1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በተለያዩ ሃገራት የተባባሰው ዝናብና ጎርፍ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016

ከቅርብ ወራት ወዲህ በተለያዩ ሃገራት የሚወርደው ከመጠን ያለፈ ዝናብ ያስከተለው ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው። የሰዎችን ሕይወት መቅጠፍን ጨምሮ የግልና የመንግሥት ንብረትቶች እንዲሁም መሠረተ ልማቶችን እንዳልነበሩ ሆነዋል። የሙቀት መጠኑ መጨመር በአንድ ወገን ሌላው የዓለማችን ስጋት መሆኑ እየተነገረ ነው።

https://p.dw.com/p/4gvRQ
የጎርፍ አደጋ የጠናባት ብራዚል
የጎርፍ አደጋ የጠናባት ብራዚል ምስል Diego Vara/REUTERS

በተለያዩ ሃገራት የተባባሰው ዝናብና ጎርፍ

የተባባሰው የተፈጥሮ አደጋ

ተከታታይ ከባድ ዝናብና ጎርፍ እንዲሁም የሙቀት ማዕበል በአፍሪቃ፤ በደቡባዊ ብራዚልና አማዞን አካባቢም ጎርፍ፤ ሕንድን ጨምሮ በመላው እስያ ኃይለኛ ሙቀት አዲሱ መደበኛ የአየር ጠባይ ሁኔታ መሆኑ እየተደጋገመ ነው። በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ዜናው ሁሉ በአየር ጠባይ ሁኔታ ማስጠንቀቂያዎች የታጀበ ሆኗል። የዓለም ሜቴሬዎሎጂ ድርጅት እስካሁን በታየው ክስተት ይህ ዓመት የአየር ሁኔታውመጥፎና ጽንፍ የወጣ ነው ብሏል። የድርጅቱ የአየር ንብረት ባለሙያ አልቫሮ ሲልቪላ ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት፤ ከጥር ወር ወዲህ ብቻ እንኳን በሁሉም አህጉራት አደገኛ የአየር ሁኔታ ታይቷል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኃይለኛ ንፋስና ወጀብ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል የሰዎች ሕይወትም ጠፍቷል። ፓፓዋ ኒው ጊኒ ውስጥ የወረደውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በደረሰ የመሬት መንሸራተት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከእነ ሕይወታቸው ሳይቀበሩ እንዳልቀሩም ተገልጿል። ባንግላዴሽና ሕንድ ውስጥ በሰዓት 135 ኪሎ ሜትር የሚወረወር ኃይለኛ ንፋስ ባስከተለው የመሠረተ ልማት ውድመት ሁለት ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ለችግር መጋለጡ ተሰምቷል።

ኃይለኛ ዝናብና ጎርፍ በብራዚል

የጎርፍ አደጋ ከጠናባቸው ሃገራት ደግሞ ብራዚል አንዷ ሆናለች። የተፈጥሮ ቁጣ በጠናባት ብራዚል ደቡባዊ ግዛቷ ላይ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የወረደው ዝናብ ከተሞቹን ውጧቸው ታይቷል። ሪዮ ግራንደ ዶ ሱል ግዛት ውስጥ በዚሁ በጎርፍ አደጋ ምክንያት ከ160 ሰዎች በላይ ሲሞቱ 44ቱ የደረሱበት አልታወቀም ነው የተባለው። ከግማሽ ሚሊየን በላይ ደግሞ ቤታቸውን እና አካባቢያቸውን ጥለው ለመሄድ ተገደዋል። በሀገሪቱ እስካሁን ታይቶ አይታወቅም በተባለው የውኃ መጥለቅለቅ ቤታቸው እስከ ወገቡ የተዋጠው የገበሬ ቤተሰብ የሆኑት የጂቼ ጀልሚዳ እና ባለቤታቸው ከአንድ ቀን በፊት በአቅራቢያቸው ቤቶች ውስጥ ገብቶ በርቀት ያዩት ጎርፍ በቀጣይ የእነሱን ቤት ውጦ ሕይወታቸውን ለማዳን ከጣራው ላይ ለመውጣት አስገድዷቸው ነበር።

ደቡብ ብራዚል
በደቡባዊ ብራዚል ቤቶች በውኃ ተውጠው ታይተዋል። ምስል Renan Mattos/REUTERS

«አንዳንድ ሰዎች ከዚህ የበለጠ ንብረት አጥተዋል፣ ቤቶቻቸውን እንዲሁም ቤተሰቦቻቸውንም ያጡ አሉ። ምንም እንኳን ወተት መሸጣችንን ብናቆምም እኛ ደህና ነን፤ እንስሶቻችንም አሉ። ምግብ የለንም ግን ደግሞ ቀስ በቀስ እናገግማለን። በመጀመሪያ ምንም አልነበረንም፤ ወደፊትም ልናጣ እንችላለን፤ ግን እንደገና እንጀምራለን።»

በመካከለኛው ምሥራቅ

ጎርፍ ብራዚል ላይ መደጋገሙን ተከትሎ ይጥና እንጂ ለወትሮው ደረቅ የአየር ሁኔታ ባላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራትም ውስጥም መከሰቱ እየታየ ነው። በተለይም በሰው ሠራሽ ስልት ሳይሆን አይቀርም በሚል ግምት የተሰነዘረበት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትን ለቀናት ያጥለቀለቀው ዝናብና ጎርፍ መንስኤ የዓለም የሙቀት መጠን መጨመር እና ደን እየተመነጠረ የከተሞችም መስፋፋት ያስከተለው መዘዝ እንደሆነ የወጡ ጥናቶች አመላክተዋል። በኃይለኛ ነጎድጓድና መብረቅ የታጀበው ዝናብ በሞቃቷ የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገር ለቀናት የነዋሪዎቿን እንቅስቃሴ እንደገታ ታይቷል። ኦማንም በተመሳሳይ ጎርፍ ጉዳት ካደረሰባቸው የአረብ ሃገራት አንዷ ናት። አፍሪቃ ውስጥ ደቡብ አፍሪቃ እና ኬንያ ውስጥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የበርካቶች ሕይወት መቀጠፉ ተነግሯል።

ጎርፍ በጀርመን

ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ ችግር ካስተከተለባቸው ሃገራት ጀርመንም ትጠቀሳለች። ከሳምንት በፊት በተለይ በደቡባዊ ጀርመን ባየርን ፌደራል ግዛት ጎርፍ በርካቶች ቤታቸውን ጥለው ወደሌላ ስፍራ እንዲሄዱ አስገድዷል። ኪውለንታል በተባለችው መንደር ከሚኖሩት መካከል የሆኑት ያልጠበቁት ተከስቶ ከመኖሪያ አካባቢያቸውና ቤታቸው ለመፈናቀል የተገደዱት ዛቢነ ፊሸር ሁኔታውን እንዲህ ነው የገለጹት።

«ትናንት ምሽት ከሌላው ቀን የተሻለ ሰላማዊ ነበር። ከአካባቢያችን መልቀቅና መውጣት እንደሚርብንም አላሰብንም። ምሽቱን ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት ጀምሮ ግን ትንሽ አሳሳቢና ውጥረት የበዛበት ሁኔታ ነበር። ሰዎች ከቤታቸው እስኪወጡ፣ እንዲሁም እዚህ እስኪደርሱ፣ እናም አሁን ደግሞ ከማለዳ 11 ሰዓት ጀምሮ እዚህ ተቀምጠናል፤ ዛሬውን ወደቤታችን መመለስ እንችል እንደሆነም አላወቅንም።»

ዱባይ ጎርፍ
መንገዶችን ድንገት የዋጠው ጎርፍ በዱይምስል Amr Alfiky/REUTERS

በደረሰው የጎርፍ አደጋ ቢያንስ የአራት ሰው ሕይወት ጠፍቷል፤ የገቡበት አልታወቀም እንዳሉ ተገልጿል። ኃይለኛው ዝናብ ወንዞች ሞትለው ከገደባቸው ውጪ እንዲፈሱ አድርጓል። አስቀድሞ ሁኔታውን በመገመት የጎርፍ መከላከያዎችን ለመግባት ጥረት ቢደረግም የመጣው ውኃ ከተገመተው በላይ መሆኑን የኖርደንዶርፍ ከንቲባ ቶቢያስ ኩንዝ ተናግረዋል።

«በትናንትናው ዕለት ወደ 40,000 የሚጠጉ ከረጢቶችን በአሸዋ ሞልተን የጎርፍ መከላከያ ግድቡን ለማጠናከር ተጠቅመናል። ከድንጋይ፣ ከእንጨት ሳጥን እንዲሁም ከጎማ መጋረጃም 240 ሜትር ርዝመት ያለው የራሳችንን አዲስ የጎርፍ መከላከያም ገንብተናል። የጎርፍ መከላከያው በመጨረሻ በጥቂቱ ረድቷል፣ ነገር ግን ዛሬ ውኃው በጣም ከመጠን በላይ በመሆኑ በቂ አልነበረም። እቅዶቹ ሁሉ ይጠቅማሉ ተብለው የታሰቡ ነበሩ፤ ግን እንዲህ ላለው ጎርፍ አልተዘጋጁም።»

በደቡባዊ ጀርመን በጎርፍ ከተጥለቀለቁት አካባቢዎች ራይሸርስሆፈን የተሰኘችው ስምንት ሺህ ገደማ ነዋሪዎች ያሏት አነስተኛ ከተማ ክፉኛ ከተጎዱት መካከል ናት። ከዚህ ቀደም ለአካባቢው ውበትን ሕይወት ሰጥተው በጸጥታ ሲወርዱ የሚታወቁት የዳኑብ ወንዝ ገባር የሆኑት ሁለት ወንዞች በአደገኛ ሁኔታ ከመጠን በላይ ሞልተው ከገደባቸው በማለፋቸው በአካባቢው የሚገኝ ግድብን ሳይቀር በማፍረሳቸው ነው ኅብረተሰቡን ለመፈናቀል የዳረገው። 

የጀርመን ባለሥልጣናት ምላሽ

ፕላስቲክ ቦት ጫማ ተጫምተው በጎርፍ አደጋ ወደተጎዳው አካባቢ ፈጥነው የደረሱት የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ በኗሪዎች ላይ የደረሰውን ችግር ለማቅለል መንግሥታቸው የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

«የተፈጥሮ ኃይሎች ግዙፍ ናቸው፤ በጣምም ጠንካራ በመሆናቸው ታላቅ ውድመት ሊያደርሱ ይችላሉ። በተለይ ደግሞ ጎርፍ፤ እንዲህ ካለ አደጋ የመከላከል ዘመቻ በተካሄደባቸው አካባቢዎች ስገኝ ይህ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ከፌደራል መንግሥት በኩል ያለውን ተጠቅመን እርዳታ በአስቸኳይ እንዲር,ስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።»

የመራሔ መንግሥቱም ሆነ የሌሎች ትላልቅ የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በአካባቢው መገኘታቸው የችግሩን አሳሳቢነት ያመለክታል ነው የተባለው። በተጠቀሰው አካባቢ ከቀናት በኋላ ውኃው እየቀነሰ መምጣቱ የሚታይ ቢሆንም በቀጣይም ዝናብ ሊመጣ ያውም መጠኑ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ግን ከወዲሁ እየተገመተ ነው።  የባየርን ፌደራል ግዛት ጠቅላይ ሚኒስትር ማርኩስ ዞደር በጎርፍ ምክንያት ከአካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ወገኖች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ከወዲሁ ስጋታቸውን ተናግረዋል።

ደቡብ ጀርመን ጎርፍ
የጀርመን መራሄ መንግሥት ኦላፍ ሾልስ ጎርፍ ከመኖሪያ ቤታቸው ያፈናቀላቸውን ወገኖች ለማነጋገርና ለማጽናናት በስፍራው ፈጥነው ነበር የተገኙት። ምስል Lukas Barth/AFP via Getty Images

«በአንዳንድ ቦታዎች ውኃው እየጎደለ የማጽዳቱ ሥራ ቢጀምርም ሁኔታው አሁንም አሳሳቢ ነው። ግድቦች እየፈረሱ፤ አዲስ ጎርፍ እየመጣ፣ ብዙ መፈናቀልም እያየን ነው። በአሁኑ ጊዜ ከሦስት ሺህ በላይ በጎርፍ ከተጎዳው አካባቢ እየወጡ ነው፤ ቁጥሩም እየጨመረ ነው።»

አውሮጳ ውስጥ ከሩሲያው ቮልጋ ወንዝ ቀጥሎ በትልቅነቱ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ዳኑብ ወንዝ በማዕከላዊ እና ደቡብ ምሥራቅ የአውሮጳ ሃገራት ይፈሳል። በደቡባዊ ጀርመን ጫካዎቹን አቆራርጦ የሚዘልቀው ወንዝ በጀርመን ግዛት ውስጥ ከሙላቱ አሁን ቢቀንስም በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ኦስትሪያ ውስጥ የዘነበው ከባድ ዝናብ ያስከተለው ጎርር በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ ችግር አስከትሏል። በትናንትናው ዕለትም የሀገሪቱ ጦር ኃይል አባላት ምሥራቃዊ ኦስትሪያ ግዛት በጎርፍ ምክንያት ለችግር የተጋለጠውን ኅብረተሰብ ለመርዳት መሰማራታቸው ነው የተገለጸው።

 

የተባባሰው የአየር ጠባይ ሁኔታ በ2024 ዓም

ባለፉት አምስት ወራት ከኃይለኛ ዝናብና ጎርፍ በተጨማሪ በአንዳንድ ሃገራት የሙቀት ማዕበልም ተከስቷል። በሚያዝያ እና ግንቦት ወራት ሕንድ እና አብዛኞቹ የእስያ ሃገራት ነዋሪዎች በከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ሲሰቃዩ ነው የከረሙት። እንደውም ሕንድ ውስጥ እስከ 47 ዲግሪ የደረሰው የሙቀት መጠን በሀገሪቱ በተካሄደው ምርጫ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማስከተሉ ነው የተሰማው። መራጮችም ሆኑ የምረጡኝ ቅስቀሳ የሚያደርጉ ፖለቲከኞች ለህመም መዳረጋቸው ተዘግቧል። በርካቶችም የሙቀት ማዕበሉ የአየር ንብረት ለውጥ ነጸብራቅና ውጤቱ ነው እያሉ ነው።

የሙቀት ማዕበል በፓኪስታን
ከፀሐይ ቃጠሎ የተሸሸጉት የፓኪስታን ወጣቶች በሞተር ብስክሌት ሲጓዙፎቶ፤ የሙቀት ማዕበል በፓኪስታን ምስል Akhtar Soomro/REUTERS

እርግጥ ነው በአየር ጠባዩ ምክንያት የሚከሰቱት ኃይለኛ ጉልበት ያላቸው የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያደርሱት ጉዳት እንደየኅብረተሰቡ የአቅም ሁኔታ የሚመዘን ነው። ጠንካራ ኤኮኖሚ ያላቸው ሃገራት በቶሎ የማገገም ዕድሉ ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል። በአንጻሩ ውቅያኖስን ከውስጡ ሰቅስቆ ወደ የብስ የመገልበጥ፣ ሕንጻዎችን እንደዛፍ የመገንደስ እና የመሳሰሉትን ኃያል አቅም ያለውን የተፈጥሮ አደጋ የሚያስተናግዱ የበለጸጉ ሃገራትንና የጎርፍ መውረጃ ቱቦዎች በመደፈናቸው ምክንያት በቀናት ዝናብ መጠነኛ ጎርፍ መኖሪያ አካባቢዎችን የሚያጥለቀልቅባቸውን የአፍሪቃ ሃገራት ጉዳት ማነጻጸር በቂ ነው። በእነዚህ ሃገራት ተፈናቃዮች ሊገጥማቸው የሚችለውን መገመት ይበቃል። ለዚህም ነው የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖው ከባድ ጉዳት እያስከተለባቸው ለሚገኘው አዳጊ ሃገራት በቂ ድጋፍ እንዲደረግ የሚጠየቀው።

የያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የዓለም የሙቀት መጠን እየጨመረ ለመሄዱ ማመላከቻዎች የታዩበት፤ የተፈጥሮ አደጋዎችም ክስተት ከመነሻው ጎልቶ የተከሰተበት መሆኑ እየተነገረ ነው። በቀጣይ ወራት ይሻሻል ይብስ እንደሁ ከኖርን የምናየው ይሆናል።

 ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ