1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ሰው ቅሬታውን በፆም በፀሎት መግለፁ ነገሩን ያስተነፍሰዋል እንጂ አይጎዳም»

ዓርብ፣ የካቲት 3 2015

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ባደረገዉ ጥቁር የመልበስ ጥሪ መሠረት ሰሞኑን በርካታ የዕምነቱ ተከታዮች ወይም አጋርነታቸውን መግለፅ የፈለጉ ሰዎች ጥቁር መልበስ መከልከላቸውን በተለያየ መንገድ ይፋ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ለመሆኑ አንድ መሥሪያ ቤት ጥቁር መልበስን መቼ ሊከለክል ይችላል? አጋርነትስ እንዴት ይገለፃል?

https://p.dw.com/p/4NJvY
Äthiopien | Orthodoxe Tewahedo-Christen
ምስል Seyoum Getu/DW

«ሰው ቅሬታውን በፆም በፀሎት መግለፁ ነገሩን ያስተነፍሰዋል እንጂ አይጎዳም»

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስን ጥሪ ተቀብለው ጥቁር የለበሱት አብዛኞቹ የዕምነቱ ተከታዮች ቢሆኑም የሌሎች እምነት ተከታዮችም ይህንን ሲያደርጉ ወይም ድጋፋቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል። ከእነዚህ መካከል ሙስሊሙ ባየ ሰይድ አንዱ ሲሆን የሚኖረው ደግሞ ሰሜን ወሎ ነው። «አጋርነት ብቻ ሳይሆን አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረን የማህበራዊ እሴት አለን። » ባየ እሱ በሚኖርበት ሰሜን ወሎ «ጥቁር አትልበሱ ብሎ የከለከለ አካል አንዳልታዘበም ገልፆልናል።  በአንጻሩ በኦሮሚያ ክልል የምትኖረው መገርቱ ሰሞኑን የነበራት ተሞክሮ አሳዛኝ እንደነበር ገልፃልናለች። እናቷን በሞት በማጣቷ ምክንያት ከቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪው በፊትም ጥቁር ትለብስ የነበረችው መገርቱ ለገጣፎ አካባቢ የገጠማትን እንዲህ ስትል ገልፃልናለች።   « ጥቁር ለብሼ ወደ ፍርድ ቤት ስሄድ መንገድ ላይ አስቆሙን እና በምን ምክንያት ነው ብለው አንገላቱን። እናታችን ሞታለች ብለን ብንላቸውም አላመኑንም። ቤተሰብ ጋር ተደውሎ እና ተጣርቶ ነው የለቀቁን።» መገርቱ ፍርድ ቤት እስክትደርስ ሶስት ጊዜ ወታደሮች አስቁመዋት እንደነበር ለዶይቸ ቬለ ገልፃለች።  ሀዘን ላይ ባትሆንም ለቅዱስ ሲኖዶሱ አጋርነቷን ለማሳየት «ጥቁር እለብስ ነበር» ትላለች። « አባታችን እኮ ናቸው ያዘዙት። ጥቁር ልበሱ ፀልዩ ያሉት እንጂ በራሳችን ያደረግነው አይደለም።»
ሰሞኑን መገርቱን የገጠማት ፈተና በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተስተዋለ ችግር እንደነበር የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል አስታውቋል። የማዕከሉ ኃላፊ የሆኑት ያሬድ ኃይለ ማርያም ለዶይቸ ቬለ እንደገለፁት የመንግስት ተቋማት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ዜጎች ሰሞኑን ጥቁር በመልበሳቸው ከስራ ተባረዋል ወይም ልብስ ካልቀየራችሁ አትገቡም ተብለዋል። ለመሆኑ አንድ መሥሪያ ቤት ጥቁር መልበስን መቼ ሊከለክል ይችላል? አቶ ያሬድ « በስራው ባህሪ ምክንያት ድርጅቱ ዩኒፎርም ያዘጋጀ ከሆነ፤ ለምሳሌ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች የግል የቤተሰብ ሀዘን እንኳን ቢገጥማቸው ጥቁር መልበስ አይችሉም።መሥሪያ ቤቱ ግን ዩኒፎርም ከሌለው ሰዎች የፈለጉትን ልብስ ቀለም መምረጥ ይችላሉ » ስለሆነውም ሰሞኑን የታየው የሰዎችን መብት የሚጥስ ተግባር ነው ይላሉi አቶ ያሬድ። 
ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ሌሎች የመብት ጥሰቶች ሰሞኑን እንደተፈፀሙ እና መረጃ እንደደረሰው የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ያሬድ ለዶይቸ ቬለ አስረድተዋል። አዲስ አበባ ውስጥ ጥቁር ልብስ ለብሰው ወደ ስራ እንዳይገቡ እየተጉላሉ የነበሩ ሰዎችን ቆመው ይቀርፁ የነበሩ ጋዜጠኞች መዋከብ እንደደረሰባቸው ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።

ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር ሆነው ያገለገሉት ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴም ቢሆኑ ሰሞኑን ከጥቁር መልበስ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ውስጥ የተስተዋለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው ይላሉ « ይሔ ደግሞ ለማንም የሚበጅ አይደለም። መንግሥት ከሆነ ይህንን እንደ ፖሊሲ የያዘው እልህ ውስጥ መግባት ያለበት አይመስለኝም። ከልክሎም የሚቆም ነገር አይደለም። ስለዚህ ይህንን መጋጫ ከማድረግ የፈለገው የፈለገውን ይልበስ ማለቱ የሚሻል ይመስለኛል።» «ሰው ቅሬታውን በፆም በፀሎት መግለፁ ነገሩን ያስተነፍሰዋል እንጂ አይጎዳም» የሚሉት የራስ ወርቅ « ያ ልብስ የህብረተሰቡን ሞራል የማይነካ እስከሆነ ወይም ሰው ራቁቱን እስካልሄደ ድረስ በልብስ ቀለው ውዝግብ ውስጥ መግባት የሰው መብት መንካት ነው» ይላሉ።
ባለፈው መስከረም ወር ኢራናዊቷ ወጣት ማሻ አሚኒ ፀጉሯን በአግባቡ አልሸፈንሽም በሚል በሀገሪቱ «ሥነ ምግባር ፖሊስ» ቁጥጥር ስር ውላ ከጥቂት ቀናት በኋላ ህይወቷ ሲያልፍ ኢራናውያን ተቃውማቸውን ለመግለፅ አደባባይ ወጥተዋል። ሌሎች በአለም አቀፍ ደረጃ ማህበራዊ መገናኛ ዘደዎችን በመጠቀም፣ ፀጉራቸውን ካሜራ ፊት በመቁረጥ እና በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞዋቸውን ሲገልፁ ተስተውሏል።  ሰዎች ጉዳዩ በቀጥታ ባይመለከታቸው እንኳን አጋርነታቸውን ማሳየት መፈለጋቸው ከምን የመነጨ ነው? ዶክተር የራስ ወርቅ « ይሔንን ያደረጉት ከኢራን ህዝብ ጋር ወይም ከተበደለው ወገን ጋር ግንኙነት ስላላቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ሁኔታም በአሜሪካ እና አውሮፓ ሰልፎች እየታዩ ነው። ተቃውሞዎች እየተሰሙ ነው። ለምንድን ነው ይኼን የሚሰማቸው ካልን ነግ በኔ የሚባል ነገር አለ።» ይላሉ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያው።

 ለተቃውሞ ጎዳና የወጡ ወጣቶች
አየር ጤና አካባቢ ለተቃውሞ ጎዳና የወጡ ወጣቶችምስል Seyoum Getu/DW


ልደት አበበ

እሸቴ በቀለ