ተቃዉሞ በኢትዮጵያ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2008ተቃዋሚዎች የሚያካሂዱት ሰልፍ ሠላማዊ መሆኑን፣ ለሚመለከተዉ አካልም የሰብዓዊም ሆነ የድሞክራሲያዊ መብት ጥያቄያቸዉን ለማቅረብ እንደሚፈልጉ ነው የሚናገሩት። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት ሰልፈኞቹን «ፀረ-ሰላም» ወይም «ፀረ-ልማት ኃይል» እንዲሁም «ሁከት ፈጥሮ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ» የሚሞክሩ ሲል ይወንጅላል።
«ማንኛዉም ዜጋ ጥያቄ ካለዉ ህገመንግስቱ በሚፈቅደዉ አግባብ በሰላማዊ መንገድ ሰልፍ አካሄዶ ለመንግስት ጥያቄዉን ማቅረብ እንደሚችል፣ ግን ጦር መሳርያ ይዞ በመዉጣት፣ ቤት በማቃጠል፣ ፈንጅ በመወርወር ወይም የሰዉ ህወት በማጥፋት አይደልም» ሲሉ በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የህዝብ ግኑኝነት ሐላፍ አቶ መሃመድ ሳይድ ለዶቼ ቬሌ ይናገራሉ። የመንግስት ተችዎች መንግስት ከመግደል እና ከማሰር አደባባይ ለወጣው ህዝብ ጥያቄ መልስ መስጠት የተሳነዉ ለምን ይሆን? ብለዉ የሚጠይቁ አሉ።
ይህ «የአንድ ወቅት ግርግር ነዉ፣ ያልፋል» የሚሉት አቶ መሃመድ መንግስት ከህዝቡ ጋር እየተወያየ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡን ከማህበረሰቡ ጠይቀን ነበር። በአድስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ግን ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት የመንግስትን ዉንጀላና የአቶ መሃመድ መልስን ይተቻሉ።
የወሎ አከባቢ ነዋሪ ነኝ ያሉትም ስማቸዉ እንዲያዝ ጠይቀዉ ህዝብ ስለ ተቃዉሞዉ ግንዛቤ የለዉም ካሉ በዋላ መንግስት ለጥያቄዉ መልስ ለመስጠት ግዜ ያስፈልጋል ይላሉ።
ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የጠየቁት ሌላኛዉ በምስራቅ ሃራርጌ የበዴሳ ነዋሪ የሆኑት የዛሬ ሳምንት አምስት ሰዎች በአከባቢያቸዉ በፀጥታ ሃይል መገደላቸዉን ጠቅሰዉ ጥያቄያችን የተቀበለ አካል የለም ይላሉ።
በፌስቡክ ደረ ገፃችን ላይም ይሄን ጉዳይ በተመለከተ አስተያየት ከሰጡን ዉስጥ ሰላማዊ ሰልፍ መሳርያ ይዞ፣ ንብረት እያቃጠሉና ባንድራ እየረገጡ አይደልም የሚሉ በአንድ ጎራ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ መንግስት አፍ እንጅ ጆሮ የለዉም፣ «መንግስት ህጋዊ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እስካልፈቀደ ህዝቡ ህጋዊ ያልሆነ ሰልፍ እንደሚያደርግ የታወቀ ነው» ሲሉ አስተያየታቸዉን ሰንዝረዋል።
መርጋ ዮናስ
ሕሩት መለሰ