1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኦሮሚያ በጸጥታ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሟል ስለመባሉ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2015

ባለፈው እሁድ ጥቅምት 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን በኬ ኦፉ ቀበሌ በደረሰ የአየር ጥቃት ከ60 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለው ከ100 በላይ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገለጡ። አስተያት ሰጪዎቹ በእለቱ ጥቃቱ የተፈጸመው ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ላይ ሕዝብ በተሰባሰበበት ነበር ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4IffZ
Äthiopien | Oromiya Region
ምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

68 ሰዎች ሲሞቱ 106 መቁሰላቸውን የዐይን እማኝ ተናግረዋል

ባለፈው እሁድ ጥቅምት 13 ቀን፣ 2015 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን በኬ ኦፉ ቀበሌ በደረሰ የአየር ጥቃት ከ60 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለው ከ100 በላይ መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ገለጡ። አስተያት ሰጪዎቹ በእለቱ ጥቃቱ የተፈጸመው ከቀኑ 5፡00 ሰዓት ላይ ሕዝብ በተሰባሰበበት ነበር ብለዋል። የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በበኩሉ “የመንግስትና በመንግስት በሚደገፉ ኃይሎች” ያሏቸው ኃይላት በኦሮሚያ ክልል የሚፈጽሙ የንፁሃን ዜጎችን ግድያ እንዲያቆሙ ሲል ጠይቋል። 

“እሁድ እለት ህብረተሰቡ ፈተና የሆነበት የሰላም እጦት እና በልማቱ ላይ ለመምከር በአከባቢው ሽማግሌዎች ልንወያይ ተሰባስበው ነበር፡፡ ከወላጆቻቸው ጋር ከመጡ ህጻናት እስከ አዛውንቶች ከ600 በላይ የሚገመቱ ነዋሪዎች ተሰባስበዋል፡፡ ከቀኑ 5፡00 ሰዓት አከባቢ ከየት መጣ ሳይባል ድሮን ቦምብ ስጥል ነው የተመለከትነው፡፡ በዚህም በርካቶች ሲሞቱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ቆስለዋል፡፡”

ይህን አስተያየት የሰጡን በምእራብ ሸዋ ዞን የጮቢ ወረዳ በኬ ኦፉ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ እንደ ነዋሪው አስተያየት የድሮን ጥቃቱ የተፈጸመው በወረዳው ቃሌ በምትባል አከባቢ ህብረተሰቡ ለውይይት ተሰባስበው በነበሩበት ነው፡፡ አስተያየት ሰጪው አክለውም ህብረተሰቡን ለውይይት ያሰባሰበውን ጉዳይም ሲያስረዱ፡ “አሁን ላይ ህዝባችን ወደ ገበያ እንኳን ሄዶ መገበያየት አይችልም፡፡ ትምህርት እንደሆነም ከተቋረጠ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ቀበሌ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ስለምንቀሳቀስ ህብረተሰቡ ወደ ገቢያ እንኳ ቢወጣ ሸነን ሸሽጋችኋል በሚል ከባድ ወከባ እና እስር ነው የሚጠብቀን፡፡ ከሶስት ዓመታት ወዲህ እርጉዝ እናቶችም ለጤናቸው ወደ ህክምና የመሄድ እድል የላቸውም፡፡ ከዚህ በፊት ወደ ከተማ ሄደው ቀንስራም ሰርተው ኑሮያቸውን የሚመሩም አሁን ከዚህ ንቅንቅ ማለት ባለመቻላቸው ኑሮ ጠቦባቸዋል፡፡ ህብረተሰቡን ያሰባሰበውም ይህን ሁሉ ችግሮቻችንን እንዴት እንፍታ በሚል ለመወያየት ነበር፡፡ በዚሁ ሳለን ነበር እንግዲህ ከአየር በመጣ የድሮን ጥቃት 68 ሰዎች ወዲያው የሞቱት፡፡ በዐይነ አይቼ የቆጠርኩኝ ቁስለኞች ደግሞ 106 ናቸው” ብለዋል።

Äthiopien | Oromiya Region
ጎጆ ቤቶች በኦሮሚያ ክልል ገጠራማ ሥፍራምስል Fischer/Bildagentur-online/picture alliance

አስተያየት ሰጪው በዚህች የጮቢ ወረዳ በኬ ኦፉ ቀበሌ የመንግስት አገልግሎትም ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱበታል በሚል ከተቋረጠ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡ ከወረዳው ወደዚህች ቀበሌ የሚመጣ አመራር አለመኖሩንም በአስተያየታቸው አንስተዋል፡፡ ከዚህ በፊት ከታጣቂዎች ታብራላችሁ የሚል ማስፈራሪያ ግን እንደሚደተርሳቸው የሚገልጹት እኚው አስተያየት ሰጪ በእሁዱ ጥቃት ከ8 ዓመት ታዳጊ እስከ 75 ኣመት አዛውንት ከሟቾች ውስጥ እንደሚገኙም ነው ያስረዱት፡፡

ገመቹ አቶምሳ ደግሞ የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ እና በእሁዱ ጥቃት የ14 ዓመት ታዳጊ ልጃቸውን በሞት የተነጠቁ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡ “ከአየር የተተኮሰው ጥይት በዚህ ግራ ትከሻዋን አግኝቶ ነው ወደ ህክምናም ሳንወስዳት ወዲያው ያለፈችው፡፡ በእርግጥ ህክምናም እንውሰድ ብንል መንገድ ስለተዘጋብን ማለፊያም አይኖረንም” ብለዋል፡፡ 
የዚሁ አከባቢ ነዋሪ መሆናቸውን የሚገልጹት ጫላ አያኖ ደግሞ በእለቱ መጠነኛ የመቁሰል አደጋን እንዳስተናገዱ ነው ያስረዱን፡፡ “እኔ 65 ዓመቴ ነው፡፡ በዚያ ስብሰባ ላይ ተሳትፌ ነበር፡፡ እኔ እንኳ መጠነኛ ቁስል ነው እጄ ላይ የደረሰው፡፡”

እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች የድሮን ጥቃቱ ትናንት ሰኞም ቀጥሎ በአከባቢው ያለ ትምህርት ቤት መምታቱን ነው በአስተያታቸው ያነሱት፡፡ ከዚሁ የተነሳ ተጨማሪ ጥቃት ፍራቻ ተሰባስበው ሟቾችንም ለመቅበር እንኳ እንዳዳገታቸውም ነው የገለፁት፡፡ በኦሮሚያ በስፋት የሚንቀሳቀሰውና ከዋነኛ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች የሆነው የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ይህ የጮቢውን ጥቃት ጨምሮ በኦሮሚያ በተለያዩ አከባቢዎች በሰላማዊ (ሲቪል) ዜጎች ላይ ይፈጸማል ያለውን ጥቃት በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል፡፡ 

ኦፌኮ በመግለጫው መንግስትን የፖለቲካ ቀውስ መፍታት ባለመቻል ከሶ፤ የመንግስት ታጣቂዎችን ንፁሃንን በመግደል፣ ቤትና እህል በማቃጠል እና ‘ዘግናኝ’ ባለው የማፈናቀል ተግባር ወንጅሏል፡፡ “በተለያዩ አቅጣጫዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጥቃት በርትቷል” ያለው ኦፌኮ  በጥቅምት ወር የመጀመሪያ 14 ቀናት ውስጥ ብቻ በድምሩ ከ120 በላይ ንፁሃን ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል ሲልም በመግለጫው አትቷል። በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ እና ሳሲጋ ወረዳዎች ጥቅምት 05 እና 09 2015 ዓ.ም. 38 ንጹሃን በመንግስት ይደገፋሉ ባለው ፋኖ መገደላቸውንም ኦፌኮ በዚሁ መግለጫው አንስቷል፡፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን ሜታ ወልቂጤ ወረዳ በምትገኘው ቀሬ ሄጦ ቀበሌ በመንግስት ኃይሎች በተፈፀመ የድሮን ጥቃት 14 ንፁሃን ዜጎች ሲገደሉ፤ በምስራቅ ወለጋ ዞን ዋማ አገሎ ወረዳ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ተመሳሳይ ጥቃቶች መፈፀማቸውንም ፓርቲው ጠቃቅሷል፡፡ “እሁድ ጥቅምት 13 ቀን 2015 ዓ.ም. በምዕራብ ሸዋ ዞን ጮቢ ወረዳ በኬ ኦፉ በተባለ ቀበሌ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ በመንግሰት ኃይሎች በድሮን በተፈፀመ ጥቃት የ7 እና 10 አመት እድሜ ያላቸው ህፃናት፣ አራስ እናቶች፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞችን ጨምሮ 38 ንፁሃን ተገድለዋል” ብሏልም ኦፌኮ በመግለጫው። 

Äthiopien | Oromiya Region
ኦሮሚያ ክልል የገጠር ጎጆ ቤቶች ከፊት ሦስት ሰዎች እየኼዱምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

ፓርቲው በኦሮሞ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ የአለምአቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብና ትኩረት እንዲሰጠው፣ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት፣ ጉዳዩ በገለልተኛ አካላት እንዲጣሩና አጥፊዎች እንዲቀጡ እና በእርስ በርስ ጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ ኃይሎች በሙሉ የሰላማዊ ዜጎችን ህይወት እየቀጠፈ ካለው እንቅስቃሴ በመታቀብ ወደ ድርድርና እርቅ መድረክ እንዲመለሱ እጠይቃለሁ ብሏል።

የነዋሪዎች አስተያየት እና የኦፌኮ መግለጫ ላይ ከአከባቢው ባለስልጣናት እንዲሁም ከኦሮሚያ እና ከፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ምላሽና ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ግን ባለስልጣናቱ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው እና የጽሁፍ መልእክት ባለመመለሳቸው አልተሳካም፡፡

ሥዩም ጌቱ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ