1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከመኖርያ ቤታቸዉ የተባረሩት የፖለቲከኛዉ ባለቤት

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 5 2016

በሽብር ተጠርጥረዉ የታሰሩት የፖለቲከኛ ታዬ ደንደአ ቤተሰብ ሲኖሩበት ከነበረው ቤት ውስጥ እንደወጡ ተናገሩ። የፖለቲከኛው ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ እንዳሉት ሐሙስ ታህሳስ 04 ቀን 2016ዓ.ም ጀምሮ መንግስት የሰጣቸዉ መኖሪያ ቤት እስከነ እቃው ታሽጓል። ወ/ሮ ስንታየሁ ደጅ እንድንወድቅ ነተደርገናል ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4aDve
ታዬ ደንደአ
ታዬ ደንደአምስል Million Haileselasi/DW

የአቶ ታዬ ባለቤት ደጅ እንድንወድቅ ነው የተደረገው ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል

ሰሞኑን መንግስት በሽብር ጠርጥሬ አስሬያቸዋለሁ ያለው የፖለቲከኛ ታዬ ደንደአ ቤተሰብ በሦስት ቀናት ውስጥ ሲኖሩበት ከነበረው ቤት ውስጥ እንዲወጡ ተነግሯቸዉ፤ ከቤቱ እንደወጡ ተናገሩ። የፖለቲከኛው ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ እንዳሉት ሐሙስ ታህሳስ 04 ቀን 2016ዓ.ም  ጀምሮ መንግስት የሰጣቸዉ መኖሪያ ቤት እስከነ እቃው ታሽጓል። ወ/ሮ ስንታየሁ ደጅ እንድንወድቅ ነተደርገናል ሲሉም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡  

በሦስት ቀናት ውስጥ ቤቱን እነድትለቁ የሚል ማስጠንቀቂያ ወዲያ ነበር የተሰጠን

አቶ ታዬ ደንደኣ ከስልጣን የመነሳት ደብዳቤ በተሰጣቸው እለት ሰኞ ምሽት ወደ ቤት ከገቡ በኋላ ለሊት ከ5፡00 እስከ 9፡00 ቤታቸው መበርበሩን ለዶቼ ቬለ የገለጹት የአቶ ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ፤ በዚያው ለሊት በርካታ የጸጥታ አካላት አቶ ታዬን ይዘውአቸው ከሄዱ በማግስቱ ማክሰኞ ጠዋት 3፡00 ቤቱን እንዲለቁ የሶስት ቀናት ገደብ ብቻ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል፡፡ “ተለዋጭ ቤትም እንዲሰጠን ለመጠየቅ እድሉን አልሰጡንም፡፡ ይህ ሰው ይነስም ለዚህ አገር አስተዋጽኦ ያደረገ ነው፡፡ እንደ ዜጋም መጠቀም ለበት ይመስለኛል፡፡ ግን የተሰጠን ሶስት ቀን ብቻ ነው፡፡ በዚያ ውስጥ እቃ የማታወጡ ከሆነ ኪራይ ቤቶች እቃውን ጭኖ መጋዘን ተከራይቶ በዚ ያስቀምጣል ይላል እሮብ 10 ሰኣት የደረሰን ደብዳቤ፡፡ ብዙም መንገዶቹ ክፍት አይደሉም ለኛ አውጥተው ነው ደጅ የጣሉን” ሲሉም አማረዋል፡፡

የመኖሪያ ቤታቸው መታሸግ

በዚህ እያሉም ትናንት ሃሙስ ፖሊሶች በብዛት ወደ ቤታቸው መጥተው ለጊዜው የሚጠቀሙበትን እቃ ይዘው እንዲወጡ ታዘው ሌላው እቃ በዚያው ቤት ውስጥ መታሸጉን አመልክተዋልም፡፡ “ለአሁን ብቻ የምትጠቀሙበትን ይዛችሁ ውጡ ተባልን፡፡ ሌላው እቃ በዚው ታሸገ፡፡ ወደ እኛ የመጡ የኪራይ ቤቶቹ የቅርንጫፍ ሰራተኞች የሚፈቀድ ከሆነ ቅሬታ ማቅረብ ትችያለሽ በተባልኩት መሰረት ወደዚ ብሔድም ቅሬታ ማቅረቢያ ቀን እሮብ ነው አሉኝ፡፡ ከዚን ደግሞ ወዲያውኑ አሁኑኑ እቃውን ጭናችሁ ወደ መጋዘን አስገቡ የሚል ትዕዛዝ መጣ” ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት
አቶ ታዬ የኦሮሚያ ክልላዊ ምክር ቤት አባል ናቸውምስል Seyoum Getu/DW

አሁናዊ የቤተሰብ ሁኔታ

በጸጥታ ችግር ምክኒያት ተፈናቅለው አብሮአቸው የሚኖሩ የአቶ ታዬ ቤተሰቦች እና ሁለት ልጆቻቸውን ጨምሮ ወደ ስምንት የሚሆኑ ቤተሰብ አባላትም መሄጃ የለውም ብለዋል ወ/ሮ ስንታየሁ፡፡ “ህዝቡ ሊያቅልን የሚገባው ያው አንደኛ አይን ውስጥ ነን ያለነው እኛ፡፡ ሁኔታዎች ትንሽ አሳሳቢ ነው፡፡ አውጥተው ነው ውጪ ላይ የጣሉን” ሲሉም አማረው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ወ/ሮ ስንታየሁ ለጊዜው ዘመድ አዝማድ ጋር ተጠልለናልም ነው ያሉት፡፡ የኪራይ ቤቶች ከሰው ወደ ሰው ርክክብ የሚደረግበትና ሲመለስም ሊሰጥ ስለሚገባው ጊዜን በተመለከት ዶቼ ቬለ ለኢትዮጵያ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ረሻድ ከማል ስልክ በመደወል በጽሁፍም መልእክት ብልክላቻም ምላሽ አላገኘም፡፡ ለኮርፖሬሽኑ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አማኑኤል አያለው ደውለን ስለጉዳዩ ስንጠይቃቸው አጣርቼ እደውላለሁ ቢሉም መልሰን ስንደውልላቸው ስልካቸው አይነሳም፡፡

ስለ አቶ ታዬ ደንደአ የየጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ

የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ አቶ ታዬን ከተለያዩ መሳሪያ እና ከተሰጣቸው ኃላፊነት ጋር የማይሄድ ያለው የማይጠበቁ ሰነዶች ከቤታቸው በብርበራ መገኘቱን አስረድቷል፡፡ ወ/ሮ ስንታየሁ ግን፡ “በዚያ ልክ አይደለም እሱ፡፡ በጣም ታማኝ አገለጋይ እንደሆነ በደንብ ያውቁታል፡፡ መሳሪያው ሹመት ላይ እያለ የሰጡት ነው ከየትም የመታ አይደለም፡፡ እኔ በዚህ ላይ ብዙ ባልል እመርጣለሁ፡፡ አስቀድሜም ቪዲዮ የሚቀርጹ ሲገቡ አንድ ሁለት ቡክ አውጥቼ ሁለት ሺህ የተጻፈት ሁለት ሚሊየን እንዳባልበት አደራ ብዬ ፖሊሶቹን ስጠይቅ አይደረግም ብለው አረጋጉኝ፡፡ የሆነው ግን አሳዛኝ ነው” ብለዋል፡፡

Äthiopien Addis Ababa | Minister | Mufrihat Kamil
አቶ ታዬ ደንደአ በቁጥጥር ሥር እስከዋሉበት ጊዜ ድረስ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በመሥሥራት ላይ ነበሩምስል Yohannes Geberegziabher/DW

በበሄተሰቦቹ ዘንድ እርምጃው የተጠበቀ ነው ወይ

ቤተሰቡ የተወሰደውን እርምጃ የጠበቁት ነበር ወይ የተባሉት የአቶ ታዬ ደንደአ ባለቤት ወ/ሮ ስንታየሁ ዓለማየሁ “አስቀድሞ የታዩ ምልክቶች ብያንስ ስልጣኑን እንደሚያሳጣው ብንገምትም በዚህ ደረጃ እንተነኮሳለን አላልንም ነበር” ነው ያሉት፡፡ አቶ ታዬ በተደጋጋሚ ለስራ ጉዳይ ወደ ውጪ እንደሚሄዱ ተነግሮአቸዋል “የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት አልፈቀደም” በሚል የጉዞ  ዓላማዎቹ በተደጋጋሚ መሰረዛቸውን ባለቤታቸው አንስተዋል፡፡

የገዛ መንግስታቸውና የፖለቲካ ድርጅታቸው ላይ የሰላ ትችት በማቅረብ የሚታወቁት አወዛጋቢው ፖለቲከኛ አቶ ታዬ ደንደዓ ሰኞ እለት ከሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኃላፊነታቸው መነሳታቸው በተገለጸ ማግስት፤ ከኃላፊነታቸው በተቃራኒ “የሽብር ቡድኖች ጋር በህቡ አብረዋል” በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውን የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ማክሰኞ ባወጣው ሰፊ አተታ ማሳወቁ አይዘለጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ