1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ሊካሔድ በታቀደው አገራዊ ምክክር የሲቪክ ማኅበራት ሚና ምን ይሆናል?

ሐሙስ፣ ሐምሌ 28 2014

ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት አገራዊ ውይይት እንዲሰምር ሀቀኛ ሥራ እንዲከውኑ ተጠየቀ።

https://p.dw.com/p/4F8Qb
Äthiopien Addis Abeba Nationaler Dialog
ምስል Solomon Muchie/DW

ለታቀደው ሀገራዊ ምክክር የሲቪክ ማሕበራት ሚና

ሕጋዊ ሰውነት አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን የተቋቋመበት አገራዊ ውይይት እንዲሰምር ሀቀኛ ሥራ እንዲከውኑ ተጠየቀ።  4 ሺህ ገደማ በሕግ እውቅና ያላቸው የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶችን በአባልነት ያቀፈው የኢትዮጵያ ሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑን የተመለከቱ አሠራሮችን ትክክለኛነት በመከታተልና ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ የሲቪል ድርጅቶች ትልቅ ኃላፊነት ከፊታቸው ይጠብቃቸዋል ብሏል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የለም በሚልና በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ በማድረጉ ማስፈለጉ መገለፁ ይታወሳል። 

በኢትዮጵያ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች በብሔራዊ ምክክሮች ውስጥ አካታችነት፣ ታማኝነትና ገለልተኛነት እንዲኖር ምን መሠረታዊ ኃላፊነት አለባቸው የሚለውን እና ሊኖራቸው የሚችለውን እገዛ በተመለከተ ከሌሎች አገሮች ልምድ በመነሳት እስካሁን በድርጅቶቹ አቃፊ የሆነው ምክር ቤት ሦስት ጊዜ ምክክር መደረጉን ጠቅሰዋል።

11 ኮሚሽነሮችን ይዞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተቋቋመው ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን ሥራ መሳካትም ራሱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪ የሆነው የኢትዮጵያ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያቀፋቸው መሰል ድርጅቶችን ያስተባብራል ብለዋል።

የብሔራዊ ውይይቱ አካሄድ ከጅምሩ የተሳሳተ አቅጣጫ እንዳስቀመጠ ማየቱን የገለፀው የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ከዚህ ቀደም "በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከተፈለገ ከሰላማዊ ትግል ወጥተው ትጥቅ አንግበው ከመንግሥት ጋር በኃይል በመፋለም ላይ የሚገኙ ኃይሎችም በምክክር ሂደቱ እንዲሳተፉ ያስፈልጋል" ሲል መጠየቁ ይታወሳል። ምክክሩ ከፖለቲካ ሀሳብ እና ፍላጎት አራማጅ ቡድኖችና ግለሰቦች ባለፈ ሰፊውን የአገሩን ሕዝብ ማካተት አለበት የሚለውም ጎላ ብሎ የተንፀባረቀ ጥያቄ ነበር። 

በዚህ ረገድ በአገር ውስጥ በአምስት ክልሎች እና ከአገር ውጪ በአፍጋኒስታን በዜጎች መብቶች መከበር ዙሪያ እንደተሠማራ የገለፀው አማኑኤል የልማት ድርጅት የተባለው የሲቪክ ድርጅት ማሕበረሰቡ የብሔራዊ ምክክሩ ተሳታፊ እንዲሆን አግዛለሁ ብሏል። ይህን ያሉት የዚሁ ድርጅት የሥራ ኃላፊ ዶክተር ተሠማ በቀለ ናቸው።

በአዋጅ ቁጥር 1265/ 2014 ዓ.ም የተቋቋመው የዚህ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ሰብሳቢ ሆነው የተሾሙት ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከዚህ ቀደም "የሀገር ሽማግሌዎች ተደምጠው ቢሆን ኖሮ የሰሜን ኢትዮጵያው ችግር ባልደረሰ" ብለው ነበር። አክለውም " ኮሚሽኑ የተጣለበትን ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት እንዲያሳካ ከደቂቅ እስከ ልሂቅ ፣ ወጣት ፣ አዛውንት፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለብሔራዊ ምክክር እንዲዘጋጅ ያስፈልጋል"  ብለዋል።

ዶክተር ተሠማ በቀለን የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶች እውን ለዚህ ሥራ ስኬት አጋዥ ሆነው ይወጡ ይሆን ? ብለን ጠይቀናቸው "ቁርጠኝነት" ካለ ምንም ጥርጥር የለኝም ብለዋል።
ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ሕዝብ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲመክር እና መፍትሔ እንዲያፈልቅ የማመቻቸት እና የማስተባበሩን ሥራ እንደሚወጣ፣ ውሳኔ ግን የሕዝብ መሆኑ ተነግሮለታል።

የሲቪክ ማሕበረሰብ ድርጅቶችስ ለዚህ ስኬት በምን ያህል በጎ ተጽእኖ ይኖራቸው ይሆን የተባሉት አቶ ሄኖክ መለሰ ተከታዩን መልሰዋል። የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ ሳያንስ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደትን ፈታኝ አድርጎታል ትብሎ ስለታመነበት ማስፈለጉ ታምኖበት ተቋቁሟል።  በኢትዮጵያ ውስጥ "መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር" ይሠራል የሚል ተስፋም ተጥሎበታል።