1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአፍሪቃዉ ቀንድ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ እና የተንታኝ አስተያየት

ዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የራስ ገዝ የሶማሊላንድ ምንግስታዊ ሚዲያ ዘገበ፡፡ በበርካታ አውቶብሶችና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ያሳየው መንግስታዊ ሚዲያው፤ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው ሲል አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/4iEgG
የሶማሌ ላንድ ሰንደቅዓላማ
የሶማሌ ላንድ ሰንደቅዓላማ ምስል Eshete Bekele/DW

በአፍሪቃዉ ቀንድ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ እና የተንታኝ አስተያየት

በአፍሪቃዉ ቀንድ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ በተንታኙ ዓይን 

በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የራስ ገዝ የሶማሊላንድ ምንግስታዊ ሚዲያ ዘግቧል፡፡
በበርካታ አውቶብሶች እና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከሶማሊላንድ ተነስተው ዋጃሌ የተባለች የድንበር ከተማን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ያሳየው መንግስታዊ ሚዲያው፤ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው ያላቸውን የሠራዊት አባላቱ በግዛቲቱ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሸኘታቸውን አስታውቋል፡፡
ይህ ክስተት የተስተዋለውም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ኤርትራ የሚሰለጥኑ የሶማሊያ ወታደሮችን ጎብኝተው በተመለሱ በቀናት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡
ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የምስራቅ አፍሪቃ ጂኦፖሊቲካን በቅርበት የሚከታተሉት የፖለቲካ ተንታኝ ይህ ሁነት ለቃጣናው ምናልባትም አስጊ የሆነ ሌላው ጦርነት ሊከሰት ለመሆኑ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት የሶማሊላንድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አዲስ አበባ ተገኝተው በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት ሲያደርጉ፤ የኢፌድሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊላንድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኢል ታኒ ጋር በይፋ ያልተነገሩ ወታደራዊ ትብብር ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጾ ነበር።
ይህም የሆነው በጎርጎሳውያኑ ጃኑዋሪ 1 ቀን 2024 ኢትዮጵያ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል እንደሆነች ከምትቆጥረው ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሠነድ መፈራረሟን ተከትሎ ነው፡፡ ስምምነቱ ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘውን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን እስከ መጥራት ማድረሱም አይዘነጋም። የሶማሊላንድ ወታደሮች ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ዜና የተሰማውም የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኤርትራ ወታደራዊ ሥልጠና ላይ ያሉ ወታደሮችን ከጎበኙ በቀናት ውስጥ ነው። በርግጥ ይህ መረጃ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል እውቅናም ሆነ ማስተባበያ ያልተሰጠበት ነው፡፡ 
የሆነ ሆኖ መሰል ሂደት በምስራቅ አፍሪካ ላይ ሌላኛው ጦርነት የመከፈት ዝግጅት ምዕራፍ ላይ መሆኑን የሚያሳይ ነው ይላሉ የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ተከታትለው በመተንተን የሚታወቁት ትውልደ ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አቶ አብዱራሃማን ሰኢድ፡፡ “ሶማሊያ ባለፉት 30 ዓመታት በተለይምየኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲካሄድ ጀምሮ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ፍላጎት በተለያዩ ጊዜያት የሚራመዱባት ሆና ነው የቆየችው” የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ ከፊል የፖለቲካ ቡድኖች በኢትዮጵያ፤ በተቃራኒው ያሉት ደግሞ በኤርትራ ስደገፉ ታይቷል ብለዋል፡፡ አሁን ላይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የግንኙነት መሻከር ከተስተዋለ በኋላ የሶማሊያ ሰራዊት በበኤርትራ ማሰልጠን በይፋ የሚታወቅ ነው ብለዋልም፡፡ አሁን ደግሞ ከዚህ አጻፋ የራስገዟ ሶማሊላንድ ግዛት ሰራዊትን ኢትዮጵያ የምታሰለጥን ከሆነ ውጥረቱ ከሮ ወደጦርነት ሊገባ የሚችልበትን እድል ያሰፋዋል በማለትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ለዚህም ምክንያት ያሉት፡ “የሶማሊያ ጦር በኤርትራ ስልጠና ስሰጣቸው የመጀመሪያው ባይሆንም በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ቦታ የምሰጣት ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ ግዛት ወታደሮችን ስልጠና ከሰጠች የጦርነት እድሎች ሊሰፉ ችላሉ” በማለት ስጋታቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ለጦርነቱ አይቀሬነት እድሉን ሊያሰፉ የሚችሉም በቃጣናው ትልቅና ተደማጭ የሆነችኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ከምዕራቡ ዓለም የተሻለ ስፍራ የሚሰጣት መሆኑና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የጀመሩት የወደብ ስምምነት ላይ አቋማቸው እንደጸና መቀጠሉ ነው ብለዋል፡፡ “ባሁን ወቅት ከኢትዮጵያ አንጻር የኤርትራ እና ሶማሊያ መንግስታት ደካማ ሊባሉ የሚችሉ ናቸው” የሚሉት ተንታኙ በተለይም ኤርትራ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላት ደካማ ግንኙነት እና ሶማሊያ ያላት ደካማ አስተዳደር ለቃጠናው መረጋጋት የሚራቡ ዓለም አጋራት ኢትዮጵያ ሊደግፉ የሚችሉበት እድል ስለሚኖር ለጦርነት የኢትዮጵያ ፍላጎት ከፍ ብሎ ሊገፋ ይችላል ብለዋል፡፡ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ባለፉት 7 ወራት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነቷ ወደተቀዛቀዘው ኤርትራ ለሦስት ጊዜ ተጉዜዋል። ሶማሊያ ኤርትራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ ወታደሮቿን ለመመለስ ሲትጥር ይስተዋላል።
 

ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ 

ፀሐይ ጫኔ