1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በነፈገው ጉባኤ ደብረፅዮን የህወሓት ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ

ሰኞ፣ ነሐሴ 13 2016

በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹና አባላቱ ባልተገኙበት ለአንድ ሳምንት በመቐለ የተካሄደው በምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው14ተኛ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በድርጅቱ ሊቀመንበርነት አቶ አማኑኤል አሰፋን በምክትል ሊቀመንበርነት በመምረጥ ተጠናቋል። ውጤቱ ተቀባይነት እንደማይኖረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጾ ነበር ።

https://p.dw.com/p/4jeLo
የህወሓት ሥራ አስፈጻሚኮሚቴ አባላት
ምርጫ ቦርድ እውቅና በነፈገው ጉባኤ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የህወሓት ሊቀመንበር፤ አቶ አማኑኤል አሰፋ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል። ምስል Million Haileselassie

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና በነፈገው ጉባኤ ደብረፅዮን የህወሓት ሊቀ-መንበር ሆነው ተመረጡ

በርካታ ከፍተኛ አመራሮቹ እና አባላቱ ባልተገኙበት ለአንድ ሳምንት በመቐለ የተካሄደው በምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው 14ተኛ የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን በድርጅቱ ሊቀመንበርነት አቶ አማኑኤል አሰፋን በምክትል ሊቀመንበርነት በመምረጥ ተጠናቋል።

በእነ ዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት ዛሬ ማምሻው ይፋ እንዳደረገው 45 አባላት ያሉት አዲስ የፓርቲው ማእከላይ ኮሚቴ መምረጡ አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ከ45ቶቹ መካከል  9 ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትም መርጧል።

በዚህ መሰረት ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የህወሓት መሪ ሆነው እንዲቀጥሉ በጉባኤው ውሳኔ መተላለፉ የተገለፀ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም የህወሓት ቃልአቀባይ የነበሩት አቶ አማኑኤል አሰፋ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲሰሩ መመረጣቸው ይፋ ተደርጓል።

የህወሓት አመራሮች ክፍፍል እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተፈጠረ ውዝግብ ሥጋት ፈጥሯል

የህወሓት ሊቀ-መንበር እና ምክትል ሊቀ-መንበርን በሚጨምረው እና ዘጠኝ አባላት ባሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውስጥ ሁለት ሴቶች ተካተውበታል። በፓርቲው ውስጥ ረዘም ላሉ ዓመታት በከፍተኛ አመራርነት ያገለገሉት ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚዓብሔር እና የቀድሞዋ የትግራይ ክልል የኮምዩንኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የነፈገው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ፍጻሜ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የነፈገው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ፍጻሜምስል Million Haileselassie

የኢትዮጵያ የገንዘብ እና የኤኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር አብርሃም ተከስተ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ሆነው ያገለገሉት ዶክተር ሰለሞን ኪዳነም የሥራ አስፈጻሚውን ተቀላቅለዋል። አቶ ተኽላይ ገብረመድህን፣ ዶክተር ር ፍስሃ ሃፍተፅዮን እና ዶክተር ረዳኢ በርሀ ቀሪዎቹ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ናቸው።

በጉባኤው መዝግያ የጉባኤተኛው የአቋም መግለጫ የቀረበ ሲሆን፥ ለጉባኤው ይጠበቅ ከነበረው 950 ተሳታፊ መካካል፥ በተደረገ ዓፈና የተወሰኑ አባላት ሳይሳተፉ መቅረታቸውን 783 ማለትም 82 ከመቶ ተሳትፎ ሕጋዊ የተባለ ውሳኔ ማስተላለፉ ተነግሯል።

 አራተኛ ቀኑን የያዘው የሕወሓት ጉባኤ እና የተቃዋሚዎች መግለጫ

ይህ ጉባኤ ሕገወጥ ብለው የገለፁ አቶ ጌታቸው ረዳ ጨምሮ፣ በርካታ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የፓርቲው ቁጥጥር ኮምሽን በጉባኤው ካለመሳተፋቸው በተጨማሪ የጉባኤው ውሳኔ እና ውጤት ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስቀድመው ገልፀው ነበር።

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል እና አቶ አማኑኤል አሰፋ
የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አቶ አማኑኤል አሰፋ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳን እንዲተኩ ተቃውሞ በበረታበት ጉባኤ ተመርጠዋል።ምስል Million Haileslasse/DW

ዛሬ ይፋ በተደረገው የስራ አስፈፃሚ አባላት ዝርዝር ውስጥ በጉባኤው ከተሳተፉት ውስጥ ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚ የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ አለም ገብረዋህድ እና አቶ ጌታቸው አሰፋ ከፓርቲው ስራ አስፈፃሚነት ዝቅ ተደርገዋል።

እነዚህ አመራሮች በማዕከላዊ ኮሚቴ ግን ተካተዋል። የአቶ አማኑኤል አሰፋ በምክትል ሊቀመንበርነት መመረጥ ያልተጠበቀ ተደርጎ ተወስዷል። የቀድሞ የትግራይ ኮምኒኬሽን ቢሮ ሐላፊ ወይዘሮ ሊያ ካሳም የህወሓት ስራ አስፈፃሚ ሆነው ተመርጠዋል። 

ይህ የህወሓት ጉባኤ ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም ተቃውሞ ቀርቦበት የነበረ ሲሆን፥ ውጤቱም ተቀባይነት እንደማይኖረው ተገልፆ ነበር። በሌላ በኩል ግን ይህን ጉባኤ ሕገወጥ ብለው የገለፁት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ፣ በርካታ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እና የፓርቲው ቁጥጥር ኮምሽን በጉባኤው ካለመሳተፋቸው በተጨማሪ የጉባኤው ውሳኔ እና ውጤት ተቀባይነት እንደማይኖረው ተገልፆ ነበር ሲል ሚልዮን ሃይለስላሴ ዘግቧል።

ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ

ኂሩት መለሰ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር