1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል የጡረተኞች የተቃውሞ ሰልፍ

ሐሙስ፣ ሰኔ 1 2015

ትግራይ ክልል ላለፉት 23 ወራት ወርሐዊ የጡረታ አበላችን አልተከፈለንም ያሉ ጡረተኞች ትናንት በመቐለ ጎዳናዎች ሰልፍ አድርገዋል ። ሰልፈኞቹ በተደጋጋሚ ለትግራይ ክልል አስተዳደር እና ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አጥተናል አስከፊ ሕይወት እየመራንም ነው ብለዋል ።

https://p.dw.com/p/4SLUO
Äthiopien | Proteste von Rentnern in Tigray
ምስል Million Hailesilassie/DW

አስከፊ ሕይወት እየመራንም ነው ብለዋል

ትግራይ ክልል ላለፉት 23 ወራት ወርሐዊ የጡረታ አበላችን አልተከፈለንም ያሉ ጡረተኞች ትናንት በመቐለ ጎዳናዎች ሰልፍ አድርገዋል ። ሰልፈኞቹ በተደጋጋሚ ለትግራይ ክልል አስተዳደር እና ለኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ አጥተናል አስከፊ ሕይወት እየመራንም ነው ብለዋል ።

በትግራይ ክልል ካሉ ከፍተኛ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር ላይ ከሚገኙ የማሕበረሰብ ክፍሎች መካከል፥ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ አገልግሎቶች የነበሩና በኃላም በጡረታ ከስራቸው የተሰናበቱ፥ በአብዛኛው በዕድሜ የገፉ ዜጎች ይገኙበታል። እነዚህ በትግራይ ክልል የሚገኙ በቁጥር 100 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ የሚገመቱ ጡረተኞች፥ ላለፉት 23 ወራት የሚያገኙት የነበረ የጡረታ አበል ተቋርጦባቸው የከፋ ችግር ላይ መሆናቸው ይገልፃሉ። አቶ ተስፋይ መኮንን ከ40 ዓመት በላይ ለሚሆን ግዜ በመንግስት ሥራ ላይ የነበሩ እና በኋላም በጡረታ የተሰናበቱ ናቸው። የቀድሞ የመንግስት ሠራተኛ የአሁኑ ጡረተኛ አቶ ተስፋይ ላለፉት 23 ወራት የሚገባቸውን የጡረታ አበል ባለማግኘታቸው ከነቤተሰቦቻቸው አደጋ ላይ መሆናቸው ይገልፃሉ። 

የሚመለከተው የመንግሥት አካል «አፋጣኝ መፍትኄ» እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል
የሚመለከተው የመንግሥት አካል «አፋጣኝ መፍትኄ» እንዲሰጣቸው ጠይቀዋልምስል Million Hailesilassie/DW

እንደ ጡረተኛው አቶ ተስፋይ የመሰሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ጡረተኞች፥ «ፍትህ ለጡረተኞች፣ የታገደ የጡረታ ክፍያችን ይለቀቅ፣ የኢትዮጵያ መንግስት የጡረተኞች መብት ያክብር፣ የጡረታ ክፍያችን በአስቸኳይ ይከፈለን» የሚሉና ሌሎች መፈክሮች በመያዝ ትላንት በመቐለ ጎዳናዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል። በሰልፉ አግኝተን ካነጋገርናቸው መካከል የሆኑት ለ38 ዓመታት በአስተማሪነት ካገለገሉ በኃላ በጡረታ የተሰናበቱት ወይዘሮ ታገኝ አዳል፥ በትግራይ ክልል ያሉ ጡረተኞች ለረዥም ግዜ ክፍያ ባለማግኘታቸው «የሚላስ የሚቀመስ አጥተዋል» ይላሉ። 

ሌላው ጡረተኛ መምህር ሙሉጌታ ወልደስላሴ በበኩላቸው «ጡረተኛ ለአገልግሎቱ ተጨማሪ ውለታ እንጂ የክፍያ እግድ አይገባውም» በማለት የሚገልፁ ሲሆን ይህ በአፋጣኝ ሊታረም፣ አለምአቀፍ ሕጎች ሊከበሩ ይገባል ይላሉ። 

«ፍትሕ ለጡረተኞች» የሚልና ሌሎች መፈክሮችንም አስተጋብተዋል
«ፍትሕ ለጡረተኞች» የሚልና ሌሎች መፈክሮችንም አስተጋብተዋልምስል Million Hailesilassie/DW

ጡረተኞቹ ጥያቄያቸውን በተደጋጋሚ ለክልሉ አስተዳደር እና የፌደራሉ መንግስት ቢያቀርቡም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውን ገልፀዋል። ትናንት በነበረው የጡረተኞች የተቃውሞ ሰልፍ በመገኘት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጡ በጡረተኞች የተጠየቁት በፌደራል የሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የሰሜን ሪጅን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክንፈ አዳነ፦ በትግራይ ክልል ያሉ ጡረተኞች ቅሬታ ለሚመለከተው የፌደራል መንግስት ተቋም መቅረቡ እና ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል። ከዚህ ውጭ ግን ዝርዝር ማብራሪያ ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በጡረተኞቹ ጉዳይ የተናገሩት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ አማኑኤል አሰፋ፥ የጡረተኞች ችግር ለመቅረፍ ከፌደራሉ መንግስት ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን፤ አወንታዊ ምላሽም እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

ሚልዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሀመድ