1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአርሲ ዞን አሰላ አቅራቢያ በታጣቂዎች የደረሰ ጥቃት

ሐሙስ፣ ግንቦት 24 2015

በአርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ ጨፌ ሚሶማ በተባለ አከባቢ ታጣቂዎች አራት ሰዎች መግደላቸውን የዓይን እማኞች ገለጡ፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ እሑድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ማንነታቸውን በውል ባልተገለጸ የታጠቁ አካላት በደረሰው ጥቃት የዴራ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ሁለት ካህናትን ጨምሮ አራት ሰዎች መገደላቸውንም አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/4S1p4
Äthiopien Bekoji | Bekoji Town, Sportzentrum & Laufzentrum | Stadion in schlechtem Zustand
ምስል Seyoum Getu/DW

በአርሲ ዞን አሰላ አቅራቢያ በታጣቂዎች የደረሰ ጥቃት

በአርሲ ዞን ጢዮ ወረዳ ጨፌ ሚሶማ በተባለ አከባቢ ታጣቂዎች አራት ሰዎች መግደላቸውን የአካባቢው የዓይን እማኞች ገለጡ፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ እሑድ ግንቦት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. እኩለ ሌሊት ማንነታቸውን በውል ባልተገለጸ የታጠቁ አካላት በደረሰው ጥቃት የዴራ አማኑኤል ቤተክርስቲያን ሁለት ካህናትን ጨምሮ አራት ሰዎች  መገደላቸውንም አመልክተዋል። ታጣቂዎቹ ከነዋሪዎች ገንዘብ መውሰዳቸውና ሁለት ሰዎችን አግተውም እንደነበር እማኞቹ ለዶቼ ቬለ አረጋግጠዋል። 

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን፤ ከስጋታቸው የተነሳም ድምጻቸው የተቀየረው የጢዮ ወረዳ ጨፌ ሚሶማ ዴራ አማኑኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ ነዋሪ፤ በእሑዱ እኩለ ሌሊት ጥቃት የተከሰተውን እንዲህ ያስረዳሉ።

«እሑድ ሌሊት እኛ እርግጠኞች ባንሆንም «ሸነ ነው» የተባሉ ታጣቂዎች ስናይፐር ጭምር የታጠቁ ይመጣሉ፡፡ መጀመሪያ መምህሬ ካሱ የተባሉትን ሰው ቤተክርስቲያን አካባቢ ያገኛሉ፡፡ እሳቸውን ይዘው መምህሬ ታደለ ቡልጋወርቅ የሚባሉ ካህን ቤት እና የወንድማቸው እንዳለ የቡልጋወርቅ ቤት ገቡ፡፡ ከዚያን ሦስቱን ይዘው ገንዘብና መሳሪያ እናገኝበታለን ብለው ወዳሰቡት ቤት ወደ 3ኪ.ሜ. ርቀው ሄዱ። ከዚም ዳንኤል አማረ የተባሉ ግለሰብ ቤት ገብተው አንድ መሳሪያ ወስደው ሁለት መቶ ሺህ ብር ጠየቁ፡፡ የነበራቸው ገንዘብ መቶ ሺህ ብር ብቻ በመሆኑ ተጨማሪ መቶ ሺህ ብር እንዲያመጡ ተነግሯቸው የ14 ዓመት ታዳጊ ልጃቸውን ይዘው ወጡና ሌላው ጎረቤታቸው ፋንታሁን ዳኛቸው የሚባሉት ሰው ጋር ገብተው እሱንም አግተው ወሰዱ፡፡ በርግጥ አሁን ሁለቱ የተጠየቀው ገንዘብ ኢተያ አካባቢ ተከፍሎ በደህና ተለቀቁ፡፡»

ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀው አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪም፡ «የታገቱት ሁለቱ ሰዎች በአራት መቶ ሺህ ብር ተለቀዋል፡፡ በዕለቱ አራት ሰዎች ግን ተገድለዋል» በማለት አክለዋል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ አስተያየት ታጣቂዎቹ አስቀድመው ይዘው የነበሩትን ሁለት ካህናት፣ የአንዱ ክህኑ ወንድም እና የአማኑኤል ቤተክርስቲያን ጥበቃን ጨምሮ ሁለት በተጨማሪነት የታገቱትን ስድስት ሰዎች ይዘው ወደ ቤተክርስቲያን በማምራት አራቱን ገድለዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሰዎቹ መገደል ባሻገር ቤተክርስቲያኑ አንደኛው በሩ ከመሰበሩ ውጪ የደረሰ የከፋ ጉዳት የለም፡፡ ይህ ጥቃት የተፈጸመበት ስፍራ ቁሉምሳ ተብሎ ከሚጠራው አሰላ ከተማ አቅራቢያ ከሚገኘው ከአሰላ ብቅል ፋብሪካ 10 ኪ.ሜ. ብቻ ወደ ውስጥ ገብቶ የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል።  ከዚህ ስፍራ አሁን ኅብረተሰቡ ተስፋ ከመቁረጥ የተነሳ ለዘመናት የኖረበትን ቀዬ እየለቀቀ እየወጣ እንደሆነም ነዋሪዎቹ በአስተያታቸውን አክለዋል፡፡ 

ዶይቼ ቬለ ስለጉዳዩ ከታጣቂው ቡድንም ሆነ ከገለልተና አካል ማጣራት አልቻለም፡፡ ይሁንና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት ጥያቄውን አቅርበን ቤተክርስቲያንቱ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው የሚል ምላሽ ሰጥታለች፡፡ በመንግሥት አካል በኩልም ለጢዮ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ግርማ ጣፋ ጥያቄውን አቅርበን ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ሳይሰጡበት ወደ ስብሰባ እየገባሁ ነው ብለዋል፡፡ ይሁንና ከሰዓታት በኋላ መልሰን ብንደውልላቸውም ስልካቸው አይነሳም፡፡ የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤትን አስተያየትም ጠይቀን ለዛሬ አልሰመረልንም።

 ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ