በኢትዮጵያ ሥጋት የደቀነዉ የበረሃ አንበጣ
ማክሰኞ፣ ጥር 26 2012ማስታወቂያ
መቀመጫውን አዲስ አበባ ካደረገው የምስራቅ አፍሪቃ የበረሃ አንበጣ መከላከያ ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው በምስራቅ አፍሪቃ ሦስት የአንበጣ አይነቶች ይገኛሉ። እነዚህም የበረሃ ፣ የአፍሪቃ ተዛማጅ እና የዛፍ የሚል መጠርያ አላቸዉ።
አሁን ላይ በቀጣናው የተከሰተው የበረሃ አንበጣ ሲሆን በኢትዮጵያም ከ ሰኔ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተከስቷል። መንጋው ከሶማሊያ በአምስት አቅጣጫ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወደ ኬንያ ሸሽቶ የነበረው ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሳ ሲሆን ይህም ስጋቱን የበለጠ እንዳናረውና በቀጣይም ለአንበጣው መዛመት ምቹ የአየር ንብረት የሚያገኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገልፆአል።
የመከላከል ስራው ከባህላዊ ባሻገር ከውጪ በክራይ በገቡ ሦስት አውሮፕላኖች የኬሚካል ርጭት እየተደረገ ነው። ያም ሆኖ የአንበጣው መንጋ የሚያርፍባቸው አካባቢዎች ተራራማና በረሃማ በመሆናቸው ስራውን ማክበዱን ነው ለማወቅ የተቻለው።
የአንበጣው መንጋ እስካሁን ያደረሰው የጉዳት መጠን በሁለት አቅጣጫ መጠናቱንና ውጤቱም በሂደት ይገለጻል ተብሏል። ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እዚያው ከተማው ላይ የተፈለፈለና ያደገ ሳይሆን ከኬሚካል ርጭት ያመለጠ እና ይህን ያህል ስጋት ዉስጥ የሚከት አይደለም ተብሏ።
ሰለሞን ሙጬ
አዜብ ታደሰ