1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ እያሻቀበ የመጣው የስደተኞች ቁጥርና አሳሳቢ ይዞታው

ሐሙስ፣ ኅዳር 6 2016

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች የሚያስፈልጓቸውን አገልግሎቶች ለማግኘት እንቅፋት የሆኑ ችግሮች መኖራቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ። በአብዛኛዎቹ ቦታዎች ምዝገባ መቆሙን እና የስደተኝነት ሁኔታ አወሳሰን እየተሰራ አለመሆኑን የስደተኞች፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብት የሥራ ክፍል ኃላፊ እንጉዳይ መስቀሌ ተናግረዋል

https://p.dw.com/p/4YuQc
Äthiopien Gambella Flüchtlingscamp
ምስል Reuters/D. Lewis

በኢትዮጵያ እያሻቀበ የመጣው የስደተኞች ቁጥርና አሳሳቢ ይዞታው

ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች በማስተናገድ ስማቸው በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አገራት ትጠቀሳለች፡፡ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሱዳን የከፋው የእርስ በርስ ጦርነት አስቀድሞም ከደቡብ ሱዳን፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የሚፈልሱትን በርካታ ስደተኞች ለምትቀበል አገር ሌላው እራስ ምታት ሆኖ ተስተውሏል፡

የዓለማቀፍ ረጂ ድርጅቶች መረጃዎች እንደሚጦቁሙትም ባሁን ወቅት በኢትዮጵያ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች አሉ፡፡ ከተለያዩ ጎረቤት አገራት ስደተኞችን ለምትቀበል ኢትዮጵያ  በተለይም በቅርቡ በሱዳን የተቀሰቀሰው የእርስበርስ ጦርነት በኢትዮጵያ የስደተኞችን ቁጥር ከፍ ለማለቱ ሌላው ሰበብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ ከስደተኞች የሚመጡ ቅሬታዎችን መነሻ በማድረግ በስደተኞች አሁናዊ ይዞታ ዙሪያ አደረኩ ባለው ምልከታ አሳሳቢ ያላቸው በርካታ ክፍተቶችን መመልከቱን አውስቷል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ ያጋሩት በኮሚሽኑ የስደተኞች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብቶች የስራ ክፍል ኃላፊ እንጉዳይ መስቀሌ በርካታ ከጎረቤት ሶማሊያ ፈልሰው ሶማሊ ክልል የተጠለሉትን፣ ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ክልል እና ከሱዳን ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የመጡ ስደተኞችን ጨምሮ በተለያዩ አከባቢዎች የስደተኞች ሁኔታን ለመመልከት ክትትሎች መደረጋቸውን አመልክተዋል፡፡

የስደተኞች ምዝገባ መቆም

ኮሚሽኑ በስደተኞች መጠለያ እና ልየታ ጣቢያዎቹ ተዟዙሮ አደረኩ ባለው በዚሁ ምልከታው አሳሳቢው የስደተኞች ጥበቃ ብሎ ከለያቸው አንደኛውና ዋነኛው ከስደተኞች ምዝገባ ጋር የሚያያዝ የመብት ጉዳይ ነው፡፡ በኮሚሽኑ የስደተኞች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብቶች የስራ ክፍል ኃላፊዋ እንጉዳይ መስቀሌ፤ “ስደተኝነትን የመጠየቅ መብት አንዱ መሰረታዊ ችግር ነው” ይላሉ፡፡ “በርግጥ በቅርቡ አንዳንድ ቦታዎች መሻሻሎች አሉ” የሚሉት የስራ ኃላፊዋ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአማራ ክልል በኩል ተደረገውን የሱዳን ስደተኞች የመቀበል ስራን በምሳሌነት አንስተዋል። 

ወደ ጋምቤላ የሚሰደዱ ደቡብ ሱዳናዉያን ቁጥር እየጨመረ ነዉ ተባለ

ይሁንና የስደተኞች የምዝገባ ሂደት አብዛኛው ቦታ ላይ መቆሙ በተለይም ደግሞ የስደተኝነት አወሳሰን (Refugee Status Determination) እየተሰራ አለመሆኑ የስደተኞችን መታወቂያ የማግኘት እና የመታወቃቸው ጊዜ ሲያበቃም የማሳደስ ስራንም ጭምር ፈታኝ አድርጎታል፡፡ ይህ በመሆኑም ስደተኞች ተገቢውን አገልግሎት ለማግኘት ሲቸገሩ ተስተውለዋል ተብሏል፡፡ በ2015 ዓ.ም. ግንቦትና ሰኔ ወራት መጨረሻዎች አከባቢ ጀምሮ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን ተከትሎ ለእስራት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በርካታ ነው ተብሏል።

የዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት የስደተኞች ምግብ ድጋፍ ማቆም የደቀነው አደጋ

በኢትዮጵያ ከስደተኞች አያያዝ ጋር ተያይዞ የተስተዋለው ሌላው ትልቁ ችግር የሰብኣዊ ድጋፍ አቅርቦት እጥረት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ “ከስደተኞች ሰብዓዊ አያያዝ ጋር ተያይዞ ሌላኛው ያስተዋልነው ክፍተት ከግንቦት ወር ጀምሮ በአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት (USAID) እና በዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) የምግብ ድጋፍ መቆሙ ነው” ሲሉም ሌላኛውን አሳሳቢ ያሉት ስደተኞች ላይ የወደቀውን አደጋ አስረድተዋልም በኢሰሞ የስደተኞች ጉዳይ ኃላፊዋ ወ/ሪት እንጉዳይ፡፡

እንደ ኃላፊዋ ማበብራሪያ ይህ ለስደተኞች የሚቀርበውን የምግብ ድጋፍ ማቋረጥ ስደተኞቹን ለከፍተኛ አደጋ የሚዳርግ ነው፡፡ “ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ከካምፖች በመውጣት ተቀባይ ማህበረሰብ ማሳዎች ውስጥ በመግባት ስደተኞች እህል በማግኘት ህይትን ለማቆየት በሚደረጉ ጥረቶች ግጭቶች ደጋግሞ ተፈጥረዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር አንዳንድ የስደተኞች መጠለያ ውስጥ ባጋጠመው የምግብ አቅርቦት እጥረት ለሞትም ጭምር የተዳረጉ ስደተኞች ነበሩ” በማለት የችግሩን አሳሳቢነት ዘርዝረዋልም፡፡ በመሆኑም በረጂ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የምግብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ መቋረጡ በተለይም ስደተኛው ማህበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩም ተነግሯል፡፡

ደቡብ ሱዳናውያን ሕጻናት ስደተኞች በኢትዮጵያ
በጋምቤላ ክልል የሚገኙ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የሰብዓዊ እርዳታ ሲቋረጥ ምግብ ለማግኘት በሚያደርጉት ጥረት ለአደጋ ተጋልጠዋል። ምስል DW/Fanny Facsar

ባጠቃላይ ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው ድጋፍ ውስንነት ያለው ስለመሆኑም ኢሰመኮ በምልከታው ታዝቧል፡፡ ኮሚሽኑ በቅርቡ አረጋገጥኩ ባለው ምልከታው ከዚህ ቀደም ለስደተኞች በተናጥለል ይሰጥ የነበረው 13 ኪ.ግ. እህል ወደ 10 ኪ.ግ. መውረዱን በምሳሌነት አንስቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት የዓለማቀፉ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ጭምር ያሳተፈ ምክክር ስለማድረጉም ተነግሯል፡፡

የረጂ ድርጅቶች በኢትዮጵያ የተቋረጠውን ድጋፍ ለስደተኞች ማስቀጠል

የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) በኢትዮጵያ ለሚገኙ 900 ሺህ ገደማ ስደተኞች የሚያደርገውን ድጋፍ ዳግም ለማስቀጠል መወሰኑን ባሳለፍነው ጥቅምት ወር መጀመሪያ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ በኢትዮጵያ የድጋፍ ቁሳቁሶች ለታለመለት ትክክለኛ ዓላማ አለመዋሉን ተቃውሞ ድጋፉን አቋርጦት የነበረው ተቋሙ፤ ድጋፉን ለመቀጠል የወሰነው ህይወታቸው አደጋ ላይ እየወደቀ መሆኑን ተገነዘብኩ ያሏቸውን ስደተኞች ከአደጋ ለማትረፍ ነው፡፡ WFP በኢትዮጵያ ስደተኛ ካምፕ የሚገኙ ሰዎች የርሃብ ሁኔታ ተባብሶ ድንበር አከባቢዎች ላይ ደህንነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሚንቀሳቀሱ ስደተኞች መስተዋላቸውን ተከትሎ አዲስ አሰራር በመዘርጋት ድጋፍ ለመቀጠል መወሰኑንም ነበር ያሳወቀው፡፡  በተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ አደጋ 23 ሚሊየን ገደማ ዜጎች ለአደጋ ተጋልጠው ድጋፍ በሚሹባት ኢትዮጵያ ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለወራት ያቋረጠውን ድጋፍ ለመቀጠል ሲወስን ግን ድጋፉ የአገር ውስጥ ተፈናቃይን እንደማይመለከት በወቅቱ አሳዉቋል።

ኢትዮጵያ ለሠፈሩ ስደተኞች ርዳታ

ተቋሙ በጥቅምት ወር መጀመሪያ በፅሁፍ ባወጣው መግለጫ “ከአጋሮቻችን ጋር ሆነን ምግብን አብዝቶ ለሚፈልጉ ለማድረስ በየሰዓቱ ያለመታከት እንስራለን” ነበር ያለው “ምግብ በአስጊ ሁኔታ ውስጥ ያሉትን ስደተኞች ህይወት ለመቀጠል ወሳን በመሆኑ ድጋፉን የማስቀጠል ውሳኔ ላይ ደርሰናል” በማለትም ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ስደተኞች ለመድረስ ቁርጠኝነቱን አሳውቋል፡፡

የረጂ ተቋማት ስደተኞችን ለመርዳት መወሰን እስካሁን ምን አመጣ?

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የስደተኞች፣ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች እና ፍልሰተኞች መብት ዳይሬክተሯ እንጉዳይ መስቀሌ የዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ቢያንስ ለስደተኞች የምግብ ድጋፍ የማቅረብ ውሳኔ ላይ መድረስ “መልካም ዜና” ብለውታል፡፡

የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ በትግራይ
በኢትዮጵያ የኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በርካታ ስደተኞች ይገኛሉምስል Million Haileselassie /DW

ኃላፊዋ አስከፊውን የስደተኞች ህይወት ሲያስረዱም፤ በቅርብ ጊዜ የባምባሲ፣ ሸርቆዬ እና ጾሬ-ኩርሙክ መጠለያ ጣቢያ ብሎም የአብራሞ ማጣሪያ ጣቢያ ውስጥ ኮሚሽናቸው ባደረገው ክትትል ላለፉት አምስት ወራት ምንም አይነት የምግብ ድጋፍ አለማግኘታቸውን መገንዘቡን አስረድተዋል፡፡ እነዚህ ስደተኞች አብዛኞቹ ከሱዳን የመጡ ናቸውም ተብሏል፡፡ ለነዚህ ተፈናቃዮች ደግሞ በቂ የመጠለያ ጣቢያም አልተዘጋጀም፡፡ እንደ የዓለማቀፉ ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) መረጃ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብቻ 80 ሺህ ገደማ ስደተኞች ሲኖሩ፤ ከነዚህ ውስጥ 16 ሺህ ያህሉ ተገን ጠያቂ ናቸው፡፡

በተለይም የሱዳን ግጭትን ተከትሎ በቤኒሻንጉል ክልል በኩል የመጣው ከፍተኛ የስደተኞች ጫና አሳሳቢነቱም እየጎላ ነው፡፡ አስቀድሞም ከፍተኛ የስደተኞች እና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በበዛበት አከባቢ ሌላ ስደተኞች የመሸከም ጫንቃው ያሳስባል፡፡ “ለምሳሌ ጾሬ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ 44 ሺህ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ነበሩ፡፡ በዚህ ላይ የሱዳን ስደተኞች ተጨምሯል፡፡ ለነሱ ተብሎ የተዘጋጀ መጠለያ አለመኖሩ ደግሞ ከተቀባይ ማህበረሰብ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ አስገድዷል፡፡ ይህ ደግሞ ሄዶ ሄዶ የጸጥታ ችግር ይፈጥራል” የኢሰመኮ ስደተኖች ጉዳይ ሃላፊ ያብራሩት ነው።

የዓለም ምግብ ድርጅት ርዳታ ኢትዮጵያ ለሰፈሩ ስደተኞች

የስደተኞች ቁጥር በሚጨምረው ልክ የዓለማቀፉ ድጋፍ አለመጨመሩ ግን ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ “በረድኤት ድርጅቶች የሚቀርበው ድጋፍ የስደተኞቹን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ አይደልም” ይላሉ ወ/ሪት እንጉዳይ፡፡ በቅርቡ በዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው ድጋፍ እንዲቀጥል ብወሰንም እስካሁን ግን ለስደተኞቹ ያመጣው ነገር የለም ተብሏልም፡፡ በአማራ ክልል የተወሳሰበው የጸጥታ ችግር ደግሞ በተለይም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ድጋፍ ለማጓጓዝ የሚደረገውን ጥረት ፈትኗል፡፡ “በምዕራብ ኦሮሚያ የታጠቁ ቡድኖች በመንቀሳቀሳቸው ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የእርዳ ምግብ የሚጓጓዘው በአማራ ክልል በኩል ነበር፡፡ አሁን ግን ከዓለም ምግብ ድርጅትም እንደተገለጸው አንድ ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ እርዳታ ተጭኖ ከባህርዳር ማለፍ ባለመቻሉ በቤኒሻንጉል ያሉ ስደተኞች ህይወት አደጋ ውስጥ ነው” ሲሉም እንጉዳይ መስቀሌ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ቃል አቀባዩ አቶ አታለል አቦሃይ ከዚህ በፊት ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የረጂ ተቋማት ድጋፍ ማቆም በመንግስት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል፡፡ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝት የነበራቸው የዓልም ፍልሰተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ኤሚ ፖፕ በበኩላቸው የዓለማቀፍ ረጂ ተቋማት ድጋፋቸውን በኢትዮጵያ ማቋረጥ በተቋማቸውም ላይ ጉሊህ የሆነ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳርፍ ብለውት እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ