1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በጦርነት ወቅት ለጥቃት የሚዳረገው የሴቶች ሕይወት

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 4 2014

በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ዘርፈ ብዙ ቢሆንም በተለይ በጦርነት ወቅት እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለከፋ ችግር እንደሚዳረጉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ኢትዮጵያ ውስጥም ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ባስቆጠረው ጦርነት የበርካቶች ሕይወት መመሰቃቀሉን ሁኔታውን በቅርበት የመመልከት አጋጣሚውን ያገኙ ይናገራሉ።

https://p.dw.com/p/49qrg
Ethiopia's Tigray conflict: Rape as a weapon of war
ምስል DW

ጤና እና አካባቢ

በተለያዩ ሃገራት በሴቶች ላይ የሚፈጸመው ጾታዊ ጥቃት ስለመጨመሩ ይነገራል። ኢትዮጵያ ውስጥ ይዞታውን ለመግለጽ የተሠራ ጥናት ባይኖርም ለመብታቸው የሚሟገትላቸው መኖሩን በመረዳት የጓዳውን ጉዳይ አደባባይ የሚያወጡት በመበራከታቸው ከወትሮው የተለየ ሊመስል እንደሚችል የሚገልጹ አሉ። በተለይ በጦርነት ወቅት ሴቶች ይበልጥ የጥቃት ተጋላጭ እንደመሆናቸው በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከ17 ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት በብዙ እናቶች እና እህቶች ላይ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት አድርሷል። ለእነዚህ ወገኖች አስፈላጊውን የህክምናም ሆነ የምክር አገልግሎት ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ቢኖሩም የተጠናከረ ትብብር እና ርብርብ እንደሚያስፈልግ እየተነገረ ነው።

የሕግ ባለሙያዋ የሴቶች መብት ተሟጋች ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ለጾታዊ ጥቃት ለተጋለጡ ሴቶች ከለላ በመስጠት የምክር እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊውን አገልግሎቶችን እያደረገ የሚገኘው የሴቶች ማረፊያ እና ልማት ማህበር መሥራች እና ሥራ አስኪያጅ ናቸው።  ኢትዮጵያ ውስጥ የጥቃቱ ሰለባዎች ቁጥር ጨምሯል ወይም ቀንሷል ለማለት የተጠና ነገር አለመኖሩን፤ ሆኖም የበረከተ መስሎ የሚታየው ጥቃት ተፈጽሞባቸው ሳይነገር በጓዳ ይቀር የነበረው ችግር አደባባይ በመውጣቱ እንደሆነ ያስረዳሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ግጭት ጦርነት ባለበት አካባቢ በአብዛኛው ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት መጋለጣቸውን በቅርቡ የተከሰተውን በማሳያነት አንስተዋል።

«በግጭት ጊዜ ሴቶች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት እንደጦር መሣሪያ አድርገው ነው የሚወስዱት። ሴቶችን ማጥቃት ማለት ያንን አካባቢ ማጥቃት አድርገው ስለሚወስዱት ኢላማ /ታርጌት/የሚያደርጉት ሴቶች ላይ ነው። ሴቶችን በመድፈር፣ ሴቶች ላይ ጥቃትን በመፈጸም የአንድን አካባቢ ሰው ሀገርንም ቢሆን በቃ ይኼ አንገት ማስደፋት እና በደል ሴቶች እንደ መሣሪያ ይጠቀሙባቸዋል። የጥቃቱ ነገር ገና በጣም ብዙ ሥራ ይፈልጋል።»

የሕግ ባለሙያው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሕብረት ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲቀንሱ ለማስቻል የሚከናወኑት ተግባራት ውጤት እንዳያስገኙ ምክንያት የሆኑ ነጥቦች ያነሳሉ።

«ከሴቶች መብት ጋር በተገናኘ ብዙ ጊዜ በተለያየ መነሻ ባደረጉ ችግሮች ምክንያት ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በብዛት ያጋጥማሉ፤ ከቀን ወደቀን እየጨመሩ መልካቸውን እየቀየሩ እጅግ በጣም በተወሳሰበ እና በዚህ መልክ ይደረጋል ተብሎ በማይታሰብ መልኩ ሁሉ በጣም በቅርብ የቤተሰንብ አባላት በጓደኞች ጭምር እነዚህ ጥቃቶች እየተፈጸሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ነው ያለው።» 

Zwei Frauen ohrfeigen sich
ምስል picture-alliance/E.Topcu

ሴቶች ላይም ሆነ ሌሎች ተጋላጭ በሆኑ አካላት የመብት ጥሰት ሲፈጸም ተቀዳሚ ኃላፊነት ያለው መንግሥት መሆኑን ያነሱት የሕግ ባለሙያው በዚህ ረገድ ያለውም ቢሆን ያን ያህል አጥጋቢ እንዳልሆነም አመልክተዋል። ከሰላማዊው አውድ ውጪ በተለይ ግጭት ጦርነቶች ሲነሱ ሴቶች ዋነኛ የጥቃት ተጋላጮች መሆናቸው እየታየ ነው። በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ከተነሳው ጦርነት ጋር በተያያዘ በትግራይ ክልልም ሆነ በአማራ ክልል በርካታ ሴቶች ለጾታዊ ጥቃት እና ተገድዶ መደፈር መጋለጣቸው ይፋ ሆኗል። ወይዘሮ ማሪያ በተለይ ለሦስት ወራት በተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውረው ተመልክተዋል። አስፈላጊውን የምክር እና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግም እየሠሩ ነው።  ከደረሰባቸው ጾታዊ ጥቃት ሌላ በጦርነቱ የተበላሸውን መተዳደሪያቸውንም መልሰው እንዲያገኙ እያቋቋሙም ነው። የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቹ አቶ መሱድ ገበየሁ ለጥቃት ሰለባዎቹ ከሚደረገው ማናቸውም ድጋፍ ባሻገር ጥቃት ፈጻሚዎችን ተጠያቂ የማድረጉ እንቅስቃሴ እንዳለ ያመላክታሉ።

 በጦርነቱ ሂደት በሴቶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በሰለባዎቹ ላይ ብቻ ያበቃል ተብሎ እንደማይታሰብ ነው በስፍራው ተገኝተው ተጎጂዎችን መመልከትም ሆነ ማነጋገር የቻሉት ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር የገለጹልን። ሊደረግ ይገባል ያሉትንም ሆነ ከትግራይ ክልልም የመገናኛው መስመር እስኪቋረጥ ድረስ የተገኘው መረጃ እና ሌሎች አሁን በወልደያ እና ደሴ ለጥቃቱ ሰለባዎች የሚደረገውን በመጪው ሳምንት መሰናዶ በዚሁ ሰዓት ለመቃኘት ቀጠሮ ይዘን በዚሁ እነሰናበት።

 ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ