ቦኮሐራም የካሜሩን ከፍተኛ ባለሥልጣን ባለቤትን አገተ
እሑድ፣ ሐምሌ 20 2006ቦኮሐራም የሚንሥትሩን ባለቤት ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን ባገተበት ድርጊቱ በርካታ ሰዎች መገደላቸውም ተነገሯል። ቦኮሐራም የሰነዘረው ጥቃት ዛሬ ማለዳ ላይ የተፈጸመው የካሜሩን ሰሜናዊ ግዛት፣ ኮሎፋታ ከተማ ውስጥ እንደሆነ የካሜሩን የኮሙኒኬሽን ሚንስትር ኢሣ ትቺሮማ ባካሪ ገልፀዋል። የቦኮሐራም ታጣቂዎች የጥቃታቸው ዒላማ አድርገው የተንቀሳቀሱት የምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ አማዱ ዓሊ እና የአካባቢው የጎሳ አለቃ ቤቶች ላይ እንደነበረም ተጠቅሷል። የሟቾቹ እና የታጋቾቹ ሁነኛ ቁጥርን ለማወቅ ጥረት እየተደረገ በመሆኑ ምን ያህል እንደሆነ ማወቅ አይቻልም ሲሉ የመንግሥት ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
ምንም እንኳን ቦኮሐራም ከናይጀሪያ መንግስት ጋር በሚያደርገው ፍልሚያ ማንም ጣልቃ እንዳይገባበት ቢያስጠነቅቅም፤ የአካባቢው ሃገራት ቦኮሐራምን ለመዋጋት በሚያደርጉት የጋራ ጥረት የካሜሩን መንግስት ተሳትፎ እየጨመረ መምጣቱ ይታወቃል። በተያያዘ ዜና ከናይጄሪያ ሰሜናዊ ከተሞች ግዙፍ በሆነችው የካኖ ከተማ አንድ የካቶሊክ ቤተክርስትያን ውስጥ ዛሬ በደረሰ የቦንብ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ፖሊስ አስታወቀ። ጥቃት አድራሹ የናይጀሪያው አሸባሪ ቡድን ቦኮሐራም ስለመሆኑ ግን እስካሁን አልታወቀም። ሆኖም ከአራት ወራት በፊት ማሮው ውስጥ የተያዙ 22 የቦኮሐራም ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስትያ ከ10 እስከ 20 ዓመታት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ ተበይኖባቸው እንደነበር መጠቀሱ ይታወቃል።
ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ