1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ድርቅ ያስከተለዉ ቀዉስ

ረቡዕ፣ ኅዳር 26 2016

በአማራ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ እንደሆነ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተናገሩ። የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን 3 ወረዳዎች ባደረገው ጥናት ሰዎችና እንስሳት መሞታቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል። በዞኑ 6 ወረዳዎች ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱም ተመልክቷል።

https://p.dw.com/p/4Zqdq
አማራ ክልል
አማራ ክልል ምስል Seyoum Getu/DW

በድርቅ ለተጎዱ ነዋሪዎች የተወሰነ እርዳታ ቢደርስም ሁሉንም ተረጂ ያማከለ አይደለም

በአማራ ክልል ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ማህበራዊ ቀውስ እየተፈጠረ እንደሆነ በድርቅ በተጠቁ አካባቢዎች የሚኖሩ አርሶ አደሮች ተናግረዋል፣ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በሰሜን ጎንደር ዞን 3 ወረዳዎች ባደረገው ጥናት ሰዎችና እንስሳት መሞታቸውን ማረጋገጡን አስታውቋል፣ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና  በበኩሉ በዞኑ 6 ወረዳዎች ከፍተኛ ድርቅ መከሰቱን አመልክቷል፡፡

ድርቅ በአማራ ክልል

ድርቅ በከፍተኛ ሁኔታ ካጠቃቸው የሰሜ አማራ አካባቢዎች መካከል አንድ አርሶ አደር ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት በድርቅ ለተጎዱ ነዋሪዎች የተወሰነ እርዳታ ቢደርስም ሁሉንም ተረጂ ያማከለ ባለመሆኑ ብዙዎች አሁንም በርሀብ እየተጠቁ ነው፡፡ ድርቁ በከፍተኛ ሁኔታ ሰዎችንና እንስሳቱን እየጎዳ ነውም ብለዋል፡፡

የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ግኝት

በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ድርቅ ካጠቃቸው ወረዳዎች መካከል በ3ቱ ጥናት ያካሄደው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ግኝቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ 8 አባላት ያሉት የጥናቱ አስተባባሪ ረዳት ፕሮፌሰር አምሳሉ ተበጀ የጥናቱን ግኝት ለዶይቼ ቬሌ አብራርተዋል፡፡ “ጥናቱ በአማራ ክልል፣ ሰሜን ጎንደር ዞን፣ በጃንአሞራ፣ በጠለምትና በበየዳ ወረዳዎች የተካሄደ ሲሆን በጥናቱ ግኝት መሰረት 36 ሰዎች ህይወታቸው አልፏል፣  72 ሺህ 387 እንስሳት ሞተዋል፣ 16 ሺህ 414 ሄክታር ማሳ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፣ 219 ሺህ 709 ኩንታል ምርት ቀንሷል፣ 107 ሺህ 407 ሰዎች ለችግር ተዳርገዋል፣43ሺህ ቶን የእንስሳት መኖና 89ሺህ 244 ቶን ተረፈ ምርት ጉዳት ደርሶበታል፣ የእንስሳት በሽታም በሰፋት ተከስቷል፡፡” ብለዋል፡፡ 

ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለዉ አማራ ክልል የሚገኙ ዜጎች
ከሌሎች ክልሎች ተፈናቅለዉ አማራ ክልል የሚገኙ ዜጎች ምስል Negassa Dessalegen/DW

ድርቁ በመማር ማስተማር ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ

ድርቁ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ መፍጠሩንም አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ “14ሺህ 847 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል፣ 16ሺህ 650 ተማሪዎች ደግሞ በርሀብና በችግር ምክንያት በአግባቡ ትምህርት እየተከታተሉ አይደለም፣ 292 ተማሪዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው ተሰድደዋል፣ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሌሎች ከተሞች የሚከታተሉ በርካታ ተማሪዎች የማቋረጥ ሁኔታ ተፈጥሯል፣ ምክንቱ ደግሞ ለመኖሪያ ክፍል (ዶርሚተሪ) የሚከፍሉት የኪራይ ገንዘብ በማጣታቸው ነው፡፡ ”

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና አስተያየት

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላክልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰላምይሁን ሙላት የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ያደረገው ጥናት በአካባቢዎቹ ያለውን የድርቅ ተጽዕኖ ያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዞኑ በስድስት ወረዳዎችና በ83 ቀበሌዎች ድርቅ መከሰቱን አረጋግጠዋል፣ የእርዳታ ግብዓት እጥረት እንዳለም ተናግረዋል፡፡ መምሪያ ኃላፊው ጭምረው እንደተናገሩት በዞኑ በአጠቃላይ በ6 ወረዳዎች ድርቅ መከሰቱንና ከ450 ሺህ በላይ  እርዳታ ፈላጊዎች አሉ ብለዋል፣ ሆኖም እስካሁን እርዳታ ከሚፈልገው መካከል እገዛ የተደረገለት ተረጂ ከ200 ሺህ እንደማይበልጥ አመልክተዋል፣ በመሆኑም የፌደራለም ሆነ የክልሉ መንግስት እርዳታውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን በድርቅ የተጎዱ አርሶ አደርም ሁሉም አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሰውንና እንስሳትን እንዲታደጉ ሲሉ ተማፀነዋል፡፡

በአማራ ክልል በድርቁ የተጎዱ ነዋሪዎች

በአማራ ክልል 8 ዞኖች ድርቅ መከሰቱንና ወደ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ከድርቁ ጋር በተያያዘ እርዳታ እንደሚፈልግ ቀደም ሲል የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ዛሬ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነዉ ጥረት ኮሚሽነሩ ስልክ ባለማንሳታቸው አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ፀሐይ ጫኔ 

አዜብ ታደሰ