1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሰብዓዊ መብቶችየመካከለኛው ምሥራቅ

ሳዑዲ አረቢያ ውሰጥ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ

ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016

በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች አሁን ድረስ እንደሚገኙ እዛው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ይናገራሉ። «ፍትሕ ለእስረኞች» ወይም «ድምፅ ሁኗቸው» የሚሉትም ብዙ ናቸው። የታሳሪ ቤተሰቦች እንደሚሉት አብዛኞቹ ታሳሪዎች ወጣቶች እና ወንዶች ናቸው።

https://p.dw.com/p/4ZeYe
ስደት ተመላሾች  አዲስ አበባ በሚገኘው የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አልጋዎች ላይ ቁጭ ብለው
ከስደት ተመላሾች አዲስ አበባ በሚገኘው የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ማዕከል - ህዳር 25 ቀን 2023ምስል Michele Spatari/AFP

ሳዑዲ አረቢያ ውሰጥ የታሰሩ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ

ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ላሉ ኢትዮጵያውያን ድምፅ ሁኗቸው የሚሉ ጥሪዎች አሁንም አላቆሙም። አልፎ አልፎም ከእዛው ከእስር ቤት በድብቅ የተቀረፁ ቪዲዮዎች በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ይለቀቃሉ። «ሹሜሲ እስር ቤት ነው የምንገኘው። ከ40 ሺህ የበለጥን ኢትዮጵያውያን ታስረን እየተሰቃየን እንገኛለን። 10 ወር ይሆነናል። ድምጽ ሁኔን» ይላል አንድ ኢትዮጵያዊ። 

ቪዲዮዎቹ ላይ በርካታ ወንዶች በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው እና መሬት ላይ ተቀምጠው ይታያሉ፤ እንዲሁ ሌላ ቪዲዮም ላይ እስር ቤት እንደሆኑ ገልጸው የኢትዮጵያን መንግሥት  ወደ ሀገራችን ይመልሰን ሲሉ ይማፀናሉ።  «እኛ ሀገራችንን እንወዳለን። ችግር ስለደረሰብን ብቻ አይደለም ሀገራችንን የምንወደው»

ለታሳሪዎች ድምፅ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን

ከእስር ቤት ውጪ ሆነው ድምፅ ሁኑዋቸው ከሚሉት ኢትዮጵያውያን መካከል ሳዑዲ አረቢያ ነዋሪ የሆነችው ሀኒ አንዷ ናት። ሀኒ ወንድሟ በእስር ላይ ስለሚገኝ ስለስቃያቸው ይመልጥ ታዉቃለች። «የሚሰማቸው፣ የሚረዳቸውም የለም። መሬት ላይ ፓንት ለብሰው ነው የሚተኙት። ወንድሜ ይነግረኛል» ትላለች።

እስር ቤት የገባው ህጋሚ የመኖሪያ ፍቃድ ስላልነበረው ነው። « አንድ ዓመት ሊሞላው ነው። እስካሁን አልተለቀቁም፤ ምን ይሁኑ ነው ይሙቱ ነው?» ስትል ትጠይቃለች።

በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች
ሳዑዲ አረቢያ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ታስረው በነበሩበት ወቅት ቢያንስ 10 ሰዎች መሞታቸውን ታሳሪዎች ተናግረዋልምስል Privat

ሀኒ እንደምትለው ወንድሟ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በህገ ወጥ መንገድ ከገባ በኋላ ነው የታሰረው « እንደመጣ ነው ድንበር ላይ የተያዘው።  እስካሁን ምንም አይነት ተቀያሪ ልብስ የለውም። ያለበት እስር ቤት በአሁኑ ሰዓት ብርድ አለ። ሊታመሙ ይችላሉ።»

ዳግም በህገ ወጥ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያን

ከዚህ ቀደም ዶይቸ ቬለ ካነጋገራቸው የሳዑዲ ስደተኞች መካከል በኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ዳግም በህገ ወጥ መንገድ በባህር ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተሰደዱ ይገኙበታል።

ሀኒ እንደምትለው ወንድሟ ግን በህገ ወጥ መንገድ ሲሰደድ የመጀመሪያው ጊዜ ነው። ምናልባትም የመጨረሻውም። « ተመልሰው የሚመጡ አሉ። ወንድሜ ግን አይፈልግም። ስቃይ አይቷል» ትላለች ሀኒ ወንድሟን በተመለከተ።

ሀኒ እንደገለፀችልን ወንድሟን በስልክ የምታገኘው አልፎ አልፎ እርስ ቤት ውስጥ ካለ የግድግዳ ስልክ ሲደውልላት ነው።  እሷ እንደምትለው ህጻናት ጭምር እስር ቤት ይገኛሉ። « ሁለት ልጆች አሉ። ሰባት ወራቸው ነው።» የምትለው ሀኒ ከእናታቸው ጋር በባህር ሲመጡ የታሰሩ መሆናቸውን ትናገራለች።

«የሀገሪቷን ህግ ሳይጥስ የሚታሰር ሰዉ የለም»

በጅዳ  ነዋሪ እንደሆኑ የገለፁልን አንድ ኢትዮጵያዊ እንደሚሉት ግን በሳዑዲ አረቢያ የሀገሪቷን ህግ ሳይጥስ የሚታሰር ሰዉ የለም።  « ሀገሩ ሰላም እና ፍቅር ያለው ነው። ህግን የጣሰ በህግ የሚጠየቅበት ሀገር ነው።  ስህተት ካለበት አጣርቶ ነው የሚለቀው። ዝም ብሎ ከሜዳ ተነስሮ የሚሰራ የለም። » የሚሉት እኝው ኢትዮጵያዊ አንዳንድ ሰዎች በሚለቁት  ቪዲዮ ላይ ሰዎች ተመርኩዘው እንደሚጮሁ ነው የሚናገሩት« ያንን ጩኸት ስንሰማ እኛም አብረን እንጮኸለን እንጂ እኛ ሌላ የምናውቀው ነገር የለም» ይላሉ። 

አንድ ኢትዮጵያዊት ተመላሽ  አዲስ አበባ በሚገኘው የአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) የመጓጓዣ ማዕከል ጊዜያዊ መታወቂያዋን አሳያለች
ከስደት ተመላሾች አዲስ አበባ በሚገኘው የአለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ማዕከል - ህዳር 25 ቀን 2023ምስል Michele Spatari/AFP

ራዲያ ሰው ቤት ተቀጥራ የምትሰራ ኢትዮጵያዊት ናት። «በፊት ነበር እንጂ አሁን ላይ በገፍ እየታፈሰ እስር ቤት የሚገባ ኢትዮጵያዊ የለም» ትላለች።  « በብዛት በኤምባሲ በኩል ወደ ሀገር ተሳፍረዋል። በፊት ግን በጣም እስር ቤት ውስጥ ስቃይ ስለነበር ተጋኖ ይሰማ ነበር» ራዲያ አሁን ላይ ያሉ እስረኞች በወንጀል እና ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ስለሌላቸው ብቻ የታሰሩ እንደሆኑ ትናገራለች» 

ሳዑዲ አረቢያ እስር ቤቶች ስለሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጎች ብዛት እና ይዞታ ለመጠየቅ  ሪያድና ጂዳ ወደሚገኙት የኢትዮጵያ ኤምባሲእና ቆንስላው ፅሕፈት ቤቶች በተደጋጋሚ ደዉለን ነበር። ይሁንና ስልኩ አልተነሳልንም።

ይህ ዝግጅት እስከተጠናቀረበት ጊዜም ምንም አይነት ምላሽ  ማግኘት አልቻልንም። ወደ ሀገር ለመሳፈር ለሚፈልጉና የጉዞ ሰነድ የሌላቸው በሳዑዲ አረቢያ  የሚገኙ ኢትዮጵያንን በተመለከተ  ግን «የኢትዮጵያ ኤምባሲ በሪያድ» ከሚለው የፌስ ቡክ ገፅ ለመረዳት እንደቻልነው ሰሞኑን የፓስፖርት (ሊሴፓሴ) እንዲሰጣቸው ሲጠባበቁ የነበሩ እና ስማቸው በይፋ የተዘረዘሩ ሰዎች በተጠሩበት ቀን እየሄዱ አሻራቸውን እንዲሰጡ እና እንዲወስዱ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።  

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ