1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ ሰዎች በድንጋይና በዱላ ተወግረው ተገደሉ

ሰኞ፣ ግንቦት 29 2014

በደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ ዘጠኝ ሰዎች በድንጋይና በዱላ ተወግረው ተገደሉ ፡፡ ግድያው ከትናንት በስተያ ቅዳሜ የተፈጸመው በልዩ ወረዳው ሶያማ ከተማ በሚገኝ የገበያ ሥፍራ ነው ፡፡ የዶቼ ቬለ DW ታማኝ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከሟቾቹ በተጨማሪ ሃያ አንድ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4CKhH
Äthiopien Markt in Burji
ምስል Sonderregionalregierung Burji

ቡርጂ ልዩ ወረዳ በገበያ ስፍራ በደረሰ ጥቃት በርካታ ሰዎች ተገደሉ

ሟቾቹ ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን በመነሳት ሶያማ ተብሎ በሚጠራው የደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳው ከተማ ለገበያ የመጡ የኦሮሞ ጉጂ ብሄር ተወላጆች ናቸው ተብሏል፡፡ በሥፍራው ነበርን ያሉ የአይን እማኞች ለዶቼ ቬለ DW እንዳሉት ግድያው በሰዎቹ ላይ የተፈጸመው ራቅ ባለ የገጠር ቀበሌ አንድ የኦሮሞ ጉጂ ብሄር አባል የቡርጂን ሰው ገድሏል የሚል ወሬ በገበያው ውስጥ ከተሠራጨ በኋላ ነው፡፡

ከጥቃቱ ለጥቂት ማምለጡን የሚናገረው አንድ የአካባቢ ነዋሪ በሶያማው የገበያ ሥፍራ ተመለከትኩ ያለውን ለዶቼ ቬሌ  DW ሲገልጽ ‹‹ በገበያ መሀል እያለን አንድ የቡርጂ ሰው በኦሮሞ ጉጂ ብሄር ተገለደ የሚል ወሬ በገበያ ውስጥ ተናፈሰ ፡፡ ወዲያውኑ በገበያው አካባቢ የነበሩ ወጣቶች በመሰባሰብ ‹‹ የእኛን ሰው እየገደላችሁ ከእናንተ ጋር እንገበያይም ›› በማለት የጀመሩት ረብሻ ወደ ግድያ ተሸጋገረ፡፡ በገበያ ውስጥ የተገደሉት ሱሮ ባርጉዳ ከሚባል የኦሮሚያ ወረዳ ዕቃ ለመሸጥና ለመግዛት የመጡ የኦሮሞ ጉጂ ብሄር ተወላጆች ናቸው ፡፡ የተገደሉትም በድንጋይ ተወግረው ፣ እንዲሁም በዱላና በሸንኮራ አገዳ ተቀጥቅጠው ነው ፡፡ አብዛኞቹ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ ሸሽተው ባይጠለሉ ኖሮ ከዚህ የበለጠ ሰው ሊጎዳ ይችል ነበር ፡፡ እኛም ለጥቂት ነው ሮጠን ያመለጥነው ›› ብሏል፡፡

በደቡብ ክልል የቡርጂ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማሬ አለማየሁ በልዩ ወረዳው ጥቃት ሥለመፈጸሙ ለዶቼ ቬሌ DW  አረጋግጠዋል፡፡ አንድ የኦሮሞ ጉጂ ብሄር አባል የቡርጂን ሰው ገሏል የሚለው ወሬ በገበያው መሀል መሠራጨቱ ለግድያው መነሻ ሰበብ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው ተናግረዋል፡፡ በጥቃቱ ዘጠኝ ሰዎች ሲገደሉ ሌሎች ሃያ አንድ ሰዎች ተጎድተው ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡

Äthiopien Markt in Burji
ምስል Sonderregionalregierung Burji

በጥቃቱ የተገደሉት ሰዎች የኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ሱሮ ባርጉዳ ከተባለው ወረዳ ወደ ደቡብ ክልል ቡርጂ ልዩ ወረዳ ለገበያ የሄዱ ሰዎች መሆናቸውን የሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ሰላም ፀጥታ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡ የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ቡልቡላ ጅኦ በዕለቱ በአጎራባች የቡርጂ ልዩ ወረዳ ድንበር ላይ እሳቸው ሽፍታ ሲሉ የጠሩት የሸኔ ቡድን አንድ የቡርጂ ተወላጅን መግደሉን ለዶቼ ቬሌ DW ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም በሶያማ ከተማ በመገበያየት ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት እንዲፈጸም ምክንያት ሆኗል ብለዋል፡፡

አሁን የደረሰው ጥቃት ተባብሶ እንዳይቀጥል በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ያሉት የቡርጂ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪው አቶ ማሬ አለማየሁ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለሕግ የማቅረብ ሥራዎች መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑወቅት የጥቃቱ ቀንደኛ ታሳታፊ የሆኑ ሰዎች እየተለዩ እንደሚገኙ የተናገሩት ዋና አስተዳዳሪው እስከአሁንም አሥር ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዋና አስተዳዳሪው ጠቅሰዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ