1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐይማኖት ተቋማትን መልሶ ግንባታ

ሰኞ፣ ግንቦት 1 2014

በስልጤ ዞን በቅርቡ ቃጠሎ ደርሶባችው የነበሩ የእምነት ተቋማትን መልሶ የመገንባት ሥራ መጀመሩን የዞኑ መስተዳድር አሰታወቀ ፡፡ በኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሐዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ግን ወደ ዞኑ እንዳልገባ በመከለከሌ መልሰው ይገነባሉ ሥለተባሉ ቤተ ክርስቲያናት መረጃው የለኝም እያሉ ነው ፡፡

https://p.dw.com/p/4B1pd
Äthiopien Silte-Zone
ምስል Silte Zone Government Communication Affairs

ከሳምንታት በፊት በጎንደር የእስልምና ሀይማኖት ተከታዮች ላይ ደርሷል የተባለውን ጥቃት ተከትሎ በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማና በሳንኩራ ወረዳ በሚገኙ ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት መፈፀሙ ይታወሳል፡፡ በየአካባቢዎች የተጀመሩ የተቃውሞ ሠልፎች ወደ ሁከት በማምራታቸው በአንድ የኘሮቴስታንትና በአራት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያናት ላይ በሙሉና በከፊል ጉዳት ደርሶ እንደነበር የጠቀሰው የሥልጤ ዞን መስተዳድር አሁን ቤተ እምነቶቹን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡

በዞኑ መስተዳድር ሰብሳቢነት በተቋቋመው የመልሶ ግንባታ ኮሚቴ አማካኝነት የጥሬ ገንዘብና የቁሳቁስ ሀብቶችን የማሰባሰብ ሥራዎችን በማከናወን ወደ ሥራ መገባቱን የዞኑ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ከድር አብደላ ለዶቼ ቬሌ DW ገልፀዋል፡፡

Äthiopien Silte-Zone
ምስል Silte Zone Government Communication Affairs

የስልጤ ዞን የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት ኘሬዝዳንትና የዞኑ የሃይማኖቶች ህብረት ሰብሳቢ ሀጂ መሀመድ ከሊል በበኩላቸው መጥፎ ነገርን በመጥፎ መመለስ ሥህተት እንደነበር በመጥቀስ የጠፋውን ንብረት ወደ ቦታው በመመለስ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በሥልጤ ዞን የወደሙ ቤተክርስቲያናትን መልሶ ለመገንባት በተጀመረው እንቅስቃሴ ዙሪያ ዶቼ ቬሌ DW ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀድያና የስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መላከ ሕይወት ቄሲስ ንጉሴ ባወቀ በበኩላቸው ወደ ዞኑ እንዳልገባ በመከልከሌ መልሰው ይገነባሉ ስለተባሉት ቤተ ክርስቲያናት መረጃው የለኝም ብለዋል፡፡

የአገረ ስብከት ሥራ አስኪያጁ ባቀረቡት ቅሬታ ዙሪያ የተጠየቁት የሥልጤ ዞን መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሃላፊ አቶ ከድር አብደላ ‹‹ ሥራ አስኪያጁ ወደ ዞኑ እንዳይገቡ የከለከላቸው አካል የለም ፤ ቅሬታዎች ካሉም ዞኑ ተቀራርቦ በመወያየት ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ልደት አበበ
ማንተጋፍቶት ስለሺ