በኢትዮጵያ ሙዚቃ ጉልኅ አሻራ ያሳረፈው ሙሉቀን መለሰ አረፈ
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 2 2016ጊዜ በማይሽራቸው የሙዚቃ ሥራወቹ የሚታወቀው ሙሉቀን መለሰ በትናንትናው እለት ጠዋት የረጅም ጊዜ የጤና ክትትል ሲያደርግ ቆይቶ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ሙሉቀን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ጉልህ አሻራቸውን ካሳረፉ ጥቂት ድምፃውያን ውስጥ አንዱ ነበር ። ለረጅም ዓመታትም ከሙዚቃ ዓለም ወጥቶ በመንፈሳዊነትና በዘማሪነት ሕይወቱን መርቷል ። የሙሉቀን መለሰ ሥራዓተ ቀብር ከነገ በስትያ ዓርብ እንደሚፈጸም ታውቋል ።
ጊዜና ሁነት የማይሽራቸው፣ የማያረጁ፣ የማይሰለቹ ፤ በያንዳንዳችን ልቦና ውስጥ ዘልቀው የቀሩ ፣ ድንቅ ሥራወችን አበርክቶልናል። በሃገራችን ሙዚቃ ውስጥ የማይፋቅ አሻራቸውን ካስቀመጡ ጥቂት ድንቅ ድምጻውያን ውስጥም አንዱ ነው። በትላንትናው እለት የረጅም ጊዜ ህክምና ሲከታተል ቆይቶ ከዚህ አለም ድካም አርፏል።
ባለቤቱ ወ/ሮ ሙሉ ካይፓግያን ሙሉቀን መለሰ በጣም መልካም እና ቅን፣ ሰወችን የሚወድ፣ እግዛብሄርን የሚፈራ ሰው እንደነበረ ይናገራሉ።
ከሦስት ዐሥርተ ዓመታት በላይ ኑሮውን አሜሪካ ያደረገው ሙሉቀን ገና በ13 አመት እድሜው፣ በ1958 ዓ/ም ፈጣን ኦርኬስትራን ተቀላቅሎ ሙዚቃን ሕይወቴ ብሎ ጀምሯል። የኪነጥበብ ባለሞያወችን የሕይወት ታሪክ በመሰነድና በመዘከር የሚታወቀው ተወልደ በየነ የሙሉቀን የሙዚቃ ጅማሮ ከሱ ቀደም የነበሩትን አንጋፋወች ዱካ ተከትሎ መሆኑን ይናገራል። የእነ ጥላሁንን ፈለግ ይዞ የሙዚቃ ሕይወቱን የጀመረው ሙሉቀን፣ ከ1960 ጀምሮ በፖሊስ ኦርኬስትራ፣ ከ1972 ዓ/ም ጀምሮ ደግሞ ዳህላክ ባንድን ተቀላቅሎ ተወዳጅ ዜማወቹን ሲያበረክትልን ቆይቷል።
ተወልደ በየነ እንደሚለው ሙሉቀን ከጊዜ በኋላ የራሱን የሙዚቃ ስበዕና ለይቶ አውቆ አሻራውን በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ማስቀመጥ የቻለ ድንቅ ድምጻዊ ነው።
የሙሉቀንን ሙዚቃውች በማቀናበር አብሮት በርካታ ስራወችን የሰራው፣ የጃዝ ሙዚቃው ንጉስ አርቲስት ሙላቱ አስታጥቄ ሙሉቀን መለሰ በሙዚቃ ክህሎቱና ለሙዚቃው ማደግ ባበረከተው አስተዋጾ ከሚያደንቃቸው ጥቂት ድምጻያን አንዱ መሆኑን ተናግሯል።
ከ1980ወቹ ዓመታት ወዲህ ሙሉቀን መለሰ የሙዚቃውን ዓለም ደህና ሰንብች ብሎ ወደ መንፈሳዊ ሕይወት ተቀላቅሏል። በዚህ ዘመኑም የዝማሬ ስራወቹን ያቀረበ ሲሆን በተለያዩ መንፈሳዊ ዝግጅቶችም ላይ ያገለግል ነበር።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሙሉቀን በአብዛኛው ከወዳጅ ጓደኞቹ ተነጥሎ የብቸኝነት ሕይወትን እንዳሳለፈ ይነገራል። ባለቤቱ ወ/ሮ ሙሉ ግን ይሄ የሆነው ለመረጠው መንፈሳዊ ሕይወት ራሱን አሳልፎ መስጠትን ስለመረጠ ነው ብለዋል።
ሙሉቀን መለሰን ለመሸኘት ከዛሬ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ቤተሰብን የማጽናናት፣ የጸሎትና የስንብት ስነስራዓት የሚከናወን ሲሆን፣ ስራዓተ ቀብሩም አርብ እንደሚፈጸም የወጣው መርሃግብር ያስረዳል።
አበበ ፈለቀ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ