1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በችግኝ ተከላው የኅብረተሰቡ ተሳትፎ

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 20 2013

ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመታት አንስቶ በዘመቻ የጀመረችው የችግኝ ተከላ ከዓመት ዓመት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ እያሳደገ መምጣቱን ዘመቻውን በቅርበት የሚያስተባብሩ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ሕዝቡም በየአካባቢው ለኤኮኖሚ ጥቅም ያላቸውን እና የሚያስፈልጉትን የችግኝ አይነቶች የሚጠይቅባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉም እየታየ ነው ይላሉ።

https://p.dw.com/p/3y8gn
Eco Africa Sendung #235 25.09.2020
ምስል DW

አረንጓዴ አሻራ

ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት ዓመት ወዲህ በሚሊየኖች እና ቢሊየኖች የሚገመቱ ችግኞችን ለመትከል ማቀዷን የችግኝ ተከላውን ሂደት የሚመዘግበው አረንጓዴ አሻራ የተሰኘው ድረ ገጽ ያመለክታል። የዘመቻ ችግኝ ተከላው ቀጣይነት እንደሚኖረውም ነው የሚጠበቀው። በዘመቻው ችግኝ ተከላ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ እየጨመረ መሄዱን አረንጓዴ አሻራን የሚያስተባብሩ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በዚህም ተስፋ ሰጪ እና አበረታች ለውጦች መታየት መጀመራቸውንም እንዲሁ።

በሚሊየንም እንበል በቢሊየን የሚገመቱት በተከታታይ ዓመታት ከተተከሉት ችግኞች ቢያንስ ግማሾቹ ቢጸድቁ ስነምህዳሩን ከማሻሻል፤ የአፈር መሸርሸርና መከላትን ከመከላከል እንዲሁም የሥራ ዕድልን ለበርካቶች ከመፍጠር አኳያ ጠቀሜታው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ሳምንት በዚሁ መሰናዶ እንግዳችን የነበሩት የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የደን ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዳይሬክተር አቶ ጥላዬ ንጉሤ ይናገራሉ።

Äthiopien - Weltrekord im Bäume pflanzen -Symbolbild
ምስል picture-alliance/A. Boureau

ኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው የኅብረተሰብ ክፍል የማገዶ እንጨትና ከሰል ተጠቃሚ መሆኑን ያስታወሱት የደን ባለሙያው ዛሬ ለፍጆታ እየዋለ የሚገኘው የደን ውጤት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በዘመቻ የተተከሉ ችግኞች ውጤት መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ። የተጎዳና የተራቆተ አካባቢ ላይ ይኖሩ የነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አካባቢያቸውን በደን ለማልበስ በተደረገላቸው ቴክኒካዊ ድጋፍ ተጠቅመው አኗኗራቸው መለወጡንም በምሳሌ ያስረዳሉ።

የደን ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አደፍርስ ወርቁ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ የደን ሀብቱ ለአደጋ መጋለጡን፤ ኅብረተሰቡም ሆነ መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጡ በዚሁ መሰናዶ እየቀረቡ ሙያዊ አስተያየቶች አጋርተው ያውቃሉ። በዚህ በአረንጓዴ አሻራ የዘመቻ ችግኝ ተከላ እንቅስቃሴም በብሔራዊ ደረጃ ዘመቻውን የሚያስተባብረው እና ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚገኙበት የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ በመሆን እየሠሩ ነው። ዛሬ አረንጓዴ አሻራ ብንለውም በዘመቻ ችግኝ የመትከሉ ልማድ በሀገሪቱ እንግዳ አይደለም ነው የሚሉት። በዘመቻ ሢሠሩ ሥራዎች የራሳቸው እጥረት ሊኖራቸው ይችላል የሚሉት ዶክተር አደፍርስ ከችግኝ ተከላው ዘመቻ የተገኙ ልምዶች እና አበረታች ተሞክሮዎችም እንዳሉ ሳይገልጹ አላለፉም። ለመሆኑ እርስዎስ አረንጓዴ አሻራዎን አኑረዋል? ክረምቱ ከማለቁ በፊት ጊዜ አልዎት። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ማዕቀፉ ያድምጡ።

ሸዋዬ ለገሠ