1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ የጸጥታ ፈተና ባለባቸው አከባቢዎች የበዓል ይዞታ

ሥዩም ጌቱ
ረቡዕ፣ መስከረም 1 2017

ማህበረሰቡ በዓሉን እንደ አቅሙ ሁኔታ ለማሳለፍ ቢጥርም ያሉት የጸጥታ ስጋቶች እና የኢኮኖሚ ቀውስ የተፈጠረው የዋጋ ንረት የተለመደውን የዓል አከባበር አደብዝዞታል ይላሉ አስተያየታቸውን ለዶይቸ ቬለ ያካፈሉን የአካባቢው ነዋሪዎች።

https://p.dw.com/p/4kVix
ምዕራብ ወለጋ ነጆ ሰዎች ጎዳና ላይ
ምዕራብ ወለጋ ነጆምስል Negassa Deslagen/DW

በኦሮሚያ የጸጥታ ፈተና ባለባቸው አከባቢዎች የበዓል ይዞታ

በኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ይዞታውና የኑሮ ውድነት የአዲስ ዓመት በዓል ድባቡን እንደተጫጫኑት የጸጥታ ይዞታው የሚፈትናቸው ነዋሪዎች አስታወቁ፡፡  ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ስር ይተዳደር የነበረውና ባለፈው አንድ ዓመት ከመንፈቅ ለሚሆን ጊዜ ወደ ምስራቅ ቦረና ዞን  ከተካለለው ጎሮዶላ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪ፤ ሀሳባቸውን ማብራራት የጀመሩት ዛሬ አሮጌ ከተሰኘው ከ2016 ዓ.ም. ትውስታ በመጀመር ነው፡፡ “በአከባቢያችን ከዞን መዋቅሩ ጋር በተገናኘ የጸጥታ ችግር አለ፡፡ በ2016 በነበረው የጸጥታ ችግርና ሁከት የጸጥታ አካላትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች በታጠቁ አካላት በብዛት የተገደሉበት ስለነበርም አሮጌውን ኣመት በህዝቡ በመልካም አይታወስም፡፡ ያው ግን ማለፉ አይቀርም አልፏል መልካም ነው” ሲሉ ያለፈውን ጥለው ስለወደፊቱ መልካም ነገር ማለማቸውን ቀጥለዋል።
አስተያየት ሰጪው አከሉ፤ በግጭት ምክንያት ምርት ማነሱ፤ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ተገድቦ ገቢያው በመቀዛቀዙ የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ ነክቷል፡፡ ይህም የበዓል አከባበር ይዞታውን እንደ ድሮ ሊያደምቅ አልቻለም፡፡ “ለስድስት ዓመታት ግድም  በጸጥታ ችግር  እየተፈተነ ለብርቱ ስቃይ ተዳረገው ህዝብ አላረሰምና የኑሮ ውድነቱ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ በትንሹም ብሆን በማሳ ላይ የተዘራውም ሆነ የተደለበ ከብት ወደ ተሻለ ገቢያ መውሰጃ መንገዱ ስለለሌ፤ በጸጥታ ችግሩ ወደ ከተማ ገብተው የሰው እጅ እየተመለከቱ ካሉ አርሶአደር ጋር ተዳምሮ ችግሩ ከፍቷል ብለዋል፡፡ ከዚህ የተነሳም ምንም እንኳ ህዝቡ እንኳን ከኣመት ዓመት አሸጋገርከን ለማለት ያህል በዓሉን ለማክበር የአቅሙን ብዘጋጅም እንደ ድሮው በተለመደ ደስታና በተሟላ ገበታ በዓል አልተከበረም ብለዋልም፡፡

አርሲ በእሳት የጋየ መኪና
አርሲ በእሳት የጋየ መኪናምስል Seyoum Getu/DW

ምዕራብ ኦሮሚያ

ከምዕራብ ኦሮሚያ ምስራቅ ወለጋ  ዞን ጊዳ አያና ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም በዓሉ በተለመደው ድባብ እንዲከበር ጥረቶች ብኖሩም የጸጥታ ይዞታው አሁንም እንቅልፍ የሚሰጥ አልሆነም ባይ ናቸው፡፡ “የጸጥታ ይዞታው ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ አሁን አንገር ጉቲን ዲቾ በሚባል ስፍራ አልፎ ወደ ነቀምቴ መሄድ አስቸጋሪነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡ በአከባቢያችን ግን አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ እናም በቻልነው መጠን በዓሉን ኮርማ በመጣል እያከበርነው ነው” ይላሉ፡፡
ሌላው አስተያየታቸውን የተቀበልነው ነዋሪ ከምእራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ነው፡፡ ይህ ስፍራም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግጭት አለመረጋጋቱ ከሚታመሱ አከባቢዎች ተጠቃሽ ነው፡፡ “ለወትሮም በኛ አከባቢ በደማቁ ከሚከበሩ አበይት በኣላት ዘመን መለወጫ አንዱ ነው፡፡ አሁን ግን እንደ ሁል ጊዜው ከሩቅ እየተገናኘን የምናከብረው አይደለም፡፡ እዚሁ በቅርባችን ካሉ ጎረቤት ጋር ዶሮው ምኑ እያዘጋጀን እያከበርን ነው፡፡ የኑሮ ውድነቱ ሌላው ፈታኝ ጉዳይ በመሆኑ ጭንቀት ግን አለ” ብለዋል፡፡

የመሬት ናዳ በዶዶላ
የመሬት ናዳ በዶዶላምስል Dodola communication

ሰሜን ሸዋ (ሰላሌ)

ከሰሞኑ ከባለፈው ሳምንት ሃሙስ ጀምሮ የስልክ አገልግሎት ተቋርጦበት የነበረው የሰሜን ሸዋ (ሰላሌ) ዞን በበዓሉ ዋዜማው ትናንት ከሰኣቱን የስልክ አገልግሎቱ ተመልሶላቸው በዓሉን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው ብለናቸዋል፡፡ አንድ አስተያየታቸውን የሰጡን የደብረጽጌ ነዋሪ፤ “በኛ አከባቢ ያው ወከባ ነበር፡፡ ሰው ማገት መዝረፍ ስለነበር እንዴት እናድር ይሆን የሚል ሰቀቀን ይበዛል፡፡ ከበፊቱ አሁን የተሸለ ይመስላል ሰው ሰላም ከሆነልን በዓሉ ጥሩ ነው” ይላሉ፡፡
አስተያየት ሰጪያችን የኑሮ ውድነቱ ነገር አይነገርም በማለት ከሁሉም በላይ ግን የሚያሳስበው የሰላም ነገር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ “ሰው እንኳ ለበዓል ማክበር ለሳሙና መግዣ ያጣ ነው ያለው፤ በዚሁ ባለው ግጭት የተነሳ፡፡ ሰው እንደአቅሙ በቆሎም ብዋል ምንም አይደለም፤ ዋናው ሰላም ነው” ብለዋልም፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ በአዲሱ ዓመት ተስፋ እና ምኞታቸውንም ገልጸው አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡  


ሥዩም ጌቱ
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ