1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃው ቀንድ ድርቅ ለምን ይደጋገማል?

ማክሰኞ፣ የካቲት 21 2015

ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በአፍሪቃው ቀንድ የተስተጓጎለው የዝናብ ወቅት የአካባቢው ሃገራትን ለድርቅ አጋልጧል። ዘንድሮም የበልግ የዝናብ ወቅት ተመሳሳይ የዝናብ እጥረት እንደሚኖር ከወዲሁ ትንበታያዎች ያሳያሉ። በተጠቀሰው አካባቢ ድርቅ ለምን ይደጋገማል? መፍትሄውስ?

https://p.dw.com/p/4O5Tv
Kenia Dürre l Leben im Dorf Parapul
ምስል Simon Maina/AFP

በአፍሪቃው ቀንድ ድርቅ ለምን ይደጋገማል?

የአፍሪቃ ቀንድ አካባቢ ሃገራት ባለፉት ተከታታይ ዓመታት ለድርቅ የመተጋለጣቸው ዜና ሲነገር ሰንብቷል። ይኽ የዝናብ እጥረት በዘንድሮውም የበልግ ወቅት እንደሚቀጥል የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የአየር ጠባይ ትንበያ አመላክቷል።

በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ የዝናብ ወቅቶች በቂ ዝናብ ከታጣ ዓመታት ተቆጥረዋል። በዚህም ምክንያት የተለያዩ የሶማሊያ አካባቢዎች ለድርቅ ተጋልጠው ብዙዎች በምግብ እና ውኃ እጥረት ሲቸገሩ አካባቢያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን የተመድ የረድኤት ተቋማት ሲገልጹ ከርመዋል። በተመሳሳይ ሰሜናዊ ኬንያ እና ደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያም የዝናብ መስተጓጎል በተለይ በአካባቢው በብዛት የሚኖሩትን አርብቶ አደሮች የኑሮ ሁኔታ ማናጋቱ እየታየ ነው። የዓለም የምግብ ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ድርቁ ከ20 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ሕይወት ለአደጋ አጋልጧል። እንዲህ ያለ የድርቅ ሁኔታ በአፍሪቃው ቀንድ የተከሰተው ከ40 ዓመታት ወዲህ መሆኑም የተገለጸው። ከሰሞኑ የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት በእንግሊዝኛ ምህጻሩ IGAD እና የዓለም ሜቴሪዎሎጂ ተቋም በጋራ ይፋ ያደረጉት የአየር ሁኔታ ትንበያ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው የበልግ ወቅት የአፍሪቃው ቀንድ የሚያገኘው ዝናብ ከመደበኛው አማካኝ መጠን በታች ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል። ይኽ እውን ከሆነ ደግሞ ለተከታታይ ስድስት የዝናብ ወቅቶች በተስተጓጎሉባቸው የአካባቢው ሃገራት ሶማሊያ፣ ኬንያ እና ኢትዮጵያ ለድርቅ የተጋለጡት አካባቢዎች የባሰ ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችልም አሳስቧል። በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ሃገራት የዝናብ እጥረትም ሆነ ድርቅ ለምን ይሆን የሚደጋገመው? የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም በአመዛኙ የአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ካለው የተፈጥሮ ሁኔታ ጋር እንደሚያያዝ ነው የደን ባለሙያው ዶክተር አደፍርስ ወርቁ የሚገልጹት።

Somaliland Giro-Sumo Flüchtllingslager
ሶማሊያ ውስጥ ድርቅ ያፈናቀላቸው ወገኖች መጠለያምስል Daniel Jukes/ActionAid/AP/picture alliance

«ይኼ የምሥራቅ አፍሪቃ ቀጣና ተፈጥሮ ተጋላጭ እንዲሆን አድርጋዋለች፤ ለምሳሌ ሙቀቱ ከፍ ያለ ነው፤ ተለዋዋጭነቱ የዝናቡ ከፍ ያለ ነው በተፈጥሮ፤ በዚያም ላይ መሬቱ ቆላማ ነው።»

የዝናብ መስተጓጎልም ሆነ የመጠኑ መቀነስ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢያመዝንም በተለይ በአፍሪቃው ቀንድ አሁን ለሚታየው የዝናብ እጥረት ግን የአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ነው የተለያዩ ጥናቶች የሚያመለክቱት። ዶክተር አደፍርስም ይኽንኑ ነው ያረጋገጡት።

Kenia Dürre l Kadaver einer Kuh, im Hintergrund Turkana-Frauen mit Feuerholz
ኬንያም በድርቁ ከተጎዱት የአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት አንዷ ናትምስል Simon Maina/AFP

«በከፍታ ደረጃ አብዛኛው አካባቢ መሬት ዝቅ ያለ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭ የሚያደርገው፤ ከድርቅ ተጋላጭ የሚያደርገው ዝቅተኛ/ላቲቲዩድ/ አካባቢ ያለ ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ስድስት ተከታታይ የዝናብ ወቅት በቂ ዝናብ ያላገኙ በርካታ አካባቢዎች ናቸው። በውኃ እጥረት ከብቶታቸው ግጦሽ ማጣት የተጎዱባቸው የቦረና አርብቶ አደሮች ጉዳይ የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት በመሳቡ መነጋገሪያ ሆነ እንጂ አብዛኞቹ የሀገሪቱ ቆላማ የአየር ጠባይ ያላቸው አካባቢዎችም ለድርቅ መጋለጣቸውን የሚያሳዩ መረጃዎችም እየወጡ ነው። እንደ ቦረና ያሉ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን ለድርቅ ያጋለጠው የሰዎች እና የተፈጥሮ መስተጋብር ሚዛን በመዛነፉ እንደሆነ አጽንኦት የሰጡት የደን ምርምር ባለሙያ የሆኑት የአውሮጳ የደን ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ እና የዓለም አቀፍ የደን አስተዳደር ቡድን ሰብሳቢ ዶክተር ይታገሱ ተክሌ ምክንያት ያሏቸውን መሠረታዊ ችግሮች ይዘረዝራሉ።

Kenia Dürre l Kamelherde läuft gen Turkana See
ድርቅ ያስጨነቃቸው የአርብቶ አደሩ ከብቶችና ግመሎች ምስል Simon Maina/AFP

«ዋናው ችግራችን በእንግሊዝኛው ሃርሞኒ ብትዊን ኔዘር ኤንድ ፒዩፕል የሚባል አለ በመካከላችን ያለው ሃርሞኒ ተበጥሷል። እኛ ከመጠን በላይ ነው ከተፈጥሮ እየወሰድን ያለነው ላለፉት መቶ ዓመታት ወደ ተፈጥሮ ምንም ነገር ሳንመልስ ማለት ነው። አሁን የቦረናው ኬዝ እንደውም ጥሩ ማሳያ ነው ያለው፤ ቦረና የሚገርም የብዝሃህይወት መገኛ የሚባል አካባቢ ነው፤ በጣም ትልቅ። ከአንድ ሺህ በላይ የእጽዋት አይነት፣ የዛፍ አይነት ፣ የወፍ ገነት የሚባል ስፍራ ነው። እናም እዚያ አካባቢ ብዙ ነገሮች ሲከሰቱ ነበር።»

ድርቁ ቦረና ላይ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ከብቶችን ፈጅቷል። በሕይወት የተረፉትንም አዳክሟል፤ ኑሮው ከከብቶቹ ጋር የተሳሰረው ኅብረተሰብም ለከባድ ችግር ተጋልጧል። ለወትሮው ቦረና በብዝሃ ሕይወት ስብጥሩ ቢታወቅም የበረታው ድርቅ ተጽዕኖው በሁሉም ላይ ጉዳት እንዳስከተለ ነው ዶክተር አደፍርስ ያመለከቱት።

የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ደኖች የሚኖራቸው አዎንታዊ አስተዋጽኦ ብዙ ይነገርለታል። የደን መኖር የአፈር በውኃ መከላትንም እንደሚከላከልም ይታመናል። ኢትዮጵያ ውስጥ ለተከታታይ ዓመታት በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል፤ እንደ ቦረላ ያሉ ቆላማ  አካባቢዎች ከዚህ በረከት ደርሷቸው ይሆን? የአረንጓዴ አሻራ ቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር አደፍርስ እንዲህ ነው ያሉት።

Kenia Dürre l Dürrefeld in der Gemeinde Kidemu im Bezirk Kilifi
በኬንያ ውኃ ማጣት የሰነጣጠቀው መሬትምስል Dong Jianghui/Xinhua/picture alliance

«እውነቱን ለመናገር የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ሥራው ሀገራዊ ሆኖ እንዲሠራ ነው ትግል ሲደረግ የነበረው። ማለትም ዝናብ በደንብ ገብ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶ በርከት ያለ ችግኝ እንዲፈላ እንዲተከል፣ ቆላማ አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ እንዲደረግ ነገር ግን በቂ እርጥበት የላቸውም ችግኝ ለማብቀል በሚባሉት ቦታዎች ላይ አዲስ ችግኝ እዛ ቦታ ላይ ከማጽደቅ ይልቅ አንዳንድ የተጎዱ ቦታዎችን በመከለል ተመልሰው በተፈጥሮ እንዲያገግሙ ለማድረግ እገዛ እንዲደረግላቸው ነው ብዙ የገፋነው።»

የአየር ንብረት ለውጥ የሰዎች እና የተፈጥሮ መስተጋብር ሚዛን መሳት ያመጣው ጣጣ ነው የሚሉት የደን ይዞታ እና የአካባቢ ተፈጥሮ ተመራማሪዎች ማስተካከያው ላይ ማተኮር እንደሚገባም ይመክራሉ። በአፍሪቃው ቀንድ አካባቢ ሃገራት ለሚደጋገመው ድርቅ ዘላቂ መፍትሄ የለም ይሆን? የደን ባለሙያዎቹ ይበጃል ያሉንን በክፍል ሁለት ጥንቅር ሳምንት ይዘን እንቀርባለን።

ሸዋዬ ለገሠ 

ነጋሽ መሐመድ