1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጸደይ ጉባኤ ስለ ኢትዮጵያ ምን ተባለ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 11 2015

በዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ጉባኤ የኢትዮጵያ ዕዳ እና ዴቪድ ማልፓስ "በቅጡ አልሰራም" ያሉት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መነጋገሪያ ነበሩ። የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ "ዘላቂ ካለመሆኑም በላይ ለኤኮኖሚው ረባሽ" መሆኑን ገልጸዋል። አቶ አሕመድ "ኢትዮጵያ የማክሮ ኤኮኖሚውን መዛባት ለመፍታት ቁርጠኛ ነች" ብለዋል

https://p.dw.com/p/4QIv8
2023 Spring Meetings of the World Bank and International Monetary Fund
ምስል Celal Gunes/AA/picture alliance

በዓለም ባንክ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የጸደይ ጉባኤ ስለ ኢትዮጵያ ምን ተባለ?

ለአንድ ሣምንት የተካሔደው የዓለም ባንክ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የጸደይ ጉባኤ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ሥመ-ጥር ባለሙያዎች የተጋበዙባቸው በዓለም ኤኮኖሚ ይዞታ ላይ ያተኮሩ ውይይቶች የተካሔዱበት ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮችን ያጎበጠው ዕዳ እና ጫናውን ለመቋቋም ሊወሰዱ የሚገቡ እርምጃዎችም ትኩረት አግኝተዋል። በጉባኤው የኢትዮጵያ ጉዳይ ብቅ ያለው ግን ገና በመክፈቻው ሰኞ ሚያዝያ 2 ቀን 2015 ነበር።

የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዲቪድ ማልፓስ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂዬቫ ጋር ጉባኤውን ለመጀመር ባደረጉት ግማሽ ሰዓት ገደማ በረዘመ ውይይት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ጉዳይ አንስተዋል። "ለጥቂቶች የሚቀርብ ኦፊሴላዊ የውጭ ምንዛሪ ግብይት እና ለተቀሩት እጅግ በጣም ውድ የሆነ የጎንዮሽ ምንዛሪ ግብይት አላቸው። ይኸ በቅጡ አልሰራም" ያሉት የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት ዴቪድ ማልፓስ  "መፍትሔ ማግኘት ይቻል ከሆነ በዕዳ ላይ በሚኖረን ውይይት ወይም በዚህ ሣምንት በምናደርገው ስብሰባ ጉዳዩን ዳግም እንመለከታለን" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዲቪድ ማልፓስ ይኸን አስተያየት በሰጡ በሁለተኛው ቀን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምኅረቱ ከተካተቱበት የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ልዑክ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። ዴቪድ ማልፓስ ባወጡት መግለጫ ውይይቱ ኢትዮጵያ ማክሮ ኤኮኖሚውን ለማረጋጋት ባላት አስቸኳይ ፍላጎት ላይ ያተኮረ እንደነበር አስታውቀዋል።

በዚህ መግለጫቸው የዓለም ባንኩ ፕሬዝደንት የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ይገባል ያሏቸውን በርከት ያሉ ምክሮች ለግሰዋል። የዴቪድ ማልፓስ ምክረ ሐሳቦች በጥቆማ መልክ ይቅረቡ እንጂ ጠጠር ያሉ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ናቸው። ኢትዮጵያ ድርቅ፣ የአገር ውስጥ ግጭቶች፣ ዕዳ እና የተወሳሰቡ መዋቅራዊ ፈተናዎች ውስጥ ብትሆንም "ፈጣን እና ቁርጠኛ የፖሊሲ ማሻሻያዎች" ተግባራዊ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኤኮኖሚው ያሉበትን መዛነፎች እንዲያስወግድ፤ ከመንግሥት-መር የኤኮኖሚ ሞዴል እንዲርቅ፤ ለቢዝነስ ምቹ የሆነ ከባቢን እንዲያሳድግ፣ በፋይናንስ ዘርፍ የበለጠ ውድድር እንዲኖር እንዲፈቅድ እና በግሉ ዘርፍ የሚመራ ኤኮኖሚያዊ ዕድገት እንዲያመቻች አበረታተዋል። ኢትዮጵያ በቡድን 20 በኩል የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ለማድረግ ያቀረበችው ጥያቄ እንዲጠናቀቅ መንግሥታዊ እና የግል አበዳሪቿ በፍጥነት ሥምምነት ላይ እንዲደርሱም ጥሪ አቅርበዋል።

በዚህ ውይይት የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት በተመለከተ የተላለፈ ውሳኔ ስለመኖሩ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። የዓለም ባንክ ፕሬዝደንት በመሩት በዕዳ ጫና እና በዕድገት ላይ ያተኮረ ውይይት ላይ የተሳተፉት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ግን መንግሥታቸው የውጭ ግብይት ምንዛሪ ሥርዓቱን ለመቀየር ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

"ኢትዮጵያ የማክሮ ኤኮኖሚውን መዛባት ለመፍታት ቁርጠኛ ነች" ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ "በተለይ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ማሻሻያው እጅግ ጠቃሚ ነው" ብለው ነበር።  "አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ዘላቂ ካለመሆኑም በላይ ለኤኮኖሚው ረባሽ ነው" ያሉት አቶ አሕመድ መፍትሔ ሊፈለግለት እንደሚገባ ጠቁመው "እንዴት መቀጠል እንዳለብን ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና ከዓለም ባንክ ጋር እንወያያለን" ሲሉ ተደምጠዋል።  

የኢትዮጵያ መንግሥት በሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓቱ በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን ሊያደርግ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል። ይኸ እርምጃ በማሻሻያ መርሐ-ግብሩ የመጀመሪያ ምዕራፍ የተካተተ ነበር። ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሀገር በቀል ማሻሻያ ምዕራፍ ተግባራዊ ስታደርግ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ሥምምነት ተፈጽሞ ነበር።

የተራዘመ የብድር አቅርቦት (Extended Credit Facility) እና የተራዘመ የፈንድ አቅርቦት (Extended Fund Facility) በተባሉ ሁለት ማዕቀፎች በሶስት ዓመታት ለኢትዮጵያ ሊሰጥ የታቀደው ብድር የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በዘላቂነት መፍታት እና በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት መዘርጋትን ጨምሮ አምስት አበይት ምጣኔ ሐብታዊ ሥራዎች ሊከወኑበት የታቀደ ነው። ይሁንና ማሻሻያው ተግባራዊ በተደረገባቸው ዓመታት ብር ከዶላር አኳያ ያለው የምንዛሪ ተመን በሽርፍራፊ ሳንቲሞች እየተዳከመ ሲሔድ ቢቆይም እርምጃው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ አልሆነም።

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት
ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የሀገር በቀል ማሻሻያ ምዕራፍ ተግባራዊ ስታደርግ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2.9 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር ሥምምነት ተፈጽሞ ነበር።ምስል Yuri Gripas/REUTERS

አቶ አሕመድ ሽዴ "የዋጋ ንረት ችግር፣ የውጭ ምንዛሪ ተግዳሮት እና የዕዳ ሥጋት መጨመር ለአጠቃላይ ኤኮኖሚው እና ከግሉ ዘርፍ መዋዕለ-ንዋይ ለመሳብ አስገዳጅ እንቅፋት እንደሆኑ ተንትነናል። መንግሥት በኤኮኖሚው ውስጥ ያለውን ሚናም ስናስተካክል ነበር። በግል ዘርፍ ለሚመራ ዕድገት ብዙ ቦታ እየፈጠርን ነበር" ሲሉ በሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ምዕራፍ መንግሥታቸው ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል እየጠቀሱ በዋሽንግተኑ ጉባኤ አስረድተዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ ከጠቀሷቸው ማሻሻያዎች መካከል "በአጠቃላይ ለመላው ህዝብ" ይደረግ ነበር ያሉት "አባካኝ የነዳጅ ድጎማ" አንዱ ነው። "አሁን ወደ የታለመ የነዳጅ ድጎማ እየተሸጋገርን እንገኛለን። የኤኮኖሚ ማሻሻያው ተግባራዊ በሆነባቸው የመጀመሪያ ጥቂት ዓመታት ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን ብድር በመገደባችን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሷል" ሲሉ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የተከሰቱ ግጭቶች፣ ድርቅ፣ የበረሐ አንበጣ ወረርሽኝ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የምግብእና የሸቀጦች ዋጋ መናርን በመሳሰሉ በርካታ ተደራራቢ ፈተናዎች የመንግሥትን ወጪ ማናራቸውን ያስታወሱት አቶ አሕመድ "አሁን እንኳ ለመልሶ ግንባታ እና ማገገሚያ የሚያስፈልገው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ ነው" ሲሉ መንግሥታቸው የገጠሙትን ፈተናዎች ጠቃቅሰዋል። "ለዚህም ነው ወደ ጉልህ ማሻሻያ በምንሸጋገርበት ነገር ግን እነዚህ በርካታ ፈተናዎች በመሠረታዊ ልማት ላይ ተጨማሪ ወጪ እንድናወጣ በሚያስገድዱበት በዚህ ወቅት ከዓለም ባንክ እና ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ያለን አጋርነት እጅግ ጠቃሚ እና አንገብጋቢ የሚሆነው" ሲሉ አገራቸው ዕገዛ እንደምትሻ ጠቁመዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ የተካተቱበት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ቆይታው ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂዮርጂዬቫ ጋር ጭምር ተገናኝቶ ተወያይቷል። ክሪስታሊና ጂዮርጂዬቫ እንዳሉት ውይይቱ "ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ሁለተኛ ምዕራፍን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እንዴት መደገፍ ይችላል?" በሚለው ጉዳይ ላይ ያጠነጠነ ነበር።

ኢትዮጵያ ለማሻሻያው ሁለተኛ ምዕራፍ እገዛ መጠየቋን ያረጋገጠው ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ወደ አዲስ አበባ የላካቸው ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተው ተመልሰዋል። ባለሙያዎቹ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ለማሻሻያው በሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ መጠን ላይ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉት ውይይት በጎ እርምጃ ማሳየቱን ገልጸዋል። ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትም ሆነ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የገንዘብ መጠኑን እስካሁን በይፋ አልገለጹም።

ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ አራት የመረጃ ምንጮች ግን ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት 2 ቢሊዮን ዶላር ለመበደር በመነጋገር ላይ እንደምትገኝ ለሬውተርስ ገልጸዋል። በሬውተርስ ዘገባ መሠረት በብድር መጠኑ ላይ ከሥምምነት ያልተደረሰ ሲሆን በኢትዮጵያ ዕዳ ዘላቂነት ትንተና እየተመከረ ነበር። ይኸ የዕዳ ዘላቂነት ትንተና በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ በጥምረት የሚዘጋጅ ሲሆን ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የገንዘብ መጠን ላይ አንዳች መረጃ የሚሰጥ ነው።

ትንተናው በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና በዓለም ባንክ እጅ ውስጥ ብቻ ተወስኖ መቆየቱን የገለጹት ዴቪድ ማልፓስ ለኢትዮጵያ እና ለአበዳሪዎቿ ጠቃሚ በመሆኑ ለሌሎች ለማጋራት ጥረት እንደሚደረግ ጥቆማ ሰጥተው ነበር። ኢትዮጵያ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ከተስማሙ ብድሩ በተቋሙ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መጽደቅ ይኖርበታል። ይኸ ቦርድ ከአራት ዓመታት በፊት ለኢትዮጵያ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ብድር አጽድቆ ነበር። ይኸ ብድር ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ እጅ ሳይገባ በመስከረም 2014 ተቋርጧል።

እሸቴ በቀለ