1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራት

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2016

በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ማለትም በነሃሴ እና መስከረም ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠነቀቀ፡፡ ደራሽ ጎርፍ በሚያስቸግራቸው የተፋሰስ አከባቢዎች የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4jB2T
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራት
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራትምስል Hanna Demisse/DW

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራት
በቀሪዎቹ የክረምት ወራት ማለትም በነሃሴ እና መስከረም ወራት ከመደበኛ በላይ ዝናብ ስለሚኖር አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ሲል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስጠነቀቀ፡፡
የብሔራዊ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ እንዳሉት ደራሽ ጎርፍ በሚያስቸግራቸው የተፋሰስ አከባቢዎች እና የክረምት ወራቱ አስቀድሞ በገባባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች የመሬት መንሸራተትን ሊያስከትል ስለሚችል አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡

ባለፉት ሁለት የክረምት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠባቂ በሆኑባቸው የአገሪቱ አከባቢዎች ላይ ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠንና ስርጭት እንደነበር፤ ይህም አስቀድሞ መተንበዩን ያስታወሱት የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በዓለም ሜቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት አቶ ፈጠነ ተሾመ፤ ባለፉት ሁለት ወራት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አከባቢዎች በሰኔ እና ሃምሌ ወራት በ24 ሰዓት ውስጥ ከ30-118 ሚ.ሜ. ዝናብ መመዝገቡን አስረድተዋል፡፡  


ከፍተኛ የክረምት ዝናብ የሚጠበቅባቸው አከባቢዎች
እንደ ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አበባ፣ ሀረርና ድሬዳዋ እንዲሁም ሰሜን ሶማሊ ባሉ የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አከባቢዎቹ የነበረው ከመደበኛ በላይ ዝናብ ለግብርናውና የተፋሰስ ውሃን በማሻሻሉ ረገድ አዎንታዊ ሚና ነበራቸው ተብሏል፡፡ በቀጣይ ነሃሴ እና መስከረም ወራትም የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ አከባቢዎች በተሻለ ጥንካሬ እንደሚቀጥል  ነው የተተነበየው፡፡ ለዚህም በክረምቱ አንዱ ሊሰራበት የሚገባው ነገር የጎርፍ መከላከል ስራን በተለይም በተፋሰሶች የታችኛው መዳረሻ መስራት ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ “የክረምት ዝናብ በሚበዛባቸው አከባቢዎች አንዱ ሊወሰድ የሚገባው አንዱ እርምጃ የጎርፍ መከላከል ስራን መስራት ነው” ያሉት አቶ ፈጠነ በተለያዩ ተፋሰሶች ስራዎች እንዲሰሩ የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ባሉበት ትንቢያዎች ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራት
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ዝናብ የሚጠበቅባቸው ቀጣይ ሁለት ወራትምስል Hanna Demisse/DW


የክረምቱ ዝናብ አዎንታዊና አሉታዊ ተጽእኖው
የክረምት ዝናቡ የግብርና ስራዎችን የሰመረ ለማድረግ እና የውሃ ሃብት አያያዝን ለማሻሻል ጉልህ ሚና እንዳለውም የተነገረ ሲሆን፤ በአሉታዊነት የሚታዩ የአፈር መሸርሸር፣ ምርት ላይ የውሃ መተኛት፣ ከእርጥበት መብዛት ጋር የሚነሱ የተለያዩ የሰብሎች በሽታዎች፣ ቅጽበታዊ ጎርፍ የሚያጠቃቸው አከባቢዎች፣ በወንዝ ዳርቻ በሚገኙ መንደሮች ላይ የወንዝ ሙላት አደጋ እንዳያስከትል ብሎም በወባ ተጋላጭ አከባቢዎች ለወባ ትንኝ መፈጠርና ማደግ አመቺ ሁኔታ እንዳይፈጠር፤ በአጠቃላይም ከሚኖረው ተደጋጋሚ ከባድ ዝናብ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ልከሰቱ የሚችሉትን አሉታዊ ተጽእኖዎች ለመቀነስ የጥንቃቄ ስራዎች እንዲሰሩም ተጠይቋል፡፡ “የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎችን እንደ ግብዓት በመውሰድ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ በምኖርበት ከተሞች አከባቢ የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓቶች ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ያሉት የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር በወንዝ ዳርቻ አከባቢዎች ያሉትን ማህበረሰብ በማንሳት በወንዝ ዳርቻ ልማት እልባት መስጠት በጎ ጅማሮ ተደርጎ ልወሰድ የሚገባ ብለውታልም፡፡


በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ሦስት ወረዳዎች፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ወላታ ዞን ብሎም በሲዳማ እና አማራ ክልል ወሎ ከወዲሁ የመሬት መንሸራተት ማጋጠሙም ተነስቶ በመሰል የመሬት መንሸራተት ስጋት ባለባቸው አከባቢዎች በቀጣይ የሚኖረው ከፍተኛ የዝናብ መጠን ተጨማሪ የአደጋው መንስኤ ሊሆን እንደምችልም ተጠቁሟል፡፡ “ከፍተኛ መጠን ያለው ዝናብ አስቀድሞ ለወራት ስዘንብባቸው የነበሩ አከባቢዎች ከሚፈለገው በላይ እርጥበት ስለምይዙ ለመሬት መንሸራተት ይጋለጣሉ” ተብሏልም፡፡  

ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ