1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ትግራይ ክልል የተቃዋሚዎች እስር

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2015

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ነገ ሊደረግ ከታቀደ ሰልፍ ጋር የተገናኘ በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና ሌሎች ግለሰቦች መታሰራቸው ተገለፀ ። በመቐለ ዛሬም ውጥረት ነግሷል።

https://p.dw.com/p/4W1gk
 መቐለ ከተማ፤ ኢትዮጵያ
በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ነገ ሊደረግ ከታቀደ ሰልፍ ጋር የተገናኘ በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና ሌሎች ግለሰቦች መታሰራቸው ተገለፀ ። ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

በመቐለ ዛሬም ውጥረት ነግሷል

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ነገ ሊደረግ ከታቀደ ሰልፍ ጋር የተገናኘ በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና ሌሎች ግለሰቦች መታሰራቸው ተገለፀ ። ወደ 20 ግድም ሰዎች መታሰራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ በእስሩ ወቅት ሰዎች የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸውም ተገልጿል ። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለነገ ከጠሩት ሰልፍ ጋር በተያያዘ በመቐለ ዛሬም ውጥረት ነግሷል። ከትናንት ጀምሮ በመቐለ ከተማ ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፖሊስ ኃይል ተሰማርቶ ይገኛል። 

ትናንት በፖሊስ ተይዘው ከታሰሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና አባላት በተጨማሪ ዛሬም ሌሎች ሰዎች በፖሊስ ተይዘዋል ። ዛሬ አመሻሹ ላይ መግለጫ የሰጡት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ መብት ነው፣ ይህን ለማንም አንከለክልም ብለዋል ። ሆኖም ግልፅ የደህንነት ስጋት አለ በማለትም የቀን ለውጥ እንዲደረግ በአስተዳደራቸው በኩል ፍላጎት እንዳለ ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ወደ 20 ግድም ሰዎች መታሰራቸው ተገለጸ።
በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ነገ ሊደረግ ከታቀደ ሰልፍ ጋር የተገናኘ በሚል በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር እና ሌሎች ግለሰቦች መታሰራቸው ተገለፀ ። እስካሁን ወደ 20 ግድም ሰዎች መታሰራቸው ተገለልጿል ።ምስል DW/M. Hailessilasie

አቶ ጌታቸው ታስረው የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተፈትተዋል ብለው በመግለጫቸው ቢናገሩም፥ የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ ኃያሉ ጎደፋይ፣ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር ደጀን መዝገቡ እና የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ኪዳነ አመነ እና ክብሮም በርሃ ለሰዓታት ከተፈቱ በኋላ ድጋሚ ታስረዋል ሲል የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ማምሻውን ለዶቼቬለ ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም ትናንት ከታሰሩት ጋር በአጠቃለይ 20 ገደማ የተቃዋሚ ፖርቲ አመራር፣ አባላት እና ሌሎች ግለሰቦች ከሰልፉ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች ለእስር መዳረጋቸውን የትግራይ ነፃነት ፓርቲ ቃል አቀባይ ገብረሥላሴ ካሕሳይ ተናግረዋል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ