1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶማሌ እና አፋር ክልሎች ተፈጸመ ባሉት ጥቃት አንዱ ሌላውን ከሰሱ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 19 2013

የሶማሌ እና የአፋር ክልላዊ መንግሥታት ሰላማዊ ሰዎች ተገድለውበታል ባሉት በአዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጸመ ጥቃት አንዱ ሌላውን ወንጅለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው በሶማሌ ክልል መግለጫ መሠረት በሲቲ ዞን በአፍደም ወረዳ ሲሆን በአፋር ክልል መግለጫ ደግሞ በገዋኔ ወረዳ ነው። ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉ እና እንደቆሰሉ ሁለቱም ያሉት ነገር የለም።

https://p.dw.com/p/3nHgG
Somalia Äthiopien Viehzucht-Nomaden
ምስል DW/J. Jeffrey

የሶማሌ እና የአፋር ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች ሰላማዊ ሰዎች ተገድለውበታል ባሉት ጥቃት ሳቢያ መወነጃጀል ጀመሩ። የሶማሌ ክልል ትናንት እሁድ የአፋር ክልል ደግሞ ዛሬ ሰኞ በመንግሥት ኮምዩንኬሽን ቢሮ የፌስቡክ ገፆቻቸው በኩል ባወጧቸው መግለጫዎች በአዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጸመ ባሉት ጥቃት ሰዎች መገደላቸውን ገልጸው ለኩነቱ አንዱ ሌላውን ከሰዋል። 

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት በሲቲ ዞን በአፍደም ወረዳ ደን ለሔለይ ቀበሌ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን፣ ጉዳት መድረሱን እና ንብረት መውደሙን እሁድ ታኅሳስ 18 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። 

ክልሉ "የህወሓት ርዝራዦች፣ እጉጉማ የሚባሉት የአፋር አማፂያንና የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ተቀናጅተው" ፈጸሙት ባለው ጥቃት "ከባድ ጉዳት" ደርሷል ቢልም ምን ያክል ሰዎች እንደተገደሉም ሆነ እንደቆሰሉ ያለው ነገር የለም። 

የአፋር ክልል በበኩሉ ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ "በገዋኔ ወረዳ ፍሪትሊ እና ሪፎ ቀበሌ ላይ የሚገኙ በመንደር የተሰባሰቡ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ላይ" ትናንት እሁድ "ከሌሊቱ 11:00 ሰአት ጀምሮ ከዚህ ቀደም ይደርስ የነበረው መሰል የሽብር ጥቃት ደርሷል" ብሏል። የአፋር ክልል ልዩ ኃይል ጥቃት ፈጽሟል በሚል ከሶማሌ ክልላዊ መንግሥት የቀረበውን ክስ "ተራ ውንጀላ" ሲል አጣጥሏል። 

የአፋር ክልል "በዚህ ጥቃት በሁለቱም በኩል ስለደረሰው ኅልፈተ-ሕይወት" ሐዘኑን ቢገልጽም ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱ ያለው ነገር የለም። የአፋር ክልል "የተደራጁ የኢሳ ቡድን አባላት" ጥቃቱን ፈፅመዋል ሲል ከሷል። 

ሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች በሚቀሰቀሱ ግጭቶች እና በሚፈጸሙ ድንገተኛ ግድያዎች በተለይ ባለፉት ሁለት አመታት በተደጋጋሚ ሲወነጃጀሉ ቆይተዋል። 

የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት በአፋር እና በሶማሌ መካከል ለረዥም አመታት የዘለቀው ግጭት የተፈጥሮ ሐብት አጠቃቀም ላይ መሰረት ያደረገ ይሁን እንጂ ታሪክ፤ የወሰን አከላለል እና ፖለቲካ የራሳቸው ድርሻ አላቸው። ግጭቶቹን በውይይት ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት ያደረጓቸው ጥረቶች እስካሁን ዘላቂ መፍትሔ አላመጡም። ለዚህም አንዱ ሌላውን ይከሳሉ። 

ለሰላማዊ ሰዎች ሞት እና ለንብረት ውድመት መንስኤ የሚሆነውን ተደጋጋሚ ግጭት "ለማስወገድ ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ በመነጋገር መፍትሔ ለመስጠት" የተደረገው ጥረት አለመሳካቱን የገለጸው የሶማሌ ክልል ትናንት ባወጣው መግለጫ "ሕግ እና አሰራርን ተከትሎ የክልሉ ነዋሪ የሆኑ ንፁሃን ሰዎችን ህይወት ለመታደግና የንብረት ውድመትን ለመከላከል ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ" እንደሚወስድ አስታውቋል።

የአፋር ክልል በበኩሉ "በክልላችን ወሰን ዘልቆ ያስገባውን ልዩ ኃይል በአስቸኳይ እንዲያወጣና ለአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት ፀር የሆኑ ፀብ አጫሪ ኮንትሮባንዲስቶችና ሽብርተኞች ሽፋን ከመሆን እንዲታቀብ" የሚል ማሳሰቢያ ለሶማሌ ክልል ሰጥቷል።