በአማራና ትግራይ ክልሎች ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይከሰት ምን ይደረግ?
እሑድ፣ የካቲት 24 2016የፕሪቶሪያው ስምምነት ተፈርሞ የጠመንጃ አፈሙዝ ልሣናት ይዘጉ እስከተባለበት ድረስ በተካሄደው የሰሜኑ ጦርነት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል ። ብዙዎች ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል ፤ ከቤት ንብረት ከቀዬያቸውም ተፈናቅለዋል ። የጦርነቱ ጠባሳ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ ግድም በኋላም በጉልኅ ይታያል ። ባለፉት ሳምንታት በትግራይ እና አማራ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል ለአጭር ጊዜያት የቆዩ ግጭቶች ከአንዴም ሁለት ጊዜ መከሰታቸው ነዋሪዎችን እጅግ አስግቷል ።
ኹነኛ መፍትኄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ሳይበጅለት ተድበስብሶ የቆየው የሁለቱ ክልሎች ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የሚጠይቁ ድምፆች እየተስተጋቡ ነው ። በሁለቱም ክልሎች በጦርነት እና ተደጋጋሚ ግጭቶች እጅግ የተጎዳው ማኅበረሰብ ለረሐብ እና ለእርዛትም ተዳርጓል ። አማራ ክልል የፋኖ እና የከመከላከያ ጦርነት ቀጥሏል ። በዚህ ሁሉ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በአማራና ትግራይ ክልሎች በርካታ ሕዝብ የተገደለበት አይነት ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት በሁለቱ ክልሎች መካከል እንዳይከሰት ምን ይደረግ? የዛሬው የእንወያይ መሰናዶዋችን ዋነኛ ትኩረት ነው ።
በውይይቱ 3 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው።
-
ገብረየሱስ ተክሉ ባሕታ (ዶ/ር)፦ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ሣይንስ እና ቋንቋዎች የኮሌጅ መምህር
-
አቶ ባይሳ ዋቅወያ፦ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሞያ፤ ላለፉት 30 ዓመታት የተመድ ባለሥልጣን
-
ሲሳይ መንግስቴ አዲሱ (ዶ/ር)፦ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ፤ ፌዴራሊዝም እና ሰብአዊ መብቶች መምህር እና ተመራማሪ ናቸው ።
በውይይቱ መግቢያ ላይም፦ የአማራና የትግራይ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በሚያነሱባቸው አካባቢዎች ከሚኖሩ ሰዎች ያሰባሰብናቸው አስተያየቶችም ተካቷል ። አስተያየት ሰጪዎቹ ውጥረቶች በመላ በሰላማዊ መንገድ በውይይት እንዲፈታ ጠይቀዋል ።
ሙሉ ውይይቱን በድምፅ መከታተል ይቻላል ።
«በአማራና ትግራይ ክልሎች ዳግም ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይከሰት»፦ በሚል ርእስ በቀረበው ውይይት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት በኢሜል ብንጠይቅም ለውይይቱ ተሳታፊ የሚሆን ሰው እንደሌለ በዛው በኢሜል ምላሽ ተሰጥቶናል ። ለመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) እንዲሁም ለምክትላቸው ሠላማዊት ካሳ በዶይቸ ቬለ በኩል የላክነው ይፋዊ የኢሜል ግብዣ ውይይቱን እስካደረግንበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘም ።
ሙሉ ውይይቱን በድምፅ መከታተል ይቻላል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ኂሩት መለሠ