1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ራዳርን ጨምሮ 17 ፈጠራዎችን ያበረከተው የ18 ዓመቱ አዳጊ

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 12 2014

ወጣት በረከተአብ ምህረተአብ የ18 ዓመት ወጣት እና የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነው።ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ሲሆን፤የፈጠራ ስራን የጀመረው የ4ተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ገና በለጋ እድሜው ነው።

https://p.dw.com/p/4AAAw
Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

«ስራዎቼን በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳወቅ ሀገሬን ማስጠራት እፈልጋለሁ»


የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ራዳር እንዲሁም በፀሀይ ብርሃን የሚሰራ የማብሰያ ምድጃን ጨምሮ 17 የፈጠራ ስራዎችን የሰራ  ታዳጊ ወጣትን ያስተዋውቃል።
ወጣት በረከተአብ ምህረተአብ የ18 ዓመት ወጣት እና የ11ኛ ክፍል የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ ነው።ትውልድ እና እድገቱ በደቡብ ክልል ስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ሲሆን፤የፈጠራ ስራን የጀመረው  የ4ተኛ  ክፍል ተማሪ እያለ ገና በለጋ እድሜው ነው። ይህ ታዳጊ ወጣት እስካሁን 17 የፈጠራ ስራዎችን በመስራት የፈጠራ ሀሳቡን ወደሚታይ እና ወደሚጨበጥ ቴክኖሎጂ መቀየር ችሏል።
በአካባቢው የሚያገኙ ነገሮችን በመጠቀም የተለያዩ ቁሳቁሶችን መስራት እንዲሁም የቤት ውስጥ መገልገያዎችን  መፍታት እና መገጣጠም ከልጅነቱ ጀምሮ የሚወደው እና የሚያዘወትረው ልምድ ቢሆንም ይህ ፍላጎቱ ወደ ተሻለ ፈጠራ እንዲያድግ ያደረገው ግን የተለዬ አጋጣሚ ነበረው።ይሄውም የአያቱ  ከተከራዮች ጋር የሚያደርጉት መብራት አጥፉ አታጥፉ ንትርክ ነበር።እናም በረከተአብ በአከራይ እና በተከራዮች መካከል ያለውን አለመግባባት ለማስቆም እና አያቱን ለማገዝ በልጅነት አቅሙ መፍትሄ ለመፈለግ ተነሳ ።

Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

በዚህ ሁኔታ የተመለከተውን ችግር ለመፍታት «ሚስድ ኮል በልብ ኮንትሮል»የተባለውን በርቀት በተንቀሳቃሽ ስልክ የቤት ውስጥ የኤለክትሪክ መብራትን ከየትኛውም ቦታ ሆኖ ማጥፋት እና ማብራት የሚችስችል ፈጠራ ከሰራ በኋላ፤ደህንነትን ለመጠበቅ ወደሚያግዙ የ(security)የፈጠራ ስራዎች በማተኮር ቤትን ከተለያዩ አደጋ የሚጠብቅ «ሴፍ ሃውስ» የተሰኘ የፈጠራ ስራ ሰርቷል።ይህ ፈጠራ በእሳት አደጋ ወቅት ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ውድመት ለመከላከል የሚያስችል  ሲሆን፤ቴክኖሎጅው በተገጠመለት ሴንሰር  እገዛ የእሳት አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የእሳት ማጥፊያውን በመክፈት ያለ ሰው እገዛ ራሱ ውሃ የሚረጭ ነው።ከዚህ በተጨማሪ  በቃጠሎው ወቅት  እሳቱ የሚያመነጨውን መርዛማ ጋዝ ወደ ውስጥ በመሳብ፤ሰዎች ሳይታፈኑና በመርዛማ ጭሱ ሳይበከሉ ከቃጠሎው እንዲያመልጡ የሚያደርግም ነው። ወጣቱ«ሴክሬት ሴል » የተባለ ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ከትክክለኛው የሚለይ ቴክኖሎጅም በተሳካ ሁኔታ መስራቱን ገልጿል።በእነዚህም ሴቭ አይዲያስ»ከተባለው ዓለም አቀፍ ድርጅት በጎርጎሪያኑ 2021 ዓ/ም የባለቤትነት መብት አግኝቷል።

Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

ሌላው የወጣቱ የፈጠራ ስራ  የፀሐይ ብርሃንን በመጠቀም ብቻ  ማብሰል የሚችል ምድጃ ሲሆን፤ይህ ቴክኖሎጂ የደን መጨፍጨፍን በማስቀረት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ያግዛል።በተጨማሪም በእንጨት እና በኩበት ለሚያበስለው የገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ምግብ በጭስ እንዳይበከልም ያደርጋል።
የቤት ውስጥ እና የመኖሪያ አካባቢን ደህንነት ከሚጠብቁ የፈጠራ ስራዎቹ ባሻገር ንብረትን  ከዘራፊዎች  መጠበቅ የሚያስችል እንዲሁም አውቶማቲክ የመንገድ መብራት፣በኤለክትሪክ የሚሰራ ብስክሌት እንዲሁም የርቀት መቆጣጠሪያ ራዳር እና ሌሎች የማኅበረሰቡን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎችም አሉት።
ከ12 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ በሰራቸው በእነዚህ የፈጠራ ስራዎቹ የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝቷል።

Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

ከነዚህም መካከል «ሴፍ ሃውስ» በተሰኘ የፈጠራ ስራው በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም በተካሄደ ሀገር አቀፍ ሳይንስ እና ምንድህስና ውድድር ላይ ሁለተኛ ሆኖ ተሸልሟል።ይህንን የፈጠራውን «ስቲም ፓወር »ከሚባለው የውጪ ድርጅት  ጋር በመሆን የ3ዲ ንድፍ  እና የሶፍትዌር  ማሻሻያ አድርጎበታል።ወጣቱ እንደሚለው  አንደ ሲሪ፣አሌክሳ እና ጎግል አሲስታንት የመሳሰሉ ሰው ሰራሽ አስተውሎቶችን አካቶ እንዲይዝ በማድረግ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችን በእጅ ስልኮቻቸው በቀላሉ በድምፅ እንዲሁም በፅሁፍ መቆጣጠር እንዲችሉ ለማድረግ አሁንም እየሰራ ነው።በገንዘብ እጥረት ሳቢያ ሁሉንም ስራዎቹን ወደ አገልግሎት መቀየር ባይችልም ሁለቱ ስራዎቹ ግን ወደ ምርት ለመግባት የተዘጋጁ መሆናቸውን ገልጿል።

Äthiopischer Erfinder Bereketab Mihiretab
ምስል Privat

ወጣት በረከተአብ የፈጠራ ችሎታውን በትምህርት ለመደገፍ የሶፍት ዌር ምህንድስና የመማር እቅድ አለው። ለወደፊቱ የራሱን ድርጅት በማቋቋም የፈጠራ ስራዎቹን ወደ ምርት እና አገልግሎት የመለወጥ እንዲሁም ሌሎችን የማገዝ ህልም አለው።
«ወደ ፊት ግቢ የመግባት እቅድ አለኝ።ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ መማር እፈልጋለሁ።እግዚአብሄር ብሎ ሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ከተማርኩኝ የራሴን «ፕላት ፎርም»ፈጥሬ ማኅበረሰቡን ችግር የሚፈታ ነገር «ክሬት»አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ።እንዲሁም የስራ እድል መፍጠር እፈልጋለሁ።»ካለ በኋላ፤ የፈጠራ ስራዎቹን «በዓለም አቀፍ ደረጃ በማሳወቅ ሀገሬን ማስጠራት እፈልጋለሁ።»በማለት ገልጿል።

ሙሉ ዝግጅቱ የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
እሸቴ በቀለ