1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በደቡብ ክልል የዞኖች በክልል የመደራጀት ጥያቄ

ዓርብ፣ ሐምሌ 15 2014

ከጌዲኦ እና ከጉራጌ ዞኖች የተወከሉ የም/ቤት አባላት << የመዋቅር ጥያቄ የአብዛኞቹ ማሕበረሰብ ክፍል ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩ የግጭትና የአለመረጋጋት መንስኤ እየሆነ ይገኛል፡ ፡እስከአሁን ምላሽ ባለመሰጠቱ የተነሳም በመረጠን ሕዝባችን ፊት ለመቆም ተቸግረናል >> ብለዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4EWNC
Äthiopien Hawasa | Parlament der SNNPR
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በመረጠን ሕዝባችን ፊት ለመቆም ተቸግረናል

የደቡብ ክልል መንግሥት ምክር ቤት አባላት የዞን ምክር ቤቶች ላቀረቡት በክልል የመደራጀት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጠየቁ፡፡ አባላቱ ጥያቄያቸውን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ነው ፡፡ እዚህ የመጣነው የወከለንን ህዝብ ድምፅ ለማሰማት ነው ያሉት የምክር ቤቱ አባላት የአደረጃጀት ጥያቄው አልባት ባለማግኘቱ ለግጭትና አለመረጋጋት ምክንያት እየሆነ ይገኛል ብለዋል ፡፡

የመዋቅር ጉዳይ ለፀጥታ መደፍረስና ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆን የለበትም ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው በበኩላቸው የክልሉ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን በውይይት ፣ በሰከነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡  

በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው  የደቡብ ክልል ም/ቤት 6ኛ ዙር 2ኛ ዓመት መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርዕስቱ ይርዳው  የመንግሥታቸውን ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በግብርናና በጤና ፣ በመሠረተ ልማት ግንባታና እንዲሁም በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ተከናውነዋል ያሏቸውን ሥራዎች ለም/ቤቱ አቅርበዋል ፤ ከአባላቱ ለተነሱላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በአባላቱ የተነሱት ጥያቄዎች አብዛኞቹ ማለት ይቻላል በአስተዳደራዊ መዋቅር አደረጃጀት ላይ ያተኮሩ ነበሩ፡፡

በተለይ ከጌዲኦ እና ከጉራጌ ዞኖች ተወክለው መምጣታቸውን የገለፁት የም/ቤት አባላት << የመዋቅር ጥያቄ የአብዛኞቹ ማሕበረሰብ ክፍል ጥያቄ ነው፡፡ ጉዳዩ የግጭትና የአለመረጋጋት መንስኤ እየሆነ ይገኛል፡ ፡እስከአሁን ምላሽ ባለመሰጠቱ የተነሳም በመረጠን ሕዝባችን ፊት ለመቆም ተቸግረናል >> ብለዋል ፡፡

Äthiopien Hawasa | Parlament der SNNPR
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

ርዕስ መስተዳድር ርዕስቱ ይርዳው ከአባላቱ ለተነሱት ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ የመዋቅር ጉዳይ ለፀጥታ መደፍረስና ለሰው ሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆን እንደሌለበት በመጥቀስ የክልሉ መንግሥትና ገዢው ፓርቲ ጥያቄውን በውይይት ፣ በሰከነ እና በተረጋጋ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡

የምናራምደው አቋም እርስ በእርሱ የሚጣረስ ሊሆን አይገባም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ‹‹  በእንድ በኩል ወያኔ በብሄር ከፋፈለን እያል መልሰን ደግሞ ከእንድነትና ከትብብር ይልቅ በተናጠል ለመቆም የምናደርገውን አካሄድ ልናጤነው ይገባል ›› ብሏል፡፡

ም/ቤቱ በርዕሰ መስተዳድሩ በቀረበው የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ተጨማሪ ውይይቶችን ካደረገ በኋላ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል፡፡

ም/ቤቱ በተጨማሪም በክልሉ የ2015 ዓ.ም. የሥራ ዕቅድ ላይ በመወያየት ለእቅዱ ማስፈፀማያ ከ46 ነጥበ 3 ቢሊዬን ብር በጀት አጽድቋል ፤ የተለያዩ ሹመቶችንም ሰጥቷል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
 ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ነጋሽ መሐመድ