1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአውሮፕላንና ድሮን ፈጠራ ላይ የተሰማራው ወጣት

ረቡዕ፣ የካቲት 24 2013

ወጣት ብሩክ በቀለ ይባላል።በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ ወጣት ሲሆን፤ አውሮፕላን መስራት የልጅነት ህልሙ ነው።ከአምስት አመታት ሙከራና ጥረት  በኋላ በተያዘው ዓመት ሞዴል አውሮፕላን በመስራት በወላይታ ሶዶ ከተማ የተግባር ሙከራ አድርጓል።ወጣቱ ሁለት የድሮን ንድፎችም አሉኝ ይላል።

https://p.dw.com/p/3q7TY
Biruk Bekele and his innovations.
ምስል Privat

ወጣት ብሩክና የፈጠራ ሥራዎቹ


በኢትዮጵያ አሁን አሁን ወጣቶች የተለያዩ አስደናቂ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት ሲያቀርቡ ይታያል።ያም ሆኖ በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ብዙዎቹ ወደ ተግባር ሲሸጋገሩ አይታይም። የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም በድሮንና በአውሮፕላን ፈጠራ ላይ ከተሰማራ አንድ ወጣት ጋር ቆይታ አድርጓል።
ወጣት ብሩክ በቀለ ይባላል።በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ  ወጣት ሲሆን፤ አውሮፕላን መስራት የልጅነት ህልሙ ነው።ተወልዶ ባደገባት የወላይታ ሶዶ ከተማ ስለ አውሮፕላን ስራ ይቅርና የቴክኒክ  ጥገና የሚሰጥ የረባ ጋራዝ ባይኖርም፤ የብሩክ  አድማስ ተሻጋሪ ሀሳብ ግን እንደ እድሜ እኩያዎቹ  አውሮፕላን አብራሪ፣መመህር ወይም ሀኪም መሆን ሳይሆን ራሱን አውሮፕላኑን መስራት ነበር።ለዚህም በልጅነት ዕድሜው በአቅራቢያቸው በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ ይመለከተው የነበረው በራሪ ነገር  የልጅነት አእምሮውን እጅግ ያስደንቀውና  ለመስራትም ፍላጎት ያሳደረበት መሆኑን ይናገራል።አስቦም አልቀረም የልጅነት አቅሙ በፈቀደለት መጠን በአካባቢው ባገኘው ነገር አውሮፕላን መስራት ጀመረ። 
«በልጅነቴ ነው የጀመርኩት።በካርቶን በቆርቆሮ በተገኘው በጭቃ ጭምር እየሰራን  ነበር ያደግነው።አሁን ዩንቨርሲቲው የተሰራበት አከባቢ አውሮፕላን ማረፊያ ነበር ።ትንንሽ አውሮፕላኖች ያርፉበት ነበር።አባቴ ለማሳየት እዛ ይወስደኝ ነበር። እና ከዛ ጊዜ ጀምሮ አንደዚህ አይነት «ኤሮ ዳይናሚክስ ሸፑን» የጠበቀ አውሮፕላን ያው ያኔ የሚታወቅ ባይሆንም፤እንደዛ  ግዑዝ የሆነ አካል ከሰማይ መጥቶ መሬት ላይ የሚያርፍበትና ከመሬት ደግሞ የሚነሳበትን ሳይ በጣም ይገርመኝ ነበር።እና ከዚያ ጀምሮ አብሮኝ ያደገ ነው።ያው በልጅነቴ  ከፍ ስል ሰባትና ስምንተኛ  ክፍል አካባቢ ከ«ኤሮቦቲክስ» ጋር የተገናኙ ነገሮችን እሞክር ነበር። በተበላሹ ቴፕ ፣ በዲናሞና ሞተር  እነሱን በመጠቀም ከዚያ ጀምሮ እሞክር ነበር።ያው እንደዚህ የመሄድ አቅም ያላቸው ባይሆኑም ከዛን ጊዜ ጀምሮ እሞክራለሁ።» 
ለቴክኒክና ለፈጠራ ስራ የተለዬ ፍላጎት እንዳለው የሚናገረው ብሩክ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሚከታተልበት ወቅት ከትምህርት ቤቱ በሚደረግለት የሙያና የቁሳቁስ ድጋፍ ከአውሮፕላን ስራው በተጨማሪ የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን መስራቱን ቀጠለ። 
«ሃይስኩል ላይም እንደዚሁ ለመሸለም ችያለሁ።የዚያኔም «ሮቦቲክስ» ላይ እሰራ ነበር።«ሪቻርጀብል» የሆኑ ባቡሮች ነበሩ በስዓት ሶስት ሺህ ሜትር መሄድ የሚችሉ። መኪናዎች ነበሩ።የተለያዩ ቁሳቁሶች ያው በሞዴል  ደረጃ ድሮኖች  ነበሩ። ለመወዳደር ያቀረብናቸው። የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖች ነበሩ። እና የዚያኔም እንደዚህ እሰራ ነበር ። ከክፍል ወደ ክፍል በተሻገርኩ ቁጥር የመሸለም በየቴሌቪዥን ጣቢያው የመቅረብ ዕድል ነበር ።»ሲል ተናግሯል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀም የፈጠራ  ህልሙን ዕውን ለማድረግ ወደ ወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ በማምራት  የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍልን ተቀላቀለ።በዚህ የዩንቨርሲቲ ቆይታውም የዩንቨርሲቲው ማኅበረሰብ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ሁለት ተጨማሪ የፈጠራ ስራዎች መስራቱን ይገልፃል።
«መመረቂያ ፕሮጀክት ሰርቼ ነበር። ከመመረቂያ አልፎ ሌሎች ወደ ሁለት ፕሮጀክቶች  ግቢ ውስ እስራ ነበር።የመጀመሪያው የግቢ «ሜን ጌት ኮንትሮል» የሚባል ማሽን ነበር የሰራሁት። የዩኒቨርሲቲው ግቢ በሰንሰለት ነበር ይከፈት ይዘጋ የነበረው። እሱን ግን የተሻለ አድርጌ ጊቢ ውስጥ መኪናዎች ሲገቡ የሰሌዳ ቁጥራቸውን የሚለይ እና የራሱ «ሴንሰር» የተገጠመለት «አውቶማቲክ ኮንትሮል» አድርጌ ነበር የሠራሁት።ሲቀጥል ደግሞ  የአትክልት መከተፊያ  ማሽን ነበር የሰራሁት። ይህንን ልሰራ የቻልኩት፤ ግቢ ውስጥ ተማሪ ይመገባል። ያው ከ20 እስከ 30 በሚደርሱ እናቶች ነበር ለምሳና ለዕራት ጥቅል ጎመን ይከተፍ የነበረው። ሃያ  ሠላሳ ሰው የነካው ጥቅል ጎመን ደግሞ ለብክለት የተጋለጠ ስለሆነ፤ ያለ ምንም ንክኪ እስከ አምስት ስድስት መቶ ኪሎ ግራም በአንድ ሰዓት ውስጥ መክተፍ የሚችል ማሽን ነበር።»
በ2011 ዓ/ም በሜካኒካል ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪውን መያዙ በሙያው ተጨማሪ የራስ መተማመን ቢፈጥርለትም፤ የአውሮፕላን ፈጠራ ስራው ግን  ከሌሎቹ የፈጠራ ስራዎች የበለጠ ዕውቀት ፤ገንዘብና ቁሳቁስ የሚጠይቅ በመሆኑ በሙያና በቁሳቁስ እጥረት ሳቢያ  ስራው እንዳሰበው ሊሄድለት አልቻለም ነበር።የኋላ ኋላ ግን  ሰርቶ የሚያገኛትትን ጥቂት ገንዘብ በማጠራቀም የአውሮፕላኑን የንድፍ ስራ ጀመረ።
«ካሰብኩ ብዙ ጊዜ ሆኖኛል። እነዚህን ዲዛይን አድርጎ ለመስራት በኛ ሀገር በኔ አቅም የሚቻል አልነበረም።ለብዙ ጊዜያት ቁሳቁስ ሳሰባስብ ነበር በተገኘው ብር ።የዲሽና የኤለክትሪክ «ኢንስታሌሽን»እሞክር  ነበርና በዚያ የተወሰነ ገንዘብ ማሰባስብ ችዬ ነበር።ያንን  ገንዘብ ቀድሞ ላሰብኩትና  ላሳካ ለምፈልገው ለነበረው አውሮፕላን   መስሪያ«ማቴሪያል» መግዣ ነበር ያደረኩት። እና ያሰባሰብኩት «ማቴሪያል»አውሮፕላን «ዲዛይን» ለመስራትና «ቢዩልድ»ለማድረግ  ይበቃል ብዬ ሳስብ ነው «ኮቪድ-19» እንደገባ አውሮፕላኔን መስራት የጀመርኩት።»
ከአምስት አመታት ሙከራና ጥረት  በኃላ በተያዘው ዓመት 2013 ዓ/ም ሞዴል አውሮፕላን በመስራት በወላይታ ሶዶ ከተማ መሬት ላይ ሙከራ ማድረጉን ተናግሯል። የተሰራበትን ሀገር ኢትዮጵያን፣የተሰራበትን አካባቢ ወላይታ ሶዶን፣የተሰራበትን ዓመተ ምህረት 2013ን በሚወክል መልኩ ለሞዴል አውሮፕላኑ EW-13 የሚል ስያሜ ሰጥቶታል።ለዚህ የፈጠራ ስራው ከኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማኅበረሰብ የዕውቅና ሰርተፌኬት ያገኘ ሲሆን ፤ከስቪል አቬሽን  ፈቃድ እንዳገኘ የበረራ ሙከራ እንደሚያደርግም ይገልፃል።
« በድሮን መልክ ቀደሞ  ሞክሬ የተወሰነ ክፍ የማለት አቅም ያለው ሄልኮፕተር ሰርቼ ነበር። ከዚያ አልፎ  ደግሞ ይሄኛው ትንሽ ከፍ ያለ ነው። በፋይናንስ አንፃርም በአቅምም ሰው ይዞ መነሳት የሚችል አውሮፕላን ነው። አሁን የሚገኝበት ሁኔታ «ራን ወይ ቴስት»/የማኮብኮብ ሙከራ/ ላይ ደርሻለሁ። ከሲቪል አቪየሽን ያው የበረራ ፈቃድ እንዳገኘሁ «ሴፍቲ» እንዳሟላሁ ያው «ቴክ ኦፍ»/መብረር/ እሞክራለሁ ብዬ አስባለሁ።ከ«ስፔስ ሳይንስ ሶሳይቲ» የእውቅና ሰርተፊኬት ሰጥተውኛል። አልፎ ተርፎም የአፍሪካ  «ኤሮናውቲክ»ና «አስትሮናውቲክ» ሴንተር የሚባል የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ የሚሰራ ማዕከል «ኮፋዉንደር» /መስራች/ አደርገው ሹመውኛል።» 
ለዚህ የፈጠራ ስራ ከሁለት መቶ ሺ ብር በላይ ማውጣቱን የሚናገረው ብሩክ፤ከአውሮፕላኑ በተጨማሪ  ወደ ስራ መግባት የሚችሉ ሁለት የድሮን ንድፎች እንዳሉትም ይገልፃል።ለዚህና ለሌሎች የፈጠራ ስራዎቹ ከኢትዮጵያ የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስተር  የባለቤትነት ፈቃድ ለማግኘት እየተጠባበቀ ሲሆን፤ድሮኑንም ሆነ አውሮፕላኑን ለመስራት በኢንተርኔት ከሚያገኘው ዕውቀት ውጭ ሌላ የተለዬ የሙያ ድጋፍ አልዳልነበረውም ያስረዳል።
«እንድሰራ በደንብ አግዞኛል የምለውው ኢንተርኔት ነው«ዩ ቲዩብ» በደንብ እከታተላለሁ ።ከዚህ በፊት«ፌል»ያደረገባቸውን ሰዎችን፣ የተሳካ በረራ ማድረግ የቻሉ ሰዎችን እከታተላለሁ።« ዩ ቱብ ላይ በደንብ እከታተላለሁ የኔንም ስራ እንዲያገዘኝ። እንድማርበት አግዞኛል ብዬ የምገምተው «ዩ ቲዩብ» እና ኢንተርኔት ነው።« ጎግል ሰርች» አደርጋለሁ። በተቻለኝ አቅም ከዛም ከዛም አድርጌ ነው የኔን «ዲዛይን» የተሳካና ጥሩ እንዲሆን ፣«ኤሮ ዳይናሚክስ ሸፕ» የጠበቀ እንዲሆን አድርጌ ለመስራት ችያለሁ። ያው ለመስራት ያገዘኝ እንተርኔት ነው።ሌላ የተለዩ ድጋፍ ወይም አውሮፕላን በተግባር በየዕለቱ ማየት ሲያስፈልገኝ የማይበት ዕድል አልነበረም።በዚህ «እስፔሻላይዝ» ያደረጉ ምሁራን ሊረዱኝ የሚችሉም አልነበሩም እና በራሴ ጥረት ነው  ከእግዚአብሄር  ጋር እዚህ የደረስኩት።»ብሏል።
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት እዚያው የተማረበት ወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲቲ  በማስተማር  ስራ ላይ ተሰማርቶ  ተማሪዎችን በማገዝ በሙያው ያለውን ክፍተት በመሙላት ላይ ይገኛል።እንደ ብሩክ ገለፃ ኮቢድ-19  ከተከሰተ ወዲህም ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆኑ ማስታጠቢያዎችንና በሞተር ሰይክል የሚሰራ የኮሮና ተዋህሲ ማፅጃን ሰርቷል ። በአጠቃላይ እነዚህን ጨምሮ  እስካሁን አስር የሚሆኑ የፈጠራ ስራዎችን  የሰራ ቢሆንም፤ በገንዘብ እጥረት የተነሳ አንዳቸውንም ወደ አገልግሎት ማስገባት አልቻለም።ያም ሆኖ ተስፋ ሳይቆርጥ እንደሚቀጥል ይናገራል።ሌሎች በፈጠራ ስራ የተሰማሩ ወጣቶችም ይህንኑ እንዲያደርጉ ይመክራል። «እንደዚህ አይነት የፈጠራ ስራዎችን መርዳት  ለሀገር አስተዋጽኦ ማድረግ ነው።» የሚለው ብሩክ፤የመንግስት አካላት፣ አቅም ያላቸው  ባለሀብቶችና ግለሰቦችም ቢሆኑ በሚችሉት መንገድ እገዛ ቢያደርጉ መልካም ነው ይላል።
«እንደዚ አይነት ስራዎችንም መርዳት ማለት ለሀገርም አስተዋጽኦ ማድረግ ነውና አቅም ያላቸው ባለሀብቶች ፣የመንግስት ባለደርሻ አካላት በሚችሉት መንገድ በሚችሉት አቅም በቁሳቁስም ሆነ በፋይናንስ እንዲህ ተሰጦ ላላቸው ልጆች የሚያደርጉት ድጋፍ ቢያደርጉ ለሀገር  እንዳደረጉ የሚቆጠር ነውና እባካችሁን የተቻላችሁን ሁሉ  እርዱን ።»በማለት ወጣት ብሩክ በቀለ ጥሪውን አስተላልፏል።

Biruk Bekele and his innovations.
ምስል Privat
Biruk Bekele and his innovations.
ምስል Privat
Biruk Bekele and his innovations.
ምስል Privat
Biruk Bekele and his innovations.
ምስል Privat

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ