1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጎበና ዳጬ

Oneko, Sella Oneko
ሐሙስ፣ ግንቦት 12 2013

ጎበና ዳጬ ወይም ራስ ጎበና ዳጬ የሸዋው ንጉስ የነበሩት ሣኅለ ማርያም ወይም ኋላ ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑት ዳግማዊ ምኒልክ የቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል። ራስ ጎበና ዳጬ ከምኒልክ ጎን በመሆን በምኒልክ ዘመን በርካታ ውጊያዎችን አሸንፈዋል። ይሁንና የራስ ጎበና የታሪክ ቅርስ ዛሬ ድረስ አከራካሪ ነው።

https://p.dw.com/p/3tKrS
DW African Roots - Gobena

ጎበና ዳጬ

ጎበና ዳጬ ማን ነበሩ?
ጎበና ዳጬ «ራስ» የሚል ትልቅ ማዕረግ ነበራቸው።  ራስ ጎበና ዳጬ የሸዋው ንጉስ የነበሩት ሳህለ ማርያም ወይም ኃላ ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሆኑት ዳግማዊ ምኒልክ የቀኝ እጅ እንደነበሩ ይነገራል። እናም ራስ ጎበና ከምኒልክ ጋር አንድ ላይ ሆነው የዛሬይቱን ኢትዮጵያ ቅርፅ መቀየር እንደቻሉ ይነገራል።
ጎበና ዳጬ መቼ ይኖሩ ነበር?
ጎበና ዳጬ በ 1810 ዓ ም ገደማ እንደተወለዱ ይታመናል። እሳቸውም ምኒልክን ሲያገለግሉ ቆይተው ንጉሠ ነገሥቱ ዙፋናቸው ላይ ከመውጣታቸው ጥቂት ወራት በፊት በ 1881 ዓ ም አርፈዋል።
የጎበና ዳጬ ምን አይነት ሰው ነበሩ?
ስለ ጎበና ዳጬ ባህሪ እምብዛም ማስረጃዎች የሉም። ነገር ግን የታሪክ ምሁራን ህይወታቸውን ሙሉ በውትድርና ያሳለፉ ሰው እንደነበሩ ይገልፃሉ። ለምኒልክም ታማኝ እንደነበሩም ይነገራል። ጎበና በዘመናቸው የነበረችውን ኢትዮጵያ በመገንባት ያምኑ ነበር። ምኒልክ እና ጎበና ወደ ደቡብ ያደረጉት የግዛት ማስፋፋት እስካሁን ድረስ በጣም አወዛጋቢ ነው። ለአንዳንዶች ራስ ጎበና የኢትዮጵያን ነገሥታት አንድ ያደረጉ ተደርገው ይታያሉ። ለአንዳንዶች ደግሞ ራስ ገዝ የሆኑ አካባቢዎችን የወረሩ ሰው ናቸው።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጎበና ዳጬን ልዩ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው?
ጎበና ከምኒልክ ጋር ብዙ ቅርበት የነበራቸው ሰው ናቸው።  ምኒልክ የሸዋው ንጉስ ከመሆናቸው በፊት የዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ እስረኛ ነበሩ። ከቴዎድሮስ እንዳመለጡም ሳህለ ማርያም ወይም ምኒልክ ጎበና ዳጬን ወዲያው ቤተ መንግሥታቸው ውስጥ ሾመዋቸዋል። ጎበና « ራስ» የሚለውን ከፍተኛ ማዕረግ ያገኙትም ያኔ ነው። ይህ ከፍተኛ ማዕረግም በርካታ ኃላፊነት አጎናፅፏቸዋል። ለምኒልክ እንዲዋጉ እና እንዲያስተዳድሩ ኃላፊነት ነበራቸው። የመከላከል ጦርነት የሚከፍቱት ላይ ውጊያ አካሂደዋል። ከዚህም ባሻገር የታሪክ ምሁሮች እንደሚሉት ጎበና የአካባቢው መሪዎች ለዳግማዊ ምኒልክ ክብር እና ታማኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ ረድተዋል።
የጎበና ዳጩ የታሪክ ቅርስ ለምን ያከራክራል?
ለአንዳንዶች የኦሮሞ ተወላጁ ራስ ጎበና የኢትዮጵያን ነገሥታት አንድ ያደረጉ ተደርገው ይታያሉ። ሌሎች ደግሞ እንደ ወራሪ ኃይል ያዩዋቸዋል። በተለይ  አሻፈረኝ የሚሉት ላይ ወይም ግብር በፍቃደኝነት የማይገብሩት ላይ በግዳጅ እንዲገብሩ ያስደርጉ እንደነበር ይነገራል። 
ከጎበና ዳጬ ሞት በኋላ ምን ተፈጠረ?
ጎበና ዳጬ አፄ ዮሀንስ 1881 ሲሞቱ በህይወት እንደነበሩ ይነገራል። ምኒልክ ግን ንጉሠ ነገሥት ሲሆኑ ለማየት አልበቁም። የሞቱት ይህ ከመሆኑ ጥቂት ወራት በፊት በዚያው ዓመት እንደሆነ ይነገራል። ይህም እቤታቸው አዲስ አበባ እንጦጦ አካባቢ ነው። እንደ ታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሹመት የምኒልክ እና የጎበና ወታደራዊ ጥምረት የቅኝ ግዛት ወታደራዊ ኃይሎችን መቋቋም የቻለ እና ኢትዮጵያን ያጠናከረ ነበር። ያኔ ጣሊያን በሰሜን በኩል ወደ ኢትዮጵያ የተጠጋችበት፤ ብሪታንያ ደግሞ ኬንያን፤ ሱዳንን እና ግብፅን ቅኝ ግዛት ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበረችበት ወቅት ነበር።  «ይህ ወቅት አብዛኛው የአፍሪካ ክፍል ከአውሮፓ ከፍተኛ ጫና የደረሰበት ጊዜ ነበር ። አውሮፓውያን አፍሪቃን የተቀራመቱበት የበርሊኑ ጉባኤ  እ.ኤ.አ. በ 1884 እንደነበር ይታወሳል ። እና ጎበና በ 1884 በሙያቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የነበሩበት ወቅት ነው። »
ራስ ጎበና  መሪያቸውን ምኒልክ ሲያገለግሉ ቆይተው ንጉሠ ነገሥቱ ዘውዱን ከመድፋታቸው ጥቂት ወራት በፊት በ 1881 ዓ ም አረፉ። በመጨረሻም ዳግማዊ ምኒልክ ጣሊያኖችን በአደዋው ጦርነት አሸንፈው ኢትዮጵያን ከአፍሪቃ ብቸኛዋ በቅኝ ያልተገዛች ሀገር አድርገዋል። 

ራስ ጎበና ዳጬ

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።