1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ወለጋ ታጣቂዎች 24 ሰዎች መግደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

ሰኞ፣ ጥቅምት 7 2015

በወረዳው ለአንድ ዓመት ያህል መንገድ መዘጋቱንና የጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ለDW ተናግረዋል፡

https://p.dw.com/p/4IHYW
Äthiopien | Wahlen | Oromia

በምስራቅ ወለጋ 24 ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ

በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ  ሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ማታ የታጠቁ ሀይሎች 24 ሰዎችን መገደላቸውንና  እና በንብረት ላይም ጉዳት ማድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በወረዳው ቦቃ በተባለች ቦታ ብዙ ሰዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡ በኪረሙ ወረዳ በተለያዩ ጊዜ በሚደርሱ ጥቃቶች በአካባቢው የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች በፋኖ ስም የሚንቀሳቁ ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ ሲያደርጉ የአማራ ተወላጆች ደግሞ የሼነ (የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት) ብሎ ራሱን የሚጠራን ቡድን ተጠያቂ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ በወረዳው ቅዳሜ ማታ ላይ በደረሰው ጥቃት 16 ሰዎች ህይወት ማለፉን የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደርም ለዶቼቬለ አመልክተዋል፡፡ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋሪ ነጋራ ቅዳሜ ማታ "ጽንፈኛ ታጣቂዎች" ጉዳት አድርሰዋ ሲሉ  ተናግረዋል፡፡
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳን ጨምሮ 13 በሚደርሱ ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር  ከ2 መቶ ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ቆይቷል፡፡ በተደጋጋሚ ታጣቂዎች ጥቃት ሲያደርሱበት የነበረው ኪረሙ ወረዳ ባለፈው ቅዳሜም ጥቅምት 5/2015ዓ.ም በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በወረዳው ጨፈ ሶራማ እና ጉድና ሶራማ በተባሉ ቦታዎች ላይ  የቁም እንስሳት መዘፋቸውና ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገልጸዋል፡፡  በወረዳው ከተማ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈናቀሉ ሰዎች ተጠልለው እንደሚገኙም ከአካባቢ ነዋሪዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
በወረዳው ለአንድ ዓመት ያህል መንገድ መዘጋቱንና የጸጥታ ችግር ውስጥ መቆየታቸውን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ ለDW ተናግረዋል፡፡ በመንገድ መዘጋት ምክንያትም የታመሙትን ወደ ተሻለ ህክምና መውሰድ እንደተሳናቸውና ሰብአዊ ድጋፍ በወቅቱ እየመጣ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከወረዳው ከተማ ራቅ ካሉ ቀበሌዎች በስጋት ምክንያት ሰዎች ወደየ ከተማው መሸሻቸውንም አክለዋል፡፡
የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዋቅጋ ነገራ በዞናቸው ስር በሚገኘው ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ቅዳሜ ማታ በደረሰው ጥቃት በተለይም በሁለት ቀበሌዎች ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ደርሰዋል ብሏል፡፡ እስካሁን በተደረገው ማጣራት 16 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 3 ሰዎች ደግሞ መቆሰላቸውን ተናግረዋል፡፡ የጸጥታ ሀይሎች ጉዳዩን እየተከታቱ ሲሆን የጉዳት መጠኑ ሊጨምር እንደሚችልም ዋና አስተዳዳሪው አመልክተዋል፡፡ በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል  የተባለ ሲሆን የተፈናቀሉ ዜጎችን ቁጥርም በመጠለያ ጣቢያ ሲመዘገቡ የሚገለጽ እንደሆነም አክለዋል፡፡ ኪራሙ ወረዳ  ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ የተባለ ወረዳ ጋር የሚዋሰን ሲሆን  ታቂዎቹ በቡሬ በኩል በመሻገር ጥቃት እንደሚፈጽሙም ገልጸዋል፡፡ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን እና የዜጎችን ደህንነት ለመጠበቅ የጸጥታ ሀይሎች በሁሉም ስፍራዎች ተሰማርተው እንደሚገኙም ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳ ባለፈው ዓመት በነበረው የጸጥታ ችግር 70ሺ የሚደርሱ ዜጎች ተፈናቅለው እንደነበር ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ ጊዜ ባወጣቸው ዘገባዎች በምዕራብ አሮሚያ የጸጥታ ስጋት መኖሩንና ትኩረት እንደሚሻ እንዲሁም የዜጎች የመኖር መብት እንዲጠበቅ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ