በቡርኪና ፋሶ ጥቃት ሰዎች ተገደሉ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2011ማስታወቂያ
በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶ ዉስጥ በሚገኝ አንድ ቤተ-ክርስትያን ላይ በደረሰ ጥቃት አምስት ሰዎች ተገደሉ። የሃገሪቱ ደኅንነት ቢሮ ዛሬ ይፋ ባደረገዉ መረጃ መሰረት ከሟቾቹ መካከል የቤተ-ክርስትያኒቱ አንድ ቄስ ይገኙበታል። ጆቦ ከሚባል ሰሜናዊ ቦርኪናፋሶ ከተማ 60 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘዉ ቤተ-ክርስትያን ላይ ለደረሰዉ ጥቃት አካባቢዉ ላይ የሚንቀሳቀሱት አክራሪ ሙስሊሞች መሆናቸዉ ነዉ የተነገረዉ። የፊታችን ረቡዕ የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ቡርኪና ፋሶን ጨምሮ ማሊን እና ኒጀርን ለመጎብኘት ወደ ምዕራብ አፍሪቃ ይጓዛሉ። ባለፈዉ የካቲት ወር ጀርመንን የጎበኙት የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ሮህ ማርክ ካቦሬ አሸባሪነትን ለመዋጋት በቅርበት የትብብር ሥራ ለመስራት መስማማታቸዉ ይታወሳል።
አዜብ ታደሰ
እሸቴ በቀለ