ጥቃት የጣለዉ ቱኒዝያዊ ተገደለ
ዓርብ፣ ታኅሣሥ 14 2009
አኒስ አምሪ የተባለዉ የ 24 ዓመት ቱኒዝያዉ ስደተኛ ወንጀሉን ለመፈፀሙ ምንም ጥርጥር እንደሌለ ተመልክቶአል። ሽብርተናዉ ተጠርጣሪ መገደሉ እፎይታን ቢሰጥም ፤እሱን ይረዱ የነበሩ ሰዎች መኖራቸዉ የማያጠያይቅና እነዚሁ ሠዎች አደናዉ መቀጠሉ ተመልክቶአል።
ተጠርጣሪዉ የቱኒዚያ ዜጋ አኒስ አምሪ በሁለት የጣሊያን ፖሊሶች ከሌሊቱ 9 ሰዓት ላይ መታወቂያ ሲጠየቅ ሽጉጥ አዉጥቶ አንደኛዉን በማቁሰሉ እዚያዉ በጥይት መገደሉ ነዉ የተገለጸዉ። የጣሊያን የሀገር ዉስጥ ሚኒስትር ማርኮ ሚኒቲ፤
«ዛሬ ሌሊት በ9ሰዓት ላይ ሚላን፤ ሴስቶ ሳን ጆቫኒ ባቡር ጣቢያ መደበኛ ቁጥጥር ሲካሄድ ለዚህ ተግባር የተሰማሩ ፖሊሶች ጥርጣሬ የፈጠረባቸዉን አንድ ሰዉ ያስቆማሉ። ግለሰቡ ወዲያዉ ሽጉጡን አዉጥቶ ሳያመነታ መታወቂያ ወደጠየቀዉ ፖሊስ ላይ ይተኩሳል። ፖሊሱ ክርስቲያን ማቪዮ ይባላል። ለጥበቃ የተሰማራዉ ፖሊስም ወዲያዉ አፀፋዉን መለሰ። እንደእድል ሆኖ ክርስቲያን ማቪዮ የሚያሰጋ ቦታ ላይ አልተመታም። ሃኪም ቤት ገብቶ በማገገም ላይ ነዉ፤ ሁኔታዉም ለሞት አያሰጋም።»
ተጠርጣሪዉ በርሊን ላይ አደጋዉን ካደረሰ ወዲህ ለቀናት በመላዉ አዉሮጳ ሲፈለግ ቆይቷል። ግለሰቡ በፈረንሳይ በኩል ወደ ጣሊያን እንደተጓዘ ከተሰማ በኋላም የአዉሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ድንበር ክፍት መሆን የለበትም የሚሉት ወገኖች ትችታቸዉን አጠናክረዋል። መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የጥገኝነት ጥያቄያቸዉ ተቀባይነት ያላገኘ የቱኒዚያ ዜጎችን ወደሃገራቸዉ የመመለሱ ርምጃ እንዲፋጠን ለቱኒዚያ ፕሬዝደንት ማሳሰቢያ አቅርበዋል። ስለተጠርጣሪዉ መገደልና የፖለቲከኞች አስተያየት የበርሊንና የሮም ወኪሎቻችን በስልክ ጠይቀናል።
ተክለዝጊ ገ/እየሱስ
ይልማ ኃይለሚካኤል
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መኃመድ