1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ወለጋ 16 ሰዎች መታገታቸዉ ተረጋገጠ

ሰኞ፣ ጥቅምት 21 2015

የምዕራብ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ 16 ሰዎች መታገታቸውን አረጋግጠ። እስካሁን ከታገቱት መካከል የተለቀቀ ሰዉ የለም፤ ተብሏል። በአካባቢው የፀጥታ ችግር መኖሩንና የታጣቂዎች አንቅሰቀሴም እንዳለም ገልጸዋል፡፡ መንዶኞቹ ከአሶሳ ከተማ ወደ ካማሺ እያቀኑ እንደነበርም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/4It9k
Karte Dodola Ethipia AM

እገታ በምዕራብ ወለጋ

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ  በምዕራብ ወለጋ  ውስጥ በምትገኘው ቤንጉዋ በተባለች ስፍራ በአንድ ተሸከርካሪ ላይ የነበሩ  ከ16 በላይ  ሰዎች  በታጣቂዎች መታገታቸው ተገለጸ፡፡ መንዶኞቹ ከአሶሳ ከተማ ወደ ካማሺ እያቀኑ እንደነበርም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሀሚድ ተናግረዋል፡፡  እስካሁን ከታገቱት መካከል የተለቀቀ ሰው አለመኖሩንም አክለዋል፡፡ የታገቱት ሰዎች በብዛት ተማሪዎች እንደሆኑ አንድ ወንድማቸው መታገቱን የነገሩን የካማሺ ከተማ ነዋሪም ጠቁመዋል፡፡ ቤንጉዋ የተባለች ከተማ ከአሶሳ ዞን ባምባሲ ወረዳ 30 ኪ.ሜ ፣ ከምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማም 20 ኪ.ሜ ትርቃለች፡፡ 
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከታገቱት መካከል ወንድማቸው እንደሚገኝበት የነገሩት አንድ የካማሺ ከተማ ነዋሪ የታገቱት ከአሶሳ እየተመለሱ ባሉበት ወቅት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤንጉዋ በተባለች ስፍራ ሲደርሱ በታጣቂዎች አሸከርካሪውን ጨምሮ በርካቶች መታገታቸውንና እስካሁን የደረሰቡት እንደማይታወቅም አብራርተዋል፡፡ በዕለቱ ሀገር አቀፍ ፈተና ወሰድው  እየተመሰሉ የነበሩ ብዙ ተማሪዎች እንደሚገኙበትም ጠቁመዋል፡፡ 
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሳ ሀሚድ ከ16 በላይ ሰዎች መታገታቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል፡፡ ሰዎቹ ከአሶሳ ለጤና ተቋም መድኃኒትና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጭኖ ወደ ካማሺ ሲያቀና በነበረው ተሽከርካሪ ላይ እንደነበሩ አመልክተዋል፡፡  የተጫነው መድኃኒትም በታጣቂዎች መወሰዱንና የታገቱትን ለማስለቀቅ የጸጥታ ኃይሎች ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው  ተኩስ እንዳለ ገልጸው እስከ ዛሬው ዕለት የታገቱት ሰዎች አድራሻ አለመገኘቱን  አቶ ሙሳ አክለዋል፡፡ በዕለቱ በርካታ ተሸከርካሪዎች በእጀባ ወደ ካማሺ መሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡
የምዕራብ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ደበላ ኦላና ሰዎች መታገታቸውን አረጋግጠው  ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ በአካባቢው የፀጥታ ችግር መኖሩንና የታጣቂዎች አንቅሰቀሴም እንዳለም ገልጸዋል፡፡ 
«ሰዎች መታገታቸውን ሰምተናል፡፡ ቆቆራ ጉራቲ በሚባል ቦታ ላይ  ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች በመኪና እየሄዱ የመታገታቸው መረጃ ደርሶናል፡፡ መረጃው ከደረሰን ጊዜ ጀምሮ ክትትል እየተደረገ ነው፡፡ ምን ያህል ሰው ነው፣ ማን ናቸው የሚልና የደረሰ ጉዳት ካለ እስካሁን የደረሰንም ሆነ ያገኘው ተጨባጭ መረጃ የለም» ብለዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ጥቅምት 17/2015 ዓ.ም ከታገቱት በብዛት ተማሪዎች እንደሆኑም ተገልጸዋል፡፡ በዚህ በምዕራብ ኢትየጵያ አልፎ አልፎ በሚከሰቱት የጸጥታ ችግሮች ከዚህ ቀደም በተደጋሚ በሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ቆይተዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በደረሱት ጥቃቶችም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸውንና የሰው ህይወት ማለፉም ሲዘገብ ቆይተዋል፡፡


ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር
ሽዋዬ ለገሠ