1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በውስጣዊ ክፍፍል ውስጥ ያለው ህወሓት የምርጫ ቦርድን መልስ እየተጠባበቀ ነው

ሰኞ፣ ሐምሌ 22 2016

በውስጣዊ ክፍፍል ውስጥ ያለው ህወሓት ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ከምርጫ ቦርድ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ። የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ጉባኤ ለማድረግ ማቀዱ ከጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር መልስ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/4is6N
Äthiopien | Flagge Tigray People’s Liberation Front (TPLF
ምስል Million Haileyessus/DW

«ሕወሓት የቀደመ ማንነቱ እንዲመለስለት እየጠበቀ ነው » ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

በውስጣዊ ክፍፍል ውስጥ ያለው ህወሓት ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት ከምርጫ ቦርድ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን አስታወቀ። የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ጉባኤ ለማድረግ ማቀዱ ከጦርነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ሲሉ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር መልስ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት፥ የትግራይ የፖለቲካ አመራር ህዝቡን ከጥፋት የሚታደግ ተግባር ከመፈፀም ይልቅ፥ በተፃራሪ ቆመዋል ብለዋል።

«ከብልጽግና ፓርቲ ጋር የውህደት ውይይት አልጀመርኩም» ህወሓት

በውስጣዊ ችግር ውስጥ ያለው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ህወሓት፥ አመራሮቹ በሐሳብ በተለያዩ ሁለት ቡድኖች ተከፋፍለው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ማድረግ እና ማዘግየት በሚል እንዲሁም ሌሎች አጀንዳዎች እየተወዛገቡ ይገኛሉ። በፓርቲው እና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በሳምንቱ መጨረሻ ለመንግስታዊ እና የፓርቲው መገናኛ ብዙሐን መግለጫ የሰጡት የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ሕጋዊ እውቅናው ለማረጋገጥ፣ ውስጡ ለማፅዳት እና በቀጣይም ጠንካራ ፓርቲ ለመሆኑ እየሰራ መሆኑ ተናግረዋል።

ህወሓት የጠራው ጠቅላላ ጉባዔ እና በፓርቲ ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል

የህወሓቱ መሪ ጨምረው ፥ በቅርቡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ ሳያገኝ ወደ ጉባኤ የሚያመራ ከሆነ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑ እና በዚሁ ጉዳይ ዙርያም ከጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ጠቁመዋል።

የህወሓት ዋና መስሪያ ቤት መቀሌ
የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን መሪ አቶ ተክለብርሃን አርአያ "ስልጣን መቆጣጠር የሚፈልጉ፥ ፓርቲ ማዳን ሳይሆን የግል ስልጣንህ ማዳን ነው ፍላጎቱ።ምስል Million H. Selassie/DW

 

ደብረፅዮን "እውቅና ይኑረው አይኑረው፥ ጉባኤ ማካሄድ ጦርነት አይታወጅበትም። ጉባኤውም ጦርነት የሚታወጅበት ስብሰባ አይደለም። ሰላማዊ ነው። በፕሪቶሪያ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነህ እየተደረገ ያለ ነው። ህወሓት መዓት ስብሰባ ነው የሚያካሂደው። ጉባኤ ስለተባለ ወደ ጦርነት የሚኬድበት ነገር የለም። ከሌለ ለጉባኤው እውቅና አለመስጠት እንጂ ሌላ ነገር አያስፈልግም" ብለዋል።

ሕወሓት በ50 ዓመት ታሪኩ አጋጥሞት በማያውቅ ፈተና ውስጥ እንዳለ ዐሳወቀ

 

የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን የፓርቲው ጠቅላይ ጉባኤ ለማድረግ የሚደረግ እንቅስቃሴ በማውገዝ በሰጠው መግለጫ፥ የታቀደው ጉባኤ የህወሓት የተወሰነ ቡድን ስልጣኑ ለማስጠበቅ ያቀደው መድረክ መሆኑ አስታውቋል።

የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን መሪ አቶ ተክለብርሃን አርአያ "ስልጣን መቆጣጠር የሚፈልጉ፥ ፓርቲ ማዳን ሳይሆን የግል ስልጣንህ ማዳን ነው ፍላጎቱ። እንደዚህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው አመራሮች አሉ ወይ ከተባለ አዎ ነው መልሱ። ምንም ቁጭት የማይሰማቸው፣ ፓርቲ ማዳን በሚል ሽፋን ጉባኤ ይፈልጋሉ። ይህ ግን የሁሉም አይደለም" ሲሉ ገልፀዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ፥ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ ማቅረቡ እና በሁለት ሳምንት ውስጥ ምላሽ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል። ህወሓት የነበረው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ እንጂ እንደአዲስ ፓርቲ መመዝገብ እንደማይፈልግ ደብረፅዮን ገልፀዋል።

ዶ/ር ደብረ ጽዪን ገብረሚካኤል
የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በሰጡት መግለጫ ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋልምስል Eduardo Soteras/Getty Images

 

ህወሓት «በልዩ ሁኔታ» በፓርቲነት እንዲመዘገብ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠየቀ

ህወሓት በተለያዩ የትግራይ ወረዳዎች የካድሬዎቹ ስብሰባ እያካሄደበት ባለበት የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ እንደሚያሳየው ፥ የግዚያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ተግባር ዘላቂ ሰላምና እና መረጋጋት ማስፈን ነው ያለ ሲሆን ከዚህ ውጭ የሚደረግ "ሰላም የሚያውኩ፣ ሕገወጥነት የተላበሱ" ተግባራት አይታገስም ሲል አስጠንቅቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ የፖለቲካ መሪዎች ህዝብና ሀገር ወደ ጥፋት ከሚመራ አካሄድ ተቆጥበው ልዩነታቸው በሰለጠነ መንገድ ይፍቱ ሲሉ በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሲቪል ተቋማት በጋራ ባወጡት መግለጫ አሳስበዋል። የትግራይ የፖለቲካ አመራር ህዝቡን ከጥፋት የሚታደግ ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት ሲገባው በተፃራሪ መንገድ መጓዙን ሲቪል ተቋማቱ ተችተዋል።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ታምራት ዲንሳ

አዜብ ታደሰ