በደቡብ አፍሪቃ ምርጫ ማን ያሰጋው ይሆን?
ቅዳሜ፣ ግንቦት 10 2016ገዥው ፓርቲ ኤኤንሲ በግንቦቱ ምርጫ አብላጫውን ድምፅ እንደሚያጣ ከወዲሁ ተገምቷል ። ለብዙ መራጮች፣ ምርጫው በደቡብ አፍሪቃ ዴሞክራሲ ተስፋውን ለመመለስ ሌላ አማራጭ ይሰጣቸዋል ተብሎ ይጠበቃል ።
ደቡብ አፍሪቃ አጠቃላይ ምርጫ ለማድረግ ከሁለት ሳምንት ያነሰ ጊዜ ብቻ ይቀራታል ። ግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫ የምታደርገው ደቡብ አፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከዴሞክራሲ ሥርዓት ጋ ከተዋወቀች 30 ዓመታት ተቆጥሯል ። ምርጫው ላይ የተጋረጠው ተግዳሮትም ከወዲሁ ብርቱ መሆኑ ዕየታየ ነው።
በርካታ ምርጫዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ፦ ገዢው የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ፓርቲ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፖዛ ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት ወዲህ አብላጫ ፓርቲነታቸውን ሊነጠቁ ይችላሉ ። ያም ሆኖ ግን ፓርቲው ጠባብም ቢሆን አብላጫ ድምጽ ሊያገኝ ይችላል ። ይህን ያሉት በደቡብ አፍሪቃ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ተቋም የአፍሪቃ መንግሥታዊ አስተዳደር እና ዴሞክራሲ ዓለም አቀፍ ተቋም ኃላፊው ስቴቨን ግሩዝድ ናቸው ።
«እኔ በግሌ የሚሰማኝ ኤ ኤን ሲ ፓርቲ ምንም እንኳን በብዙኃኑ ዘንድ ተቀባይነቱ ቢቀንስም የሚያገኘው ድምፅ ከ50 በመቶ በትንሹ ከፍ እንደሚል ነው ። » እንደ ስቴቨን ግሩዝድ ከሆነ፦ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ ባለፉት ዓመታት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜያት ለነበረው ደካማ እንቅስቃሴ በምርጫ ሊቀጣ ይችላል ።
ዴሞክራሴ የተጋረጠበት ፈተና
የደቡብ አፍሪቃ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ተንታኙዋ ቴሳ ዱምስ ግን ምርጫው የሚያሰጋው ኤኤን ሲን ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ያለው አጠቃላይ የምርጫ ሥርዓቱንም ነው ባይ ናቸው ። «ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ በዚህ ዓመት ምርጫው የደቀነው ሥጋት ከፍተኛ ነው ። እጅግ በርካታ ሰዎች በዚህ ወቅት ዴሞክራሲ በሚለው ጽንሠ-ሐሳብ ራሱ ግራ ስለተጋቡ ሥጋቱ ከፍ ያለ ነው ።» እንደ ቴሳ ዱም ትንታኔ፦ ምርጫዎች ሕዝቡ የሚፈልገውን ባለማስገኘታቸው ዴሞክራሲ በማኅበረሰብ ግንባታ ላይ ስለሚጫወተው ሚና በርካቶች ተስፋ ቆርጠዋል ።
«እናም ሰዎች ራሳቸውን ከምርጫ ሥርዓት እያገለሉ ነው ። ሌሎች ዴሞክራሲያዊ ተቋማትም በብዙኃኑ ዘንድ እየተተዉ ነው ።» ቴሳ ዱም ምርጫ የዴሞክራሲ አካል ከመሆን ባሻገር ያመጣው ለውጥ የለም የሚል ስሜት በበርካቶች ዘንድ መስረጹን አክለዋል ።
መራጮች ቃል የተገባለቸው አልተጠበቀም
በደቡብ አፍሪቃ መራጮች በከፍተኛ ደረጃ የመከፋት ስሜት እንዳደረባቸው ቴሳ ዱም ይናገራሉ ። እናም በርካቶች ምናልባትም በግንቦት መጨረሻው ምርጫ ያጡትን እምነት መልሰው ያገኙ እንደሆነም ተስፋ ሰንቀዋል። «እናስ ዴሞክራሲያዊ ሒደቱ በእርግጥም ለውጥ እና ውጤት ማስገኘት ችሎ መራጮች ያጡትን እምነት መልሰው ያገኙ ይሆን? » ይጠይቃሉ የፖለቲካ እና የማኅበራዊ ተንታኙዋ ቴሳ ዱምስ ።
ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ዴምክራሲያዊ ሥርዓቱ የተፈለገውን ያህል ውጤታማ አለመሆኑ በዜጎች የኑሮ ሁኔታ ላይ ተጽእኖውን አሳርፏል ። ምንም እንኳን ደብብ አፍሪቃ የአኅጉሪቱ የአፍሪቃ የምጣኔ ሐብት ቀንዲል ብትሆንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ ግን በማኅበረ ኤኮኖሚያዊ ችግሮች ጥልቅ አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀዋል ። ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፖሳ ባለፈው የካቲት ወር ለመላ ሀገሪቱ ነዋሪዎች ንግግር ባሰሙበት ወቅት፦ የደቡብ አፍሪቃ ድህነት እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1993 ከነበረበት 71 በመቶ በ2020 ወደ 55 ከመቶ ዝቅ ማለቱን ገልጠዋል ። 1993 በደቡብ አፍሪቃ የነች የበላይነት የአፓርታይድ ሥርዓት በይፋ ያከተመበት ወቅት ነው ። የዓለም ባንክ የ2008 መረጃ እንደሚያመለክተው የድሕነት መጠኑ በደቡብ አፍሪቃ ከ62 እስከ 63 በመቶ እንደነበር ያሳያል ።
የወጣቶች ሥራ አጥነት
መሻሻል የሚገባው የወጣቶች ሥራ አጥነት ኹኔታም በምርጫው ወቅት አንዱ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ። በደብ አፍሪቃ የሥራ አጥነቱ መጠን ባለፈው ዓመት 32.4% እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ ።
ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት እሥራኤልን በጋዛ ሠርጥ ድብደባ መክሰሷም በምርጫው ላይ የራሱ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተንታኞች ይናገራሉ ። ስቴቨን ግሩዝድ እንደሚሉት ከሆነ የደቡብ አፍሪቃ ይህ እንቅስቃሴ በሀገሯ ምእራባዊ ኬፕ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ሙስሊሞችን ድምፅ ለማግኘት በሚል ነው ።
«ደቡብ አፍሪቃ በዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትላይ ያላት ጠንካራ የፍትሕ አቋም እና እሥራኤልን በዘር ፍጅት መክሰሷ በምእራብ ኬፕ እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የሙስሊሞችን ድምፅ በምርጫ ለማግኘት ያለመ መሟሟት ነው ሲሉ አንዳንዶች ይናገራሉ ። »
የጄኮብ ዙማ ከANC ፓርቲ መልቀቅ ያስከተለው ጣጣ
የቀድሞው ፕሬዚደንት ጄኮብ ዙማ ከአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግሬስ (ANC) ፓርቲ ለቅቀው ሌላ ፓርቲ በማቋቋማቸው ኤኤንሲ በዘንድሮ ምርጫ የማሸነፍ ዕድሉ አሽቆልቁሏል ሲሉ ቴሳ ዱምስ ይሞግታሉ ። ስቴቨን ግሩዝድ በተቃራኒው የጄኮብ ዙማ ሌላ ፓርቲ ማቋቋም ኤኤንሲን በምርጫው ከማሸነፍ አያግደውም ብለዋል ። ይልቁንም ከባዱ ጉዳይ ጥምር መንግሥት ለማቋቋም መቸገሩ ይሆናል ብለዋል።
ኤኤንሲ በምርጫው አሸንፎ መንግስት መመሥረት ካልቻለ፥ ምናልባትም በአንደበተ ርትኡው ፖለቲከኛ ጁሊዬስ ማሌማ ከሚመራው የየኤኮኖሚ ነጻነት ታጋዮች (EFF) ፓርቲ ጋ ጥምረት ሊኖር እንደሚችል ብዙዎች ከወዲሁ ይገምታሉ ። የሁለቱ ጥምረት ግን ኤኤንሲን ጭራሽ ወደ ግራ ዘመም ወስዶት ይበልጥ ወግ አጥባቂ ሊያደርገውም ይችላል ። ውጤቱ ምንም ሆነ ምን ግን ደቡብ አፍሪቃውያን መራጮች ለመላ ሀገሪቱ የሚተርፍ የኤኮኖሚ እድገት እና ደኅንነትን አጥብቀው ይሻሉ ። ደቡብ አፍሪቃውያን በስተመጨረሻ ምን እንደወሰኑ በአጠቃላይ ምርጫው ግንቦት 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም መመልከት ነው ።
ኢሣቅ ካሌዲች/ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ