1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በበጀት አዙሪት ውስጥ የሚገኘው የደቡብ ክልል

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

በደቡብ ክልል በተለያዩ አካላት እጅ ይገኛል የተባለው 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የማዳበሪያ ዕዳ በኮማንድ ፖስት የዕዝ ሠንሰለት ለማስመለስ እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ፡፡ ቢሮው እርምጃውን መውሰድ የጀመረው የእዳው ተመላሽ አለመሆን በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ክፍያና በልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅኖ በማሳደሩ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4SDCU
Teferi Abate Head SNNPRS  Finance
የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

የክልሉ መንግሥት በአንድ ወር ውስጥ በስምንት ዞኖችን ኦዲት ለማድረግ ዝግጅቱን አጠናቋል

በደቡብ ክልል በተለያዩ አካላት እጅ ይገኛል የተባለው 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ የማዳበሪያ ዕዳ በኮማንድ ፖስት የዕዝ ሠንሰለት ለማስመለስ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታወቀ ፡፡ ቢሮው እርምጃውን መውሰድ የጀመረው የእዳው ተመላሽ አለመሆን በክልሉ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ክፍያና በልማት ሥራዎች ላይ አሉታዊ ተፅኖ ማሳደሩን ተከትሎ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የደቡብ ክልል መንግሥት አሁን ላይ የተቆለለበት የአፈር ማዳበሪ ዕዳ 4 ቢሊየን ብር ይጠጋል፡፡ ክልሉ ዓመታዊ በጀቱን በዋስትና በማስያዝ የወሰደውን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ በወቅቱ መመለስ አለመቻሉ  አሁን ለገባበት የበጀት ጉድለት ቅርቃር ምክንያት መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ ያልተከፈለ ዕዳ ታዲያ አሁን ላይ ክልሉ ለሠራተኞቹ ደሞዝ ለመክፍል እጅ እንዲጥረው አድርጎታል ፣ የልማት ሥራዎችንም ለማከናወንም ዳገት ሆኖበታል ነው የሚባለው ፡፡

የክልሉ መንግሥት በተለያዩ አካላት እጅ ይገኛል ያለውን ዕዳ ለማስመለስ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ መጀመሩን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ አስታውቋል፡፡ የክልሉ መንግሥት  ከዕዳ ማስመለስ ጋር በተያያዘ  በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በስምንት ዞኖች ውስጥ የኦዲት ተግባር ለማከናወን የሚስችለውን ዝግጅት ማድረጉን ነው የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ፡፡

Teferi Abate Head SNNPRS  Finance
አቶ ተፈሪ አባተ፤ የደቡብ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዋናነት ከ2005 እስከ 2010 ዓም ድረስ የተከናወነውን የአፈር ማዳበሪያ ሽያጭ በተደራጀ አካሄድ ኦዲት ለማድረግ ዝግጅት ተደርጓል ያሉት የቢሮው ኃላፊ “ የእጅ በእጅ ሽያጭ እንዲከናወን ከተወሰነ ወዲህ ያለውን ደግሞ በክልል ፣ በዞኖችና በልዩ ወረዳዎች ደረጃ ተሽጦ ገቢ ያልተደረገው ገንዘብ የት ነው ያለው የሚለው ኦዲት የሚደረግ ይሆናል ፡፡ ይህንንም አንድ ወር ባነሰ ግዜ ውስጥ ለማከናወን አቅደንል ወደ ሥራ እየገባን እንገኛለን  “ ብለዋል፡፡

ዕዳውን የማስመለሱን ሂደት ሥኬታማ ለማድረግ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ የኮማድ ፖስት ወይንም የዕዝ ሠንሰለት መዋቅር መዘርጋቱን የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ተናግረዋል፡ከተጠያቂነት አንጻር ሂደቱን ለማስስተጓጎል የሚሞክር ማንኛውም አካል በህግ አግባብ እርምጃ የሚወሰድበት ይሆናል ያሉት ኃላፊ “  ለዚህም ዕዳውን የማስፈጸሙ ሂደት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት እና የክልሉን ፍትህ ቢሮ ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት በተውጣጣ ኮማንድ ፖስት እንዲመራ ተደርጓል ፡፡ የኮማንድ ፖስቱ ዋና ዓላማ ገንዘቡን ማስመለስ ነው ፡፡ የሚፈለግባቸውን ገንዘብ በሚያሸሹ ወይም ራሳቸውን ሊያሸሹ በሚሞክሩ አካላት ላይም የተጠናከረ ክትትል ይደረጋል፡፡ ያለባቸውን ዕዳ ሲመልሱም እጃቸው ላይ ካቆዩበት የወለዱ መጠን ጋር የሚመልሱ ይሆናል  ›› ብለዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ደገላ ኤርገኖ የደቡብ ክልልን ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች በቅርበት ከሚከታተሉት የዘርፉ ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው ፡፡ ክልሉ አሁን ላይ ከአፈር ማዳበሪያ ዕዳ አመላለስ ጋር በተያያዘ ባጋጠመው የበጀት መዛባት  ዙሪያ በዶቼ ቬለ DW አስተያየታቸውን የተጠየቁት ዶክተር ደገላ የበጀት ክፍተቱ በቶሎ መፍትሄ ካላገኘ በክልሉ ላይ ምጣኔ ሀብታዊና ፖለቲካዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳላቸው ተናግረዋል ፡፡

በክልሉ መመለስ የነበረበት ዕዳ ወደ መንግሥት ቋት አለመግባቱ ክልሉ ጤናማ በሆነ የበጀት ሥረዓት ውስጥ እንዳይገኝ እንዳደረገው የጠቀሱት ዶክተር ደገላ “ ይህ ሁኔታ አይደልም አንገብጋቢ የድህንት ቅነሳ ሥራዎችን ለማከናወን ቀርቶ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች  ለሠራተኞች ደሞዝ መክፈል የማይችልበት ደረጃ ላይ ሊያደርሰው ችሏል ፡፡ የበጀት ክፍተቱን በቶሎ ማስተካከል ካልተቻለ በክልሉ ላይ ተጨማሪ ፖለቲካዊ ተፅኖ ሊያሳድር ይችላል ፡፡ምክንያት ሁኔታው ግብር እየከፈሉ ልማት ያላገኙ ዜጎችን ቅሬታ ውስጥ የማስገባት ዕድሉ ሠፊ ነው ፡፡ ይህም በጊዜ ሂደት አስፈጻሚውን አካል ፖለቲካዊ ጫና ውስጥ ሊከተው ይችላል “ ብለዋል ፡፡ 

በቀጣይ የክልሉ ምክር ቤትና አስፈጻሚው አካል የተጣለባቸውን ሃላፊነት ሊወጡና ተጠያቂነትን ሊያሰፍኑ ይገባል ያሉት የምጣኔ ሀብት መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ደገላ በተለይ በዕዳ አመላለስ ሂደቶችም ሆነ ለወደፊቱ በሚኖረው የበጀት አስተዳደር ሥራ ላይ ክልሉ በፋይናንስ ህግና ደንብ ብቻ እንዲመራ በማድረግ ከችግሩ ሊወጣ የሚችልበት ዕድል መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ነጋሽ መሐመድ