1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«በድርቁ ምክንያት ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠዋል»

ሰኞ፣ ጥር 20 2016

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ረሃብ ተከትሎ በተለይ ህፃናት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ተገለፀ። በክልሉ በረሃብ በተጠቁ አካባቢዎች የምግብ እጥረት ችግር ገጥሞአቸው ወደ ሆስፒታል የሚገቡ ህፃናት መጠን በሶስት እጥፍ ማደጉም ተነግሯል።

https://p.dw.com/p/4bniA
ትግራይ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎች
ትግራይ በድርቅ የተጎዱ አካባቢዎችምስል Million Haileselassie/DW

በትግራይ ክልል የተከሰተ ረሃብ

በትግራይ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በስፋት እየታየ ያለው ረሃብ በተለይም በህፃናት እና እናቶች ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል። በተለይም በድርቅ በተጎዱ የተለያዩ ወረዳዎች መታዘብ እንደሚቻለው በምግብ እጥረት ምክንያት ለበሽታ ተጋልጠው ወደ ሕክምና ተቋማት የሚገቡ ህፃናት ቁጥር ተበራክቷል፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ ህፃናት መጠን ጨምሯል፣ በከተሞች በልመና የተሰማሩ፣ ለጉልበት ብዝበዛ የተዳረጉ፣ ወደ ስደት የሚያመሩ በርካቶች ናቸው። 

በትግራይ በረሃብ በከፋ ሁኔታ ከተጎዱ ወረዳቸው መካከል በሆነችው አበርገለ የጭላ ወረዳ የሚገኘው የጭላ ሆስፒታል በርካታ ህፃናት በየቀኑ የምግብ እጥረት የወለደው በሽታ እየገጠማቸው ወደ ተቋሙ እንደሚመጡ ከሆስፒታሉ የጤና ባለሙያዎች ገልፀውልናል። በየጭላ ሆስፒታል የህፃናት ሕክምና ክፍል አስተባባሪው ነርስ ዮሴፍ ገብረሚካኤል እንደሚለው፥ በሶስት ወራት ውስጥ 80 ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት በከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጠቅተው በሆስፒታሉ እንክብካቤ እንደተደረገባቸው ይገልፃሉ። ነርስ ዮሴፍ "በጥቂት ወራት ውስጥ ብቻ የተወሳሰበ ከፍተኛ የምግብ እጥረት የገጠማቸው ከ80 በላይ ህፃናት በሆስፒታላችን ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። ይህ ቁጥር እየተመላለሱ የሚታከሙ፣ በግብአት እጦት ምክንያት የሕክምና አገልግሎት ጨርሶ ያላገኙ ሳይጨምር ነው። ረሃቡ በተለይ በህፃናት ጫናው የከፋ ሆንዋል። ሕክምና ጨርሰው የሚወጡት ጭምር ዳግም የሚመጡበት ሁኔታ ነው የሚስተዋለው ያለው። በአጠቃላይ ህፃናት አደጋ ላይ ናቸው" ይላሉ።

እንደ የሕክምና ባለሙያው ገለፃ በአካባቢው አስቀድሞም የምግብ እጥረት ይታይ የነበረ ቢሆንም በተለይም ከጦርነቱ በኃላ ግን የህፃናት የምግብ እጦት ችግር በሶስት እጥፍ ማደጉ ይገልፃሉ። 
"ከዚህ በፊትም በአካባቢያችን የህፃናት የምግብ እጥረት ይታይ የነበረ ነው። አጠቃላይ በምግብ ዋስትና ላይ ችግሮች ነበሩ። ይሁንና አሁን የዝናብ መጥፋት እና ጦርነቱ የወለደው ቀውስ ተጨምሮበት የከፋ ሆኗል። ድርቅ በትግራይከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የህፃናት ማልኒቱሪሽን መጠን በሶስት እጥፍ አድጓል" ይላሉ የሕክምና ባለሙያው።

በትግራይ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በስፋት እየታየ ያለው ረሃብ በተለይም በህፃናት እና እናቶች ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል።
በትግራይ የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በስፋት እየታየ ያለው ረሃብ በተለይም በህፃናት እና እናቶች ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ይገኛል። ምስል Million Haileselassie/DW


በየጭላ ሆስፒታል ከአጎራባች የአማራ ክልል ወረዳዎች የሚመጡ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ችግር የገጠማቸው ህፃናትም ሕክምና እየተሰጣቸው መሆኑን ባለሙያው ጨምረው ገልፀውልናል። ይህ በህፃናት የጠናው ረሃብ በርካቶች ከትምህርት ገበታ እንዲርቁም እየገፋ ነው ተብሏል። እንደ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ መረጃ በትግራይ 625 ትምህርቶች ውስጥ የሚገኙ 222 ሺህ ተማሪዎች ድጋፍ ካልተደረገላቸው በረሃብ ምክንያት ትምህርታቸው ሊያቋርጡ ይችላሉ። የአበርገለ የጭላ ወረዳ ትምህርት ፅሕፈት ቤት ሐላፊ መምህር ግዚያዊ ተክላይ በአካባቢው ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርት አቋርጠዋል ይላሉ። መምህር ግዚያዊ "ሳይመዘገብ የቀረ እንዲሁም ተመዝግቦ ያቋረጠ ጨምሮ በአጠቃላይ 4449 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል። ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ድርቅና ረሃቡ ነው። ህፃናት መማር ሲገባቸው ትምህርት አቋርጠው ልመና ላይ ተሰማርተው ይታያሉ። ፈታኝ ሆኖ ነው ያለው" ይላሉ።

በትግራይ ባለው ስብአዊ ቀውስ ዙርያ የፌደራል መንግስቱ እና የትግራይ አስተዳደር አካላት የተለያየ መረጃዎች ያወጣሉ። የፌደራል መንግስቱ ለትግራይ በቂ እርዳታ እየቀረቀ ነው የሚል ሲሆን የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር  በበኩሉ በክልሉ የሚገኝ 91 በመቶ ህዝብ በድርቁ ምክንያት ለአደጋ ተጋልጦ ይገኛል ይላል።    

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ