅት በጀመረችው በቲክቶክ ፣ ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ ቲክቶከሮች ጋር ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ህክምናዎች ያስፈልጓቸው ለነበሩ ሰዎች ብዙ እገዛዎች አድርጋለች። ከመካከላቸው በከባድ የጤና ችግር ምክንያት እስካሁንም ህክምና የሚደረግላትና እርስዋም ከድርጅቱ ጋር የምትደግፋት ህጻን ትገኝበታለች ።

https://p.dw.com/p/4Uekp
Nardos Abebe
ምስል Privat

ናርዶስ አበበ፤ሞዴል ቲክቶከርና በጎ አድራጊ

በሀገርዋ በሞዴልነት እውቅና ለማትረፍ በቅታለች። ከዚሁ ጎን ለጎን በቲክቶክ እርዳታ ለሚሹ ፣ከሌሎች ቲክቶከሮች ጋር ገንዘብ በማሰባሰብ ትረዳለች። በአምባሳደርነት ለምታገለግለው የበጎ አድራጎት ድርጅትም የበኩልዋን አስተዋጽኦ እያደረገች ነው። ማናት ለምትሉ መልሱን ከዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ታገኙታላችሁ።ኂሩት መለሰ አዘጋጅታዋለች።
ሞዴል ቲክቶከርና በጎ አድራጊ ናት። ቲክቶክን ለበጎ ተግባር ከሚጠቀሙ ታዋቂ ሰዎች አንዷናት። በህክምና እጦት የሚሰቃዩ ፣ ለተለያዩ ከባድ የጤና ችግሮች የተዳረጉና የተፈናቀሉ ወገኖችን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ከሌሎች ቲክቶከሮች ጋር ሆና ለተከታዮቻቸውና ለሚያውቋቸው መረጃውን  በማስተላለፍ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ትታወቃለች ፤ ሞዴል ናርዶስ አበበ። ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ የጾታ ጥቃት ሰለባ ሴቶችን ፣አካል ጉዳተኞችንና ከሀገራቸው ተሰደው ለስቃይ የተዳረጉ ሴቶችን ለሚያቋቁመውና በሌሎችም የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ለተሰማራው «ስንቅ በጎ አድራጎት ድርጅት አምባሳደር ናት።

Hayat Mohammed
ናርዶስ አበበና ሀያት መሐመድ በአምስተርዳሙ ዝግጅት ላይ ከስንቅ በጎ አድራጎት ድርጅት ተባባሪዎች ጋር ምስል Hayat Mohammed

 በአምባሳደርነት ከምታገለግለው ከስንቅ ጋር የተዋወቀችበትን አጋጣሚ ያስታወሰችው ናርዶስ ከዛሬ 9 ዓመት አንስቶ ኑሮዋ ሮም ጣልያን ቢሆንም በባለቤትዋ ስራ ምክንያት በተለያዩ ሀገራት ትዘዋወራለች። በአሁኑ ጊዜም ኡጋንዳ ነው የምትኖረው። ባለፈው ሳምንት አምስተርዳም በተካሄደው በአውሮጳ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ላይ «ስንቅ በጎ አድራጎት ድርጅት» በደብረ ብርሃን ለተጠለሉ ሴት ተፈናቃዮች የንጽህና መጠበቂያ ለማሰባሰብ ባካሄደው ዝግጅት ላይ የሦስት ወር ህጻን ልጅዋን ይዛ መጥታ ተሳትፋለች። የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ ሃያት መሐመድ አሊ ለዶቼቬለ እንደተናገረችው፣የድርጅቱን አምባሳደር ናርዶስ አበበን ጨምሮ ሌሎች በጎ ፈቃደኞች በአምስተርዳም ለዚህ ዓላማ በተለያዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች ላይ ተሰማርተው ነበር።

Model Nardos Abebe
ሞዴል ናርዶስ አበበና ባለቤቷምስል Privat

ከተቋቋመ ሦስት ዓመት የተጠጋው ስንቅ በጎ አድራጎት ድርጅት በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ መቅደላ ማሻ ነው የሚገኘው። ሃያት ድርጅቱን የመሰረተችው «ጾታዊ ጥቃትና ስደት በኔ ይብቃ »የሚለውን መርህ ይዞ ነው። ሞዴል ናርዶስ እንደምትለው ከስንቅ በጎ አድራጎት ድርጅት ጋር መስራት ከመጀመሯ በፊትም በቲክቶክ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ትሳተፍ ነበር። ከቤት በማይወጣበት በኮቪድ ወቅት በጀመረችው በቲክቶክ ፣ ከሌሎች በጎ ፈቃደኛ ቲክቶከሮች ጋር ብዙ ገንዘብ የሚጠይቁ ህክምናዎች ያስፈልጓቸው ለነበሩ ሰዎች ያደረጓቸውን እገዛዎች ታስታውሳለች። ከመካከላቸው በከባድ የጤና ችግር ምክንያት እስካሁንም ህክምና የሚደረግላትና እርስዋም ከድርጅቱ ጋር የምትደግፋት ህጻን ትገኝበታለች ።

ሞዴል ናርዶስ በቦረናው ድርቅ ወቅትም ናርዶስና በአካል እንኳን የማታውቃቸው ቲክቶከሮች ገንዘብ በማሰባሰብ እርዳታ ልከዋል። ናርዶስ ለበጎ አድራጎት ስራ በምትጠቀምበት በቲክ ቶክ ከቤተሰቦቿ ጋር በመሆን የሀገርዋን ባህልም ታስተዋውቃለች። በእርዳታ ማሰባሰቡ ስራም ሃይማኖት ዘር ሀገር ሳይለዩ በሚተባበሩት ሰዎች ብዙ አይቻለሁ ትላለች።ከተረጂው ወገን የምትሰማው ደግሞ በእጅጉ የሚያረካት ነው። በቀድሞ አጠራሩ ናዝሬት በአሁኑ አዳማ የተወለደችውና ያደገችው ናርዶስ ሞዴልነት የጀመረችው በዚሁ ከተማ ነው። በአዳማ ለሚስ ቱሪዝም ማዕረግ የበቃችው ናርዶስ በአዲስ አበባው አቢሲኒያ ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት እየተማረች ሳለ በጎርጎሮሳዊው 2010 ፌስ ኦፍ አፍሪካ በሚባል ውድድር የመሳተፍ እድል አገኘች።

Nardos Abebe
ሞዴል ናርዶስ አበበ ከተቀበለችው ሽልማት ጋር ምስል Privat
Nardos Abebe
ናርዶስ አበበ እርዳታ ካበረከተችላቸው ሰዎች ጋር ምስል Privat

በሀገር ውስጥ የማጣሪያውን አልፋ  ኢትዮጵያን ወክላ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪቃ ፣በመጨረሻም ናይጀሪያ ውስጥ ከ53 የአፍሪቃ ሀገራት ከተወከሉ ሞዴሎች ጋር ተወዳድራ ከመጀመሪያዎቹ አምስት ተመራጮች መካከል አንዷ ለመሆን በቃች። ከዚህ ማዕረግ በኋላም የአንድ ናይጀሪያዊ ዘፈን ቪድዮ ክሊፕ ሰርታለች። ይህን ሁሉ ከትምህርትዋ ጎን ለጎን ታካሂድ የነበረችው ናርዶስ በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሶስት ዓመት ሲቪል ምህንድስና ተምራለች። ከዚያም ስራ አግኝታ ሱዳን የሄደችው ናርዶስ ብዙም ሳይትቆይ ትዳር ያዘች። ልጆችም ከወለደች በኋላ የሞዴልነት ስራዋን አቆመች። ከኤርታራዊ ኢጣልያዊ ጋር ትዳር ከመሰረተች በኋላ ነበር ኑሮዋን ሮም ጣሊያን ያደረገችው። ጣልያን ለናርዶስ አዲስ አልነበረችም፤ ከዚያ በፊት በሚላን ጣሊያን የፋሽን ትርዒትም ላይ ተሳትፋ ነበርና። የአራት ልጆች እናት ናርዶስ  ወደ ሞዴሊንግ የመመለስ ሃሳብ አላት።


ኂሩት መለሰ 

ሸዋዬ ለገሠ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ዘገባና ትንታኔ

ዘገባና ትንታኔ

Hayat Mohammed